የፋኖ ኀይሎች ለድርድር እንዲዘጋጁ ጥረት እያደረገ መሆኑን የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል አስታወቀ።
ፋኖዎች ከተበታተኑበት ተሰባስበው ራሳቸውን ለሰላም ንግግር እንዲያዘጋጁ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል አስታውቋል፡፡
ካውንስሉ የሰላም ጥሪ ከማድረግ ባሻገር ሁለቱን ወገኖች በቅርበት እያነጋገረ እንደሚገኝም የካውንስሉ ሰብሳቢ አቶ ያየህይራድ በለጠ ተናግረዋል፡፡
አቶ ያየህይራድ “የፋኖ ወንድሞቻችን መሪዎችን በአካል፣ በስልክ እና ሰው በመላክ ላቀረብንላቸው የድርድር ሀሳብ ፈቃደኝነታቸውን ስላሳዩን በካውንስሉ ስም አስቀድመን እናመሠግናቸዋለን” ብለዋል።
ድርድሩ እንዲሳካ የፋኖ ኀይሎችን ወደ አንድ አደረጃጀት ማምጣት ትልቁ ተግባር ነው ያሉት አቶ ያየህይራድ፤ በዚህ ተግባር ኅብረተሰቡ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራን ሕዝብ ከጉስቁልና ለመታደግ የፋኖ ኀይሎች ወደ አንድነት መምጣትና ድርድሩ እንዲካሄድ ማድረግ እንደሚገባቸው ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል መንግሥት በካውንስሉ የቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ ለድርድር ዝግጁ መሆኑን የገለጹት ሰብሳቢው፤ ኅብረተሰቡ ለሰላም ንግግሩ ስኬት ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአማራ ክልል ሕዝብ በጫካ ያሉ ልጆቹ ወደ ንግግር እንዲመጡ ሊመክር እና ሊያበረታታ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ዮናስ አሽኔ (ዶ.ር) በበኩላቸው፤ “መንግሥትም ሆነ ታጣቂዎች በሰላማዊ ንግግር ችግሮችን ለመፈታት በቁርጠኝነት ሊሠሩ ይገባል” ብለዋል፡፡
ወደ ሰላም ንግግር የሚደረገው ጉዞ የተሳካ እንዲሆንም ተኩስ ማቆም፣ ከጥላቻ ንግግር እና ከሌሎች ለሰላም ጥረቱ እንቅፋት ከሚሆኑ እርምጃዎች መታቀብ እንደሚገባ አበክረዋል፡፡
የአማራ ክልል ሰላምን ለመመለስ እየተደረጉ ካሉ ጥረቶች መካከል ሰኔ 17 እና 18 ቀን 2016 ዓ.ም የተደረገው የሰላም ኮንፈረንስ አንዱ ሲሆን በኮንፈረንሱ ማጠቃለያ ላይ በመንግሥት እና በፋኖዎች መካከል የሚደረገውን ድርድር እንዲያመቻች 15 አባላት ያሉት ካውንስል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወቃል፡፡
(አሚኮ)