የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ትህነግ የጀመረው ተከታታይ ጦርነት ለበርካታ የትግራይ፣ የአፋርና የአማራ ነዋሪዎች መፈናቀል፣ ሞት፣ የንብረት ውድመት በኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተኛውን የሚያዝና አስደንጋጭ የክስረት አዋጆች የተመዘገበበት ነው። መቀለ ከተከበበች በሁዋላ በፕሪቶሪያ ስምምነት የተቋጨው ይህ አስከፊ ጦርነት በክረምት ዳግም እንደሚጀመር በረካቶች ቀጠሮ ይዘውለት እንደነበርም ይታወሳል።
አሁን ላይ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በጦርነቱ የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ እየተደረገ ነው። ከጠለምትና ማይጸብሪ አካባቢ የተፈናቀሉ ወገኖችን የመመለሱ ሂደት ሲጀመር አዳዲሶች ተቀላቀለው በተፈናቃይ ስም እንዳይገቡ አካባቢዎንና ነዋሪውን የሚያውቁ ከሁለቱም ወገን የተውጣጡ የመለያት ስራ እየሰሩ ሲሆን፣ ስራውን የሚመራው መከላከያ እንደሆነ ተመልክቷል።
የማስፈር ስራው ሲጠናቀቅ ከህዝብ የሚመረጡ አካባቢውን እንዲያስተዳድሩ እንደሚደረገና በሂደት በህዝብ ድምጽ ውሳኔ ሪፈረንደም ተካሂዶ ዘላቂ መፍትሄ እንደሚበጅ ስምምነት በተደረሰው መሰረት አዲስ የተቋቋሙት አስተዳደሮች እንዲፈርሱ መደረጋቸውን የተለያዩ የመረጃ ምንጮች ዘግበዋል። ቢቢሲ የሚከተለውን ዘግቧል።
በአማራ ክልል መስተዳደር ሥር የተቋቋሙት ሦስት የጠለምት እና ማይጸብሪ አካባቢ አስተዳደሮች ፈርሰው፤ ቢሮዎቻቸው መታሸጋቸውን የአካባቢው ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ። በጦርነት ምክንያት ከአካባቢዎቹ ተፈናቅለው የነበሩ ነዋሪዎችም ወደ ቀያቸው እየተመለሱ መሆኑ ተገልጿል።
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መነሳትን ተከትሎ በአማራ ክልል ሥር ሲተዳደሩ ከቆዩ አካባቢዎች ውስጥ የጸለምቲ (በአማራ ክልል ስር ጠለምት በሚል የሚጠሩት) ሁለት ወረዳዎች እና አንድ የከተማ አስተዳደር ተጠቃሽ ናቸው።
ምሥራቅ እና ምዕራብ ጠለምት ወረዳ እንዲሁም የማይጸብሪ ከተማ አስተዳደር የሚል አስተዳደራዊ መጠሪያ የተሰጣቸው እነዚህ አካባቢዎች በአማራ ክልል ውስጥ የነበሩት ለሰሜን ጎንደር ዞን ተጠሪ ሆነው ነው።
ላለፉት ዓመታት የቆው የሦስቱ መዋቅሮች አስተዳደር የፈረሰው ካለፈው ሳምንት አርብ ሰኔ 21/2016 ዓ.ም. አንስቶ እንደሆነ የሰሜን ጎንደር ዞን እና የአካባቢው አስተዳደሮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአማራ ክልል የተሾሙ አንድ የአካባቢው ባለሥልጣን፣ ሦስቱ የጠለምት አካባቢዎች አስተዳደር የነበራቸው “መንግሥታዊ መዋቅር” አገልግሎት መስጠት እንዲያቆም የተደረገው “ከፌደራል እና ከአማራ ክልል” ከተወከሉ የመንግሥት እና የብልጽግና ፓርቲ ኃላፊዎች ጋር ስብሰባ ከተደረገ በኋላ እንደሆነ ገልጸዋል።
አርብ ዕለት በነበረው በዚህ ስብሰባ ላይ አካባቢውን ሲመሩ የነበሩት በአማራ ክልል የተሾሙ አመራሮች “ሥራ እንዲያቆሙ ትዕዛዝ እንደተሰጣቸው” አስረድተዋል። ከዚሁ ዕለት አንስቶም የአስተዳደሮቹ ቢሮዎች መታሸጋቸውን ምንጩ ተናግረዋል።
ይህንኑ የሚያረጋግጥ ሪፖርት እንደደረሳቸው የሚገልጹ አንድ የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደር ምንጭ በበኩላቸው፤ “[የአካባቢዎቹ መዋቅሮች] እስከ አርብ ሥራ ላይ ነበሩ። ከአርብ በኋላ መከላከያ ቢሮዎችን የማሸግ ሥራ ሰርቷል” ብለዋል።
ከመዋቅሮቹ መፍረስ በተጨማሪ፤ በአካባቢዎቹ ላይ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት “ፖሊስ፣ ሚኒሻ እና ሰላማ አስከባሪ ኃይል” ከቅዳሜ ዕለት አንስቶ አጎራባች ወደ ሆነው የሰሜን ጎንደር ዞን አዲ አርቃይ ወረዳ “እንዲወጡ” መደረጉን የአካባቢው አስተዳደር ምንጭ ገልጸዋል።
ይህ ከተከናወነበት ቅዳሜ ዕለት አንስቶም በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት ከአካባቢው የተፈናቀሉ ነዋሪዎች መመለስ እንደጀመሩ ሁለቱ ምንጮች ገልጸዋል።
የአካበቢው አስተዳደር እና የሰሜን ጎንደር ዞን ምንጮች በበኩላቸው ተመላሾች ወደ ቅያቸው ከደረሱ በኋላ ወደ “ቀድሞ መኖሪያ ቤቶቻቸው” እየተመለሱ መሆኑን ተናግረዋል።
ተመላሾች ወደ የቤታቸው የመመለሳቸውን ጉዳይ ክትትል የሚያደርጉት በማይጸብሪ ከተማ የሚገኙ ከአማራ ክልል መንግሥት እና ትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የተወጣጡ ታዛቢዎች እንደሆኑ የጠለምት አካባቢዎች አስተዳደር ምንጭ ገልጸዋል።
ተወካዮቹ የታዛቢነት ሚናቸውን የሚወጡት “የአካባቢው አስተዳደሮች ፈርሰዋል? የታጠቁ ኃይሎች ወጥተዋል? ተፈናቃዮች በምን ዓይነት ሁኔታ እየገቡ ነው?” በሚሉት ጉዳዮች ላይ እንደሆነም ገልጸዋል።
ከሁለቱ ክልሎች የተወጣጡ ተወካዮች ተፈናቃዮች ጉዞ ከሚጀምሩበት እንዳባጉና ከተባለ የትግራይ ክልል አካባቢ ጀምሮ በታዛቢነት እንደተሰማሩ የሰሜን ጎንደር ዞን ምንጭ ጠቅሰዋል። ጨምረውም ተፈናቃዮች በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አማካኝነት እንዳባጉና ከደረሰቡ በኋላ ያለውን ሂደት የሚመራው የመከላከያ ሠራዊት መሆኑን አስረድተዋል።
የመከላከያ ሠራዊት ይህንን ሥራ የሚያከናውነው ተፈናቃዎቹ ከሚመለሱባቸው አካባቢዎች ተመርጠው ወደ እንዳባጉና በተወሰዱ ነዋሪዎች እገዛ እንደሆነም ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ የተመረጡት “ቀበሌዎቹን በደንብ ያውቃሉ” በሚል መነሻነት እንደሆነ የሚገልጹት ምንጩ፤ ተፈናቃዎቹ “በእርግጥም የአካባቢው ነዋሪ መሆናቸውን የማረጋገጥ” ሚና እንዳላቸው አስረድተዋል።
ለዚህ ሚና የተለዩ ሰዎች ከአካባቢዎቹ ተመርጠው ወደ እንዳባጉና መሄዳቸውን የጠለምት አካባቢዎች አስተዳደር ምንጭ አረጋግጠዋል። ይሁንና ምንጩ የተመረጡት ነዋሪዎች “በተባለው ልክ እየሠሩ አይደለም” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
እንዳባጉና ላይ የሚናወነውን “የተፈናቃዎችን ነዋሪነት የማረጋገጥ” ሥራን የሚታዘቡት ከአማራ እና ከትግራይ ክልሎች የተወጣጡ አመራሮች እንደሆኑ ሁለቱ ምንጮች ተናግረዋል።
ከአማራ ክልል በኩል ከተወከሉት አመራሮች መካከል እንደሆኑ የተጠቀሱት ሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ፤ የተፈናቃዎች መመለስን በመለከተ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ “ሥራ ላይ ነን። አሁን ማውራት አንችልም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
የትግራይ ክልል የማኅበራዊ ጉዳይ እና መልሶ ማቋቋም ቢሮ ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል ዘውዱ ኪሮስም በተመሳሳይ ስለ ተፈናቃዎች የመመለስ ሂደት መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ሜጀር ጄኔራል ዘውዱ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ፤ “የመጀመሪያውን ዙር ከጨረስን በኋላ ብንሰጥ ይሻላል” ብለዋል።
ለረጅም ጊዜ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች መካከል በይገባኛል ሲያወዛግቡ ከቆዩት አካባቢዎች የጦርነቱን መቀስቀስ ተከትሎ የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ በፌደራል መንግሥቱ እና በሁለቱ ክልሎች አማካይነት የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ የቆዩ ሲሆን፣ አሁን እየተካሄደ ያለው የመጀመሪያው እርምጃ እንደሂነ የቢቢሲ ዘገባ ያስረዳል።
ይህ በነዲህ እንዳለ በአማራ ክልልም ሆነ የማንነት ጥያቄ ሲያነሱ የቆዩት የህብረተሰብ ክፍሎች “ሰላማዊ ነዋሪዎች ይመለሱ፣ ወንጀለኞች ግን ለፍርድ ይቅረቡ” በሚል በተደጋጋሚ መናገራቸው አይዘነጋም። ሞረሽ አማራም በቅርቡ በተመሳሳይ ይህን አቋም እንደሚያራምድ ጠቅሶ መገለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።
እርምጃው ህዝብ በሰላም እንዲኖር ፖለቲካዊ ፍትጊያውን በማቆም እንዲደገፍ በርካቶች እያሳሰቡ ነው። ሁሉም ወገኖች በህዝብ መፈናቀልና እልቂት የሚያካሂዱት ቁማር አቁመው ማናቸውንም ውሳኔ ለህዝብ እንዲተው የሚያሳስቡ ” ሰሞኑን በተጀመረው መልሶ ማስፈር የተለያዩ ሰላማዊ ወገኖች ሲላቀሱና በዕምባ አንድነታቸውን ሲያሳዩ መየቱ ይበቃል። ቢዲያዎችም ይህንኑ የህዝብ እንድነት ማጉላት ይጠበቅባቸዋል” ሲሉ ከወዲሁ ጥሪ አቅርበዋል።