በገበታ ለሀገር መርኃ ግብር የተገናባው የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ዛሬ ተመርቋል፡፡ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላችው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የጎርጎራ ፕሮጀክት እጅን ከአፍ ላይ በሚያስጭን መልኩ ማለፊያ ኾኖ ተጠናቅቋል ብለዋል፡፡ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም በርካታ ውጣ ውረዶች ቢኖሩበትም ዛሬ በስኬት አንድ ኾነን እንድናስመርቅ የበርካቶች እምነት፣ ቁርጠኝነት እና ታታሪነት ታይቶበታል ነው ያሉት፡፡
በጎርጎራ ፕሮጀክት ግንባታ ሂደት ውስጥ ከጅማሬው እስከ ፍጻሜው 17 ጊዜ ተመላልሻለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጎርጎራ ፕሮጀክት ያስተማረን እውነት ሀገር በእጆች እንጅ በምላስ እንደማትሰራ ነው ብለዋል፡፡ በመመላለሳቸው ውስጥም የትናንቷን ጎርጎራ ከዛሬዋ ጎርጎራ የሚያነጻጸሩበት እድል እንዳገኙ ጠቁመዋል፡፡
“ጎርጎራ ትናንት ሳየው የገባኝ ጎርጎራ ፊደል ነው፣ ድምጸት እና ምስል ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፊደል ኾኖ ማንም ሊሰርዘው፤ ማንም ሊደልዘው በማይችል መንገድ ታሪክ ጽፏል ብለዋል፡፡ ጎርጎራ ድምጸት ኾኖ ህልማችንን ለሕዝባችን አሰምቷል፤ ጎርጎራ ስእልም ኾኖ ሥራችንን እና ህልማችንን ግልጥ አድርጎ አሳይቷል ነው ያሉት፡፡ ህልሞቻችን ማየት ያልቻሉ ወንድም እህቶቻችን ጅማሮዎቻችን አይተው እንደሚረዱን ተስፋ አደርጋለሁም ብለዋል፡፡
የጎርጎራ ፕሮጀክት ለሕዝባችን ያለንን ፍላጎት እና መሻት ታሪክ እና ትውልድ መስካሪ እንዲኾን ያግዛል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነገር ግን የሕዝባችንን ሕይዎት የመለወጥ ጽኑ ፍላጎታችን እና ህላማችን ብቻውን አይገልጥም ነው ያሉት፡፡ ለዚያም ሲባል በባሕር ዳር እና ጎንደር ከተሞች ላይ ተያያዥ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል፡፡
ጎርጎራ – የዐቢይ ሙሽራ
ባሕር ዳር በተፈጥሮ ውብ ናት፤ ሥራችን ውበት መግለጥ እንጅ ውበት መጨመር አይኾንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለዚያ የሚኾን ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነ አንስተዋል፡፡ ከቦሌ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቀጥሎ ግዙፍ የአየር ማረፊያ ማስፋፊያ፣ ከ33 ኪሎ ሜትር በላይ ደረጃውን የጠበቀ መንገድ እና ሌሎችም እየተሠሩ ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልእክታቸው ባሕር ዳርን ከጎርጎራ ጋር ለማንሰላሰልም እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ከ180 በላይ ሰው የመጫን አቅም ያላቸው ሁለት ግዙፍ መርከቦች ተገዝተው ወደብ ላይ እንደደረሱ ጠቁመዋል፡፡ ተጓጉዘው ጣና ሐይቅ ላይ ሲደርሱ በባሕር ትራንስፖርት በኩል የተሳለጠ አገልግሎት ይሰጣሉ ነው ያሉት፡፡ የጎርጎራ አምሳያ በግል ባለሃብት በባሕር ዳር የሚገነባው ሆቴልም አጋዥ የቱሪስት መዳረሻ ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የጎርጎራ ፕሮጀክት ከሌሎች ጋር መስተሳሰር ካልቻለ ብቻውን ደሴት ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም ሲባል ከባሕር ዳር እና ጎንደር ከተሞች ጋር ማስተሳሰር ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
ጎንደር ታሪክ ጠገብ ውብ ከተማ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመንግሥታት ትኩረት መነፈግ ምክንያት ተረስቶ ቆይቷል ብለዋል፡፡ የጀመርናቸው አንዳንድ ፕሮጀክቶች ቢኖሩም በሥፋት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የፋሲል ቤተ መንግሥት ሥራው እንደገና መጀመሩንም አንስተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፒያሳ እስከ ፋሲል ቤተ መንግሥት የኮሪደር ልማት ዛሬ ተጀምሯል ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱን በአንድ ዓመት ጊዜ እናጠናቅቃለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥንታዊነቱን እና ታሪካዊነቱን በጠበቀ መልኩ ይሠራል ነው ያሉት፡፡
ሀገርን ለትውልድ መገንባት ስንፈልግ ከበድ ከበድ ያሉ ውሳኔዎችን መወሰን ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ውሳኔዎቹ በወቅቱ ደጋፊ ላይኖራቸው ይችላል፤ ነገር ግን መስካሪው ታሪክ ፈራጁ ትውልድ ይኾናል ብለዋል፡፡ ዛሬ የምንወስናቸው ውሳኔዎች የሚጎረብጥ የሚመስላቸው ቢኖሩም ሳንታክት እና ሳንሰለች ካልሰራን በቀር ለልጆቻችን የበለጸገች ሀገር ማስረከብ አንችልም ነው ያሉት፡፡
በተፈጥሮ የታደለች ሀገር አለችን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእኛ ስንፈት እና ልግመት ከምንለምን ሳይሰለቹ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃሳባችን፣ ህልማችን እና ጅማሮዎቻችን አይቶ ተባባሪ ሊኾን ይገባል ሲሉም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
አሚኮ