ባለፈው ሰኞ ዕለት ከደባርቅ ዩኒቨርስቲ በሁለት አውቶብስ ተሳፍረው ወደ ቤተሰብ እየተጓዙ የነበሩ ተማሪዎች ገብረ ጉራቻ ከተማ ሲደርሱ በታጣቂዎች መታገታቸውን ያመለጠ ተማሪ አረጋግጦ ነበር። ቲክቫህ ያነጋገረው ይህ ተማሪ “ሁለት አውቶብስ ተማሪዎች በታጣቂዎች ታግተዋል” ነበር ያለው። ዛሬ በተሰማ ዜና በርካታዎቹ ያለምንም ክፍያ ተለቀዋል። የተረፉት እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር እየተጠየቁ ነው። እገታው እንድተፈጸመ “ መከላከያ አብዛኛዎቹን ልጆች አስመልሶ መከላከያ ካምፕ ውስጥ ያደሩ ልጆች እንዳሉ፣ የተወሰኑ ደግሞ በሌላ መኪና ተሳፍረው አዲስ አበባ መግባታቸውን የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት አስታወቀዋል።
ከ2ኛ እስከ 4ኛ ዓመት ተማሪዎች መታገታቸውን የዓይን እማኞች፣ የታጋች ቤተሰብና ዩኒቨርሲቲው አረጋጠው መስክረው ተጨማሪ ማረጋገጫ ሰጥተዋል። እንደተባለው ከሆነ ሁለት አውቶብሶች ከደባርቅ፣ አንድ ደግሞ ከባህር ዳር ሰው ሞልተው ሲጓዙ የነበሩት አውቶቡሶች ውስጥ የነበሩ ተማሪዎች የታገቱት በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገብረ ጉራቻ አካባቢ ነው። አጋቾቹም የሸኔ ታጣቂዎች እንደሆኑ ተመልክቷል። ከገታው የተወሰኑ ተማሪዎች ሲያመልጡ ዛሬ ደግሞ የተወሰኑት 150 የሚደርሱ መለቀቃቸውን ቲክቫክ ቤተሰቦቻቸውን ጠቅሶ ዘግቧል።
ፖለቲካዊ ዓላማ የሌለውና እያደር ንግድ የሆነው የእግት ድራማ በመላው አገሪቱ መስፋፋቱ ዜጎችን አመርሯል። መፍትሄውም ግራ የሚያጋባ ሆኗል። በተደጋጋሚ ሰዎችን አገቱ የሚባል ዜና ከመሰማቱና ለማስለቀቅ ከሚጠይቁት ከፍተኛ ገንዘብ አንጻር ከመደናገጥ በስተቀር ታጣቂዎቹ በየአቅጣጫው ለምን እንደሚያግቱ፣ ምን ፖለቲካዊ ጥያቄ ለማስፈጸም እገታ እንደሚፈጽሙ፣ እነማንን መርጠው እንደሚያግቱ በጭራሽ አስታውቀው አያውቁም። በርስም የሚጠሩት ድርጅቶችም ሃአፊነት ወስደው አያውቁም። ይህ የጅምላ እገታ ህዝብን ከማሰቃየትና ከዘረፋ የዘለለ ዓላማ ስለሌለው ዜጎችን እረፍት ነስቷል።
ራሱን ደብቆ ማምለጥ እንደቻለ የተናገረው ተማሪ “ከታጋቾቹ መካከል የሚያውቃቸው የአይቲ ፣ የእንስሳት ሳይንስ ዲፓርትመንት ተማሪዎች እንዳሉ ገልጾ፣ ያገቷቸው የሸኔ ታጣቂዎች መሆናቸውን አስረድቷል።
አንድ የታጋች እህት ረቡዕ 3 ሰዓት ከ28 ደቂቃ ደውላ ስታናግረው እየሮጡ ነበር፣ የተኩስ ድምጽም ይሰማል። “በቃ ከአሁን በሁዋላ ስልኬ አይሰራም። ላታገኝኝ ትችያለሽ በታጣቂዎች ታግተናል” ስትል ለዚሁ አመለጥኩ ላለው ተማሪ ማናገሯን የቲክቫህ ዜና ያስረዳል።
ቤተሰቦች በገታው በከፍተኛ ጭንቀት ላይ እንደሚገኙ፣ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ታጋቾቹን በህይወት እንዲያተርፏቸው በመማጸን ድምጻቸውን ማሰማታቸውን የተለያዩ ዘገባዎች አመልክተዋል። በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ፤ የወንጌላውያን ክርስቲያን ተማሪዎች ህብረት በበኩሉ፣ እገታው እውነት መሆኑን እንዳረጋገጦ ርብርብ እንዲደረግ አሳስቧል።
ኀብረቱ በሰጠው ቃል “ አጋቾቹ ለአንድ ተማሪ 400 ሺህ ብር እየጠየቁ ነው። ‘ ገንዘቡን ካላመጣችሁ እንገድላችኋለን ’ እያሏቸው ይገኛል ” ሲል የሰማውን አስረድቷል።
የሞቱ ፣ የተጎዱ ስለመኖራቸው የደረሰው መረጃ እንደሌለ የገለጸው ማህበሩ ፣ የሚመለከታቸውን አካላት ሁሉ ለማነጋገር ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጿል። ገብረ ጉራቻ ላይ በታጣቂዎች የታጋቱ ተማሪዎች ቤተሰቦች በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ናቸው ፤ ምን እየተሰራ ነው ? በሚል ደባርቅ ዩኒቨርሲቲን ከየአቅጣጫው ጥያቄ ሲቀርበለት ነበር።
የዩቨርሲቲ ተወካይ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስማማው ዘገዬ “ ጉዳዩን ሰምተናል። ከዚህ ድርጊት ያመለጡ ተማሪዎች ነግረውናኛል። እንደነገሩኝ ማድረግ ያለብኝ ለሚመለከተው የፌደራል መስራያ ቤት፣ ለትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ሪፓርት ማድረግ ስለነበረብን አድርጌአለሁ ” የሚል መልስ ለቲክቫህ ሰጥተዋል።
“ እነርሱም ‘ ለሚመለከተው የጸጥታ አካል ሪፓርት እናደርጋለን ’ ብለውኛል ” ያሉት ዶክተር አስማማው፣ “ እኔ ከእገታ ያመለጡትን ልጆች Informally communicate አድርጌአቸው ነበር ” ብለዋል። አክለውም “ መከላከያ አብዛኛዎቹን ልጆች አስመልሶ መከላከያ ካምፕ ውስጥ ያደሩ ልጆች እንዳሉ ሰምቻለሁ። የተወሰኑ ደግሞ በሌላ መኪና ተሳፍረው አዲስ አበባ የገቡ እንዳሉ ሰምቻለሁ ” ሲሉ ተናገረዋል። “በጣም ዝናባማ ስለነበር መከላከያና ፓሊስ ሳይደርስባቸው አጋቾቹ ይዘዋቸው የሄዱ የተወሰኑ ልጆች እንዳሉ ሰምቻለሁ ” ብለዋል።
“ ቁጥራቸውን በእርግጠኝነት አላውቀውም ” ያሉት ዶክተር አስማማው፣ ተማሪዎቹ በሶስት አውቶብስ እንደተሳፈሩ መረጃው አለኝ። ከሶስቱ ሁለቱ አውቶብሶችን ነው ያስቆሟቸው ” ሲሉ አመልክተዋል።
በዛሬው ዕለት ወደ አዲስ አበባ ከተማ እየተመለሱ ነው የተባሉት ተማሪዎች በአጋቾች ስር ከነበሩት መካከል እና በተለያዩ ቦታዎች ተደብቀው ከእገታ ማምለጥ የቻሉ መሆናቸውን ቤተሰቦቻቸው ለቲክቫህ ተናግረዋል።
የወንጌላዊያን ተማሪዎች ህብረት በበኩሉ፣ አሁንም ገና በአጋቾች እጅ ያሉ ፣ ወደ ቤተሰብ መመለስ እየቻሉ ተሽከርካሪ ያላገኙ ፣ የተወሰኑት ታጋቾች ግን እንደተለቀቁ ማረጋገጡን ጠቁሟል።
ተለቀቁ የተባሉትም ከአጋቾቹ ጋር ተግባብተው እንጂ ገንዘብ ከፍለው እንዳልሆነ የተመላከተ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ በችግር ላይ እንደሆኑ መረጃው እንደደረሰው ገልጿል። ታጋቾቹ በትልቅ ጫካ ታጉረው እንደሚገኙ እና ገንዘብ እየተጠየቁ መሆናቸውን የታጋች ቤተሰቦች ጠቁመዋል።
በዚህ ኑሮ ውድነት ግማሽ ሚሊዮን ብር እንደማያገኙ ለገልጸው መንግስት ለታጋቾች እንዲደርስላቸው በእንባ ታጅበው ተማጽነዋል። ትምህርት ሚኒስቴር በጉዳዩ ዙሪያ ምን እየሰራ እንደሆነ ለመጠየቅ የተደረገው ሙከራ ተደጋጋሚ ስልክ ለማንሳት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ለጊዜው ሳይሳካ ቀርቷል።
ዜናው ከቲክቫህ፣ ቢቢሲና ማህበራዊ ሚዲያ የተውጣጣ ነው