የዐቃቤ ህግ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
ተከሳሾቹም÷ 1ኛ የሁለተኛ ተከሳሽ ወኪል የሆነው ፍፁም ተክሉ አፅብሀ፣ 2ኛ የኡስታስ አቡበከር ሁሴንን ተሽከርካሪ በስሙ አዙሯል የተባለው አበራ ነጋሳ ሆርዶፋ፣ በአዲስ አበባ አሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አዲስ ከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ውስጥ የተሽከርካሪ አገልግሎት ባለሙያ ናቸው የተባሉት አብዮት አበራ፣ ልየው አሰፋ አንዱአለም፣ አለሙ ኦልጅራ ናቸው።
በተራ ቁጥር 6 እና 7 ላይ የተጠቀሱት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የንፋስ ስልክ ፖሊስ መምሪያ የልዩ ልዩ ወንጀሎች ቡድን ኃላፊ ዋና ሳጅን መኳንንት ተመስገን እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የኢንተለጀንስ ቡድን አባል የሆነው ዋና ሳጅን ገመቹ ብርሃኑን በሚመለከት በወቅቱ ታዘው በስራ ላይ ተመድበው እንደነበር ተጠቅሶ ተቋሞቻቸው ማረጋገጫ በማቅረባቸው ምክንያት ነጻ ተብለዋል።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በአጠቃላይ በሰባት ተከሳሾች ላይ የወንጀል የተሳትፎ ደረጃቸውን ጠቅሶ ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸው ነበር።
በአጠቃላይ የተሳትፎ ደረጃን ጠቅሶ ዐቃቤ ህግ ባቀረበው ክስ ዝርዝር ላይ ተከሳሾቹ ንብረትነቱ የግል ተበዳይ ኡስታዝ አቡበከር ሁሴን መሀመድ የሆነውንና የዋጋ ግምቱ 7 ሚሊየን ብር የሆነ ቪ8 ተሽከርካሪ ሀሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም፣ ማህደሩን በመለወጥና በሽያጭ በማስተላለፍ ለመውሰድ ሲሉ የተያዙ መሆኑ ተጠቅሶ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ነበር የተከሰሱት።
ተከሳሾች የክስ ዝርዝር ከደረሳቸው በኋላ የወንጀል ድርጊቱን አልፈጸምንም በማለት የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ህግም የግል ተበዳዩን ኡስታስዝ አቡበከርን ጨምሮ ሌሎችንም ምስክሮች አቅርቦ የምስክር ቃላቸውን በችሎት አሰምቷል፡፡
ፍርድ ቤቱም የምስክር ቃል መርምሮ ከ6ኛ እና ከ7 ኛ ተራ ቁጥር ከተጠቀሱ የፖሊስ አባላት ውጪ ያሉ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።
ሆኖም በክስ መዝገቡ በተራ ቁጥር 6 እና 7 ላይ የተጠቀሱትን በሚመለከት በወቅቱ ታዘው በስራ ላይ ተመድበው እንደነበር ተጠቅሶ ተቋሞቻቸው ማረጋገጫ በማቅረባቸው ምክንያት ነጻ ተብለዋል።
ተከላከሉ የተባሉትን የመከላከያ ማስረጃ ለመጠባበቅም ከሐምሌ 19 ቀን 2016ዓ.ም ጀምሮ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
(ፋና በታሪክ አዱኛ)