የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መንግሥት የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመን በገበያ ሥርዓት እንዲመራ መወሰኑን ተከትሎ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ከዛሬ ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም. ጀምሮ መሻሻሉን አስታውቋል።
ብሔራዊ ባንክ በመግለጫው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያው በአዲሱ የውጭ ምንዛሪ መመሪያ መሠረት የሚተገበር ይሆናል ብሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓቱ የውጭ ምንዛሪ ተመን በባንኮች እና በደንበኞቻቸው መካከል ወደሚወስንበት የገበያ ሥርዓት ይሸጋገራል ያለ ሲሆን፤ በዚህ ውስጥ የባንኩ ሚና ገበያውን ማረጋጋት ላይ ያተኮረ እንደሚሆንም ተገልጿል።
ውሳኔው የብርን የመግዛት አቅም የሚያዳክም ነው።
ይህንን ውሳኔ ተከትሎ መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሜሪካ ዶላር መግዣ እና መሸጫ ዋጋ ላይ የ17 ብር ጭማሪ አደርጓል።
ባለፈው ሳምንት አርብ ባንኩ አንዱን የአሜሪካ ዶላር ሲሸጥ የነበረው 58.63 ብር የነበረ ሲሆን ዛሬ ወደ 76.23 ብር ከፍ ብሏል።
– ለመሆኑ የገንዘብ መግዛት አቅም መዳከም ምንድን ነው?
አንድ አገር መገበያያ ገንዘብ ከዋና ዋና የውጭ አገራት ገንዘቦች በተለይም ከአሜሪካን ዶላር አንጻር የነበረው ዋጋ ሲቀንስ የመግዛት አቅሙ ቀንሷል ይባላል።
ለምሳሌ ያህል አንድ ዶላር ይመነዘርበት ከነበረበት 57 ብር ወደ በ76 ብር መመንዘር ከጀመረ የብር መግዛት አቅም ተዳክሟል ይባላል።
በርካታ አገራት ፍላጎት እና አቅርቦትን ለመቆጣጠር የመገበያያ ገንዘባቸውን ያዳክማሉ።
የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም ጥቅሞች
የገንዘብ የመግዛት አቅም ሦስት ዋና ዋና ጥቅሞች አሉት።
የወጪ ንግድን ያሳድጋል
በወጪ ንግድ እና ገቢ ንግድ መካከል ያለውን ልዩነት ያጠባል
አገራት የገንዘብ የመግዛት አቅምን የሚቀንሱበት ዋነኛው ምክንያት የወጪ እና ገቢ ንግዳቸውን መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ በሚል ነው።
የገንዘብ የመግዛት አቅምን በመቀነስ ለወጪ ንግድ ሚቀርቡ ምርቶችን ዋጋ መቀነስ የሚቻል ሲሆን፣ ይህም በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪነትን ያሳድጋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ዋጋ ይጨምራል። ይህም ተጠቃሚዎች ከውጭ ከሚገቡ ምርቶች ይልቅ የአገር ውስጥ ምርቶችን እንዲገዙ እንደሚገፋፋ ይታመናል።
በአገር ውስጥ ያለው የገንዘብ ፍሰት መጨመር ደግሞ የአንድን አገር ኢኮኖሚ የሚያነቃቃ እንደሚሆን የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ይስማማሉ።
በዋጋ መዳከም ምንያት በሚፈጠር የዋጋ መርከስ ምክንያት የወጪ ንግድ ሲጨመር ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች ደግሞ በተቃራኒው ዋጋቸው ስለሚጨምር፤ ለገቢ ምርቶች ያለው ፍላጎት ይቀንሳል።
የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ደግሞ በገቢ እና በወጪ ንግድ መካከል ያለውን ልዩነት ያጠባል።
አገራት ያለባቸው ውጭ ዕዳ ከፍተኛ ከሆነ እና እድገታቸውን ከተፈታተነ የገንዘብ የመግዛት አቅም ማዳከምን ሊተገብሩ ይችላሉ። የገንዘብ የመግዛት አቅምን መቀነስ በረዥም ጊዜ ዕዳቸውን የመክፈል አቅማቸውን ያሳድግላቸዋል።
ለምሳሌ ያህል አንድ አገር ባለባት የውጭ ዕዳ ምክንያት በየወሩ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ወለድ የምትከፍል ከሆነ የአገሪቱን ገንዘብ የመግዛት አቅምን በመቀነስ የወለድ መጠኑን መቀነስ ይቻላል።
በዚህ አካሄድ ግን ከቦንድ ጋር ከተያያዙ ብድሮች ጋር ውጤታማ አይሆንም። ምክንያቱም የገንዘብ የመግዛት አቅም መቀነስ ይህን መሰሉን ብድር የመመለስ ዋጋን ይጨምረዋል።
የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም ጎጂ ጎኖች
የገንዘብ የመግዛት አቅምን በጊዜ ሂደት የምርቶችን እና የአገልግሎቶችን ዋጋ ሊጨምር ይችላል። ዋጋ ጭማሪው ግን በገቢ ምርቶች ውድድር እና በፍላጎት መጠን ላይ ይወሰናል።
የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም የወጪ ንግድን በማሳደግ የአገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት (ጂዲፒ) እና ዋጋ ንረትን ይጨምራል። አምራቾች ከውጭ የሚያሰግቡት ጥሬ ዕቃ ዋጋው ስለሚጨምር የምርቶቻቸውን ዋጋ ለመጨመር ይገደዳሉ።
ዋናው ከገንዘብ የመግዛት አቅም ጋር መዳከም ጋር የሚያያዘው ጉዳይ የገበያ አለመረጋጋት ነው። የኢኮኖሚው አቅጣጫ በግልጽ ስለማይታወቅ በፍላጎት እና በአቅርቦት ላይ አለመረጋጋጥ ይፈጥራል። ይህም ኢኮኖሚያዊ ወድቀትን ሊያስከትል እንደሚችል ይታመናል።
የገንዘብ የመግዛት አቅምን በማዳከም የሚታወቁ አገራት
ቻይና የአገር ውስጥ ጠቅላላ ምርትቷን ለማሳደግ የገንዘብ የመግዛት አቅምን አዳክማለች። ከዚያወዲህ በዓለም ንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ተጽዕኖ ፈጠሪ ለመሆን በቅታለች።
እአአ በ2016 የተደረገውን የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተከትሎ ገንዘቧን በተመለከተ ውሳኔ እንደምታስተላልፍ አስታውቃ ነበር።
ከአሜሪካ ዶላር አንጻር የቻይናው ዩዋን ያለውን አቅም ለማሳደግ የተያዘውን ዕቅድ ከግምት በማስገባት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቻይና ምርቶች ላይ ከፍተኛ ታሪፍ ጫኑ።
ግብፅ በ2016 (እአአ) መገበያያ ገንዘቧ ከዶላር አንጻር በ14 በመቶ እንዲዳከም አደረገች። ይህም የትይዩ ገበያውን እንቅስቃሴ ለመግታት ያለመ ነበር።
ጥቁር ገበያው ግን በግብፅ ፓውንድ እና በአሜሪካ ዶላር መካከል ያለውን የመግዛት አቅም ይበልጥ በማስፋት ምላሽ ሰጥቷል። በዚህም አገሪቱ ያሰበችውን ያህል ውጤት አግኝታለች ለማለት አይቻልም።
ከኢትዮጵያ አንጻርም ውሳኔው ምን ውጤት እንደሚያመጣ በሂደት የሚታይ ቢሆንም፣ በርካቶች አሁን ያለውን የሸቀጦች የዋጋ ውድነት ሊያባብሰው ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።
ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት አገሪቱን ይህንን እርምጃ እንድትወስድ ለዓመታት ግፊት ሲያደርጉ ቢቆዩም ተቀባይነት ሳያገኝ ቆይቶ ነበር።
በጦርነት እና በዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ምክንያት በአገሪቱ ተፈጠረውን ውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር እንዲሁም ታይቶ በማይታወቅ የዋጋ ንረት የተዳከመውን ምጣኔ ሀብት ለመደገፍ መንግሥት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው።
ይህ የውጭ ምንዛሪ ግብይት በገበያ ሥርዓት እንዲተመን የሚያደርገው ውሳኔም የተከታታይ ማሻሻያዎቹ አንድ አካል ነው።
BBC Amharic