ባለፋት 11 ወራት 466 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ገለጹ።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ሥብሠባ እየተካሄደ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ገቢ እና ወጭን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እንዳሉት በበጀት ዓመቱ መንግሥት 529 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ ባለፉት 11 ወራት 466 ቢሊዮን ብር ሰብስቧል። የዕቅዱን 96 በመቶ አሳሳክቷል ነው ያሉት።
ወጭን በተመለከተ 730 ቢሊዮን ለማውጣት አቅዶ 716 ቢሊዮን ብር ወጭ ኾኗል። ይህም 98 በመቶ መኾኑ ነው።
በገቢ እና ወጭ መካከል ያለው የበጀት ጉድለት 2 ነጥብ 5 ነው።
በወጭ እና ገቢ ውስጥ ኮንትሮባንድ፣ የገቢ ሥወራ እና የንግድ ማጭበርበር ገቢ ለመሰብሰብ ጋሬጣ ኾኗል።
ከጂዲፒ ግብር የሚሰበሰበው 7 በመቶ ብቻ ነው።
ከለውጡ በፊት በሁሉም መስኮች 19 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ይገኝ ነበር። ከለውጡ በኋላ 23 ቢሊዮን ዶላር ማመንጨት ተችሏል።
ዘንድሮ ወደ ውጭ ከወጣው ሸቀጣሸቀጥ 10 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል።
ጥራጥሬ፣ ቡና፣ አበባ፣ ወርቅ… አምና ከነበረው ገቢ ዘንድሮ መሻሻል አሳይተዋል። ዘንድሮ ወደ ውጭ ከተላከው ከአምናው በአራት በመቶ አድጓል።
ሪሚንታንስ ከአምናው ከ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል።
ወደ ሀገር ውስጥ ከምናስገባው ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ በሀገር ውስጥ ተመርቶ መሸፈን ተችሏል።
40 በመቶ የፋብሪካ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት ተችሏል።
ለነዳጅ በየዓመቱ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ይወጣል። ለማዳበሪያ 1 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ወጭ ይኾናል። ለዕዳ ክፍያ 2 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ይኾናል።
በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ለነዳጅ፣ ለአፈር ማዳበሪያ እና ለዕዳ ክፍያ 7 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ኾኗል።
“ምርት እና ምርታማነት እያደገ ሲሄድ የኑሮ ውድነቱም እየተሻሻለ ይሄዳል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ላይ እንዳሉት የውጭ ባንኮችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት ውድድርን እንደሚፈጥር አንስተዋል፡፡
ሀገሪቱ ለረዥም ጊዜ ባንኮችን ለውጭ ውድድር ዝግ አድርጋ ስትሠራ መቆየቷን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ላይ ግን ውድድርን ለመፍጠር ባንኮችን ለውጩ ዓለም ክፍት ማድረግ እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡
ይህን ለማድረግም በባንኮች ላይ መሠራት ያለበት ሥራ ስለመሥራቱ ነው ያስረዱት፡፡ ባንኮችም ጤናማ በሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኙም አረጋግጠዋል፡፡
የኑሮ ውድነት በዓለም ደረጃም ፈታኝ እንደኾነ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓለም ላይ ያሉ ያደጉ ሀገራት ጭምር የኑሮ ውድነቱን ለምርጫ ቅስቀሳ እንደመወዳደሪያ እየተጠቀሙ እንደኾነ ገልጸዋል። ይህም ችግሩ ምን ያክል ስር የሰደደ እንደኾነ ማሳያ ስለመኾኑ አስረድተዋል፡፡
የኑሮ ውድነት በዓለም ላይ ስብራት፣ ጭንቀት እየኾነ ስለመምጣቱ አብራርተዋል፡፡ የኢትዮጵያም ከዚህ የተለየ እንደማይኾን ነው የተናገሩት፡፡
ልማትን የሚያፋጥን መንግሥት በዛውም የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ ከባድ እንደሚኾንበት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊዚህም ምክንያቱ ለልማት የሚያውለውን ገንዘብ ለኑሮ ውድነት መቀነሻ በድጎማ ስለሚያውለው እንደኾነም አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ልማቷን ሳታቋርጥ የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ ያደረገችው ጥረት የተሻለ ውጤት የተመዘገበበት እንደኾነም ነው ያስገነዘቡት፡፡
ምርታማነትን ማሳደግ የሁሉ ነገር ቁልፍ ነው በሚል ሢሠራ ስለመቆየቱም ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ስትሠራው የቆየችው የኩታገጠም የስንዴ፣ የሩዝ፣ የፍራፍሬ፣ የጓሮ አትክልት፣ የተማሪዎች ምገባ፣ የማዕድ ማጋራት እና መሰል ሥራዎች ለውጥ ስለማምጣታቸው ነው ያስገነዘቡት፡፡
ምርት ተመረተ ይባላል ግን ዋጋ አልቀነስም ለሚለው ሃሳብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲያብራሩ የምርት ዕድገት አለ ሲባል ምርትን ሁሉም ቦታ ማዳረስ እና የገበያ ሁኔታውን ማየት ስለሚፈልግ ይህ ሌላ ፈተና እና መሠራት ያለበት ሥራ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
ሀገሪቱ በምርት ላይ ውጤት ማስመዝገብ የቻለችው መሬት፣ ውኃ እና የሰው ኀይል ስላላት እንደኾነም ነው ያስገነዘቡት፡፡
የሌማት ትሩፋት ከተጀመረ ሁለት ዓመት ያልሞላው ቢኾንም ያስገኘው ውጤት ግን ተጨባጭ እና ሊታይ የሚችል ስለመኾኑም ነው ያስረዱት፡፡
ባለፈው ዓመት 30 ሺህ የንብ ቀፎ የነበረ ሲኾን በዚህ ዓመት ግን 1 ሚሊዮን የንብ ቀፎ ስለመድረሱ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማር ምርትም በሰባት እጥፍ ስለማደጉ ነው ያብራሩት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው “በየደረጃው ምርት እና ምርታማነት እያደገ ሲሄድ የኑሮ ውድነቱም እየተሻሻለ እንደሚሄድ” ነው ያብራሩት፡፡
Via (አሚኮ)