ህወሓት በ50 አመታት ታሪኬ አጋጥሞኝ የማያውቅ ፈተና ውስጥ ነኝ አለ፣ በቀጣይ ሳምንታት የፓርቲ ጉባኤየን ለማካሄድ ወስኛለሁ ብሏል!
የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ለ11 ቀናት ሳካሂደው የነበረው የፓርቲው ከፍተኛ አመራር ስብሰባ እና ግምገማ አጠናቅቂያለሁ ሲል ዛሬ ሐምሌ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።ሳካሂደው የሰነበትኩት በፓርቲው አመራራ ላይ ያተኮረ የ11 ቀናት ስብሰባ እና ግምገማ “ፓርቲውን ከመበታተን ሊታደግ የሚችል ጉባኤ እንዲካሄድ ምቹ ሁኔታዎችን የፈጠረ ነው” ብሏል።
በያዝነው ሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም ባሉት ቀጣይ ጥቂት ሳምንታት የፓርቲ ጉባኤ ይካሄዳል ሲል የገለጸው የህወሓት መግለጫ “ብሔራዊ ህልውናችንን ማረጋገጥ ቀዳሚ ተልኳችን ነው” ሲል አስታውቋል።
አሁን “በፓርቲው የማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ያጋጠመው ችግር ድርጅቱ ከተመሰረተ ጀምሮ ባሉት 50 አመታት አጋጥሞኝ አያውቅም” ያለው ህወሓት ዋነኛ የለየኋቸው ችግሮቼ “ቡድንተኝነት፣ ፀረ ዲሞክራሲያዊነት፣ ጎጠኝነት እና ሙስና ወደ ላቀ ደረጃ አድጎ ፓርቲውን አላፈናፍን ከማለት ባለፈ የመፈራረስ አደጋ ደቅነውብኝ ነበር” ብሏል።
[Addis Standard]