የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የጸጥታ መደፍረስ ዘርፉን ክፉኛ እንደጎዳው ገለጸ፡፡
የሙያዎች ሁሉ መሠረት ትምህርት በመኾኑ በትምህርት ላይ ትኩረት ሰጥተው የሠሩ ሀገራት በሁሉም ረገድ ውጤታማ ሲኾኑ ይታያል፡፡
የትምህርት መሠረተ ልማት በበቂ ደረጃ ባልተሟላበት አማራ ክልል ተደጋጋሚ የሰላም መደፍረስ ችግሮች ዘርፉን ክፉኛ ጉዳት አድርሰውበታል ብሏል ትምህርት ቢሮ፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ በሰጠን መረጃ መሰረት በ2016 የትምህርት ዘመን በአማራ ክልል ያጋጠመውን የሰላም እጦት ተከትሎ ከ3 ሺህ 700 በላይ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፡፡ ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችም ከትምህርት ገበታ ውጪ ኾነዋል፡፡
የቢሮው ጽሕፈት ቤት ኅላፊ ደግሰው መለሰ እንዳሉትም የሰላም መደፍረስ ችግሩ ተማሪዎች በበቂ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳይከታተሉ አድርጓል፡፡
በቅርቡ በተሰጠው የስምንተኛ እና የስድስተኛ ክልል አቀፍ ፈተና ተማሪዎቻቸውን ያስፈተኑ ትምህርት ቤቶች ቁጥርም ዝቅተኛ መኾናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ ኅላፊው ጸጋዬ እንግዳወርቅ እንዳሉትም በዞኑ 245 ትምህርት ቤቶች የተዘጉ ሲኾን የትምህርት መሠረተ ልማቶችም ጉዳት እና ውድመት አስተናግደዋል፡፡
የመማር ማስተማር ሥራ በተካሄደባቸውም ትምህርት ቤቶችም ቢኾን ሕጻናት በተኩስ ድምጽ መካከል ስለነበሩ በቂ ዕውቀት ማግኘት አለመቻላቸው ተጠቅሷል፡፡
ትምህርት ቤቶች ሀገር ተረካቢ ትውልድ የሚወጣባቸው በመኾኑ ከማንኛውም የፖለቲካ እና የጦርነት አውድ ነጻ ሊኾኑ እንደሚገባም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ችግሮችን በመቅረፍ በ2017 የትምህርት ዘመን ውጤታማ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲካሄድ በክረምት የሚከናወኑ ተግባራትን ይበልጥ ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት፡፡
ትምህርት ቢሮው የትምህርት ቤቶችን ገጽታ ከማሻሻል ጀምሮ በሁሉም መስክ ውጤታማ ለመኾን የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ማሳደግ ይገባል ብሏል፡፡
ከሁሉም በላይ ግን አስተማማኝ ሰላምን ማስፈን ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ የትምህርት ቢሮ ጽሕፈት ቤት ኅላፊው ደግሰው መለሰ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፦ (አሚኮ)