በደቡብ ኢትዮጵያ ጎፋ ዞን በደረሰው ተከታታይ የመሬት መንሸራተት አደጋ የሞቱ ሰዎች ቁጥር እስከ 500 ሊደርስ እንደሚችል የተባበሩት መንግሥት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ገለጸ።
ጽህፈት ቤቱ ከአካባቢው ባለሥልጣናት ያገኘውን መረጃ መሠረት አድርጎ ባወጣው የሁኔታዎች መግለጫ ላይ ነው በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች አሃዝ እስከ 500 ሊደርስ እንደሚችል ያመለከተው።
እሁድ ሐምሌ 14 እና ሰኞ ሐምሌ 15/ 2016 ዓ.ም. በደቡብ ኢትዮጵያ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ተቀብረው የጠፉ ሰዎችን የማፈላለጉ ሥራ ዛሬም ለአራተኛ ቀን እየተካሄደ ነው።
በአደጋው ስፍራ የሚገኙት የቢቢሲ ዘጋቢዎች እንደገለጹት ዛሬን ጨምሮ በአካባቢው እየጣለ ባለው ዝናብ ውስጥ ጭምር ከተንሸራተተው መሬት ስር ለማውጣት የሚደረገው የነፍስ አድን ጥረት ቀጥሏል።
ባለፉት ቀናት በተደረጉት የፍለጋ ጥረቶች በአደጋው ሕይወታቸው አልፎ የተገኙ ሰዎች ቁጥር 257 የደረሰ ሲሆን፣ የሟቾች ቁጥር እስከ 500 ሊደርስ እንደሚችል የአካባቢው አስተዳዳሪዎች ስጋታቸውን መግለጻቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) አመልክቷል።
በመሬት መንሸራተቱ አደጋ ሕይወታቸው ማለፉ እስካሁን ከተረጋገጡት 257 ሰዎች በተጨማሪ 12 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ለሕክምና ወደ ሳውላ ሆስፒታል መወሰዳቸው ተገልጿል።
አደጋው በደረሰበት ስፍራ ነዋሪ የነበሩ ቢያንስ 125 ሰዎች ደግሞ ቤት ንብረታቸው በመውደሙ ምክንያት ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ተጠልለው ይገኛሉ።
ግለሰቦች እና የተለያዩ አካላት ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ድጋፍ የሚውል እርዳታዎችን በማሰባሰብ ወደ ስፍራው እየላኩ መሆናቸው እየተዘገበ ነው።
የቢቢሲ ዘጋቢ እንዳለው የአካባቢው ባለሥልጣናት ነዋሪዎችን በማስተባበር በእጅ የቁፋሮ መሳሪያዎች በመታገዝ ፍለጋ እያካሄዱ ሲሆን፣ የቁፋሮ መሳሪዎችን ወደ ቦታው ማስገባት ባለው ጭቃማ ሁኔታ ምክንያት አስቸጋሪ መሆኑን ገልጿል።
በነፍስ አድን ሥራው ላይ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን የኦቻ ሪፖርት አመልክቷል።
በመሬት መንሸራተቱ ምክንያት ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ቁጥር ከ15 ሺህ በላይ መድረሱን የመንግሥታቱ ድርጅት ተቋም ጠቅሶ፣ በአካባቢው ከፍተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ ስላለ በአስቸኳይ ወደ ሌላ ስፍራ እንዲወጡ መደረግ እንዳለበት ገልጿል።
ተጋላጭ ከሆኑት የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ቢያንስ 1,320 ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት ሲሆኑ፣ 5,293 ደግሞ ነፍሰጡር እና የሚያጠቡ እናቶች ናቸው ተብሏል።
የፌደራል መንግሥቱ ከክልሉ እና ከዞኑ ባለሥልጣናት ጋር በመተባበር ለተጨማሪ አደጋ ተጋላጭ ናቸው የተባሉትን ሰዎች ከስፍራው ለማስወጣት የሚያስችላቸውን ተግባራት እያጠናቀቁ መሆናቸውንም የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አመልክቷል።
BBC Amharic