– ባለሥልጣኑ የቡና የግብይት ሰንሰለትን በማሳጠር ችግሩን ሙሉ ለሙሉ መፍታቱን አስታውቋል
አዲስ አበባ፡- ቡና ላኪዎች ለሚገዙት ቡና ክፍያ በወቅቱ ባለመፈፀማቸው ምክንያት ከአምራቾች ጋር እየተጋጩ መሆኑን ቡና አቅራቢዎች አስታወቁ፡፡ የቡና የግብይት ሰንሰለትን በማሳጠር ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ተፈቷል ሲል የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን በሰጠው ምላሽ አሳውቋል፡፡
ቡና አቅራቢ የሆኑት አቶ አበራ ማንደፍሮ፤ ቡና ከአምራቾች በኩፖን ተረክበው ለላኪዎች እንደሚያቀርቡ ለኢፕድ ገልጸዋል፡፡
ላኪዎች ላቀረብንላቸው የቡና ምርት ክፍያ ሲፈፅሙ ለአርሶ አደሮች በተስማሙበት ዋጋ መሠረት ክፍያ እንደሚፈፅሙ የተናገሩት አቶ አበራ፤ ነገር ግን ቡና ላኪዎች ክፍያ በሰዓቱ እንደማይከፍሏቸው አብራርተዋል፡፡
ይህም ለአምራቶች በተነጋገርነው መሠረት በሰዓቱ መክፈል እንዳይችሉ እንዳረጋቸው እና ወደ አላስፈላጊ ግጭት እንደሚያስገባቸው ነው የገለጹት፡፡
ላኪዎች ለሚቀርብላቸው የቡና ምርት በጊዜ እንደሚከፍሉ ውል ገብተው ቢወስዱም ውላቸውን በተያዘው የጊዜ ገደብ መፈፀም ሳይችሉ ይቀራሉ ያሉት አቶ አበራ፤ በዚህም ለተለያዩ ችግሮች እየተጋለጥን ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በአምራች፣ አቅራቢና በላኪ መካከል የተፈጠረው የቀጥታ የግብይት ሥርዓት ላኪዎች በክፍያ ዙሪያ እየፈጠሩት ያለውን ችግር ሊፈታ አልቻለም፤ በትኩረት ሊሠራበት ይገባል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
የቡና ላኪና አቅራቢ የሆኑት አቶ አኗር ጂያድ፤ ችግሩ እንዳለ አምነው፤ ሆኖም ችግሩ የሚፈጠረው ራሳቸው ቡና አቅራቢዎች በሚፈጥሩት ስህተት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
አንዳንድ ጊዜ አቅራቢዎች ለላኪዎች የሚያሳዩት የቡና የጥራት ናሙናና የሚልኩት ምርት የተለያየ ነው የሚሉት አቶ አኗር፤ ይህም ክፍያ ለመፈፀም መጓተት እንደሚፈጥር ያስረዳሉ፡፡
ቡና ላኪው መጀመሪያ የተቀበለው የቡና ናሙና እና የተላከለት ምርት ጥራቱ አልመጣጠን ሲለው በናሙናው ጥራት ልክ ክፍያ ለመፈፀም እንደሚቸገር ጠቁመው፤ በዚህ ምክንያት በአቅራቢው እና በላኪው መካከል በሚፈጠር ክርክር ክፍያው ይዘገያል ብለዋል፡፡
ችግሩን ለመፍታት አቅራቢዎች ያሳዩትን የቡና ናሙና ጥራቱን ጥብቀው መላክ አለባቸው ያሉት አቶ አኗር፤ ላኪዎችም ክፍያውን በሰዓቱ ሙሉ በሙሉ ከፍለው መውሰድ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ አመላክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) የተነሳው ቅሬታ ከዛሬ ሁለት፣ ሶስት ዓመት በፊት የነበረ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ተቀርፏል ሲሉም ያብራራሉ፡፡
እንደ ዶክተር አዱኛ ገለፃ፤ በአምራቾች፣ በአቅራቢዎችና በላኪዎች መካከል የተዘረጋው የቀጥታ የግብይት ሥርዓት አቅራቢዎች ለአምራቾች፣ ላኪዎች ለአቅራቢዎች ሙሉ ክፍያ በጊዜውና በሰዓቱ በመፈፀም እንዲገበያዩ ትልቅ እድል የከፈተ በመሆኑ በክፍያ ዙሪያ ጋር የነበሩ ችግሮች ሙሉ ለሙሉ ተፈትተዋል፡፡
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በዘረጋው የቀጥታ የግብይት አሠራር ከአቅራቢዎች ቡና ወስደው ክፍያ ያልፈፀሙ ላኪዎች ፊት ለፊት በማገናኘት እንዲከፍሉ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት ላኪዎች ለአቅራቢዎች የከፈሉበትን የባንክ ደረሰኝ ሳያሳዩ ምርቱን እንዳይወስዱ ተደርጓል ያሉት አዱኛ (ዶ/ር)፤ ይህም ችግሩን በመቅረፍ ትልቅ ውጤት አሳይቷል ብለዋል፡፡
ታደሠ ብናልፈው አዲስ ዘመን ሐምሌ 4 ቀን 2016 ዓ.ም