ሴናተሩ ኢትዮጵያን ነክሰው የያዙና ፊት ለፊት ገጦ በሚታይ ደረጃ የሚከሱ ነበሩ። ለግብጽ መወገናቸው ብቻ ሳይሆን ትህነግ የመዋጋት አቅሙ ፈራርሶ ሲያጣጥር ” ጦርነቱን ለማስቆም እና ለደረሱ ጥሰቶች ተጠያቂነት እንዲኖር ተጽዕኖ ይፈጥራል የተባለውን ረቂቅ ህግ ሴኔቱ እንዲያሳልፈው እገፋለሁ ብለዋል” በማለት የተኩስ ማቆም እንዲደረግ ሲያስፈራሩ ነበር።
በፍጹም አድሎ ኢትዮጵያን ሲያሳድዱና ሲያጠቁ የነበሩት ሴናተር በሌብነት ተጠርጥረው መከሰሳቸው፣ ቤታቸው ሲበረበር ከፍተኛ ገንዘብና ወርቅ እንዲሁም ቅንጡ መርሰዲስ መገኘቱን ይፋ ተደርጎ “ሙስናው ከግብጽ የተሰጠ ነው” በሚል ክስ እንደሚመሰረት በወቅቱ ተገለጾ ነበር። ቢቢሲ የክስ ሂደቱ በመጨረሻ ጥፋተኛ እንዳደረጋችው ገኦልጾ የሚከተለውን ዘግቧል።
የኒው ጀርዚው ሴናተር ቦብ ሜኔንዴዝ ጉቦ በመቀበል የግብፅ መንግሥትን ጨምሮ የውጪ መንግሥታትን መርዳት በሚሉ የሙስና የወንጀል ክሶች ጥፋተኛ ተባሉ።
በ16 የሙስና ወንጀሎች ጥፋተኛ የተባሉት የቀድሞው የአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀመንበር፤ የቅጣት ውሳኔ ሲተላለፍባቸው በርካታ ዓመታትን በእስር ሊያሳልፉ ይችላሉ።
ዐቃቤ ሕግ፤ ሴናተሩ ከውጭ መንግሥታት ከፍተኛ ጥቅማ ጥቅሞችን መቀበላቸውን ለማሳየት የባለሙያዎች ምስክርነትን፣ የሴናተሩን የኢሜል እና የጽሁፍ መልዕክት ልውውጦችን አቅርቧል።
ሜኔንዴዝ የውጪ መንግሥታትን ፍላጎት ለማስፈጸም ከተቀበሏቸው ስጦታዎች መካከል 100ሺህ ዶላር የሚያወጣ ወርቅ እና ቅንጡ መርሰዲስ መኪና የተጠቀሱ ሲሆን፣ በመኖሪያ ቤታቸውም 480 ሺህ ዶላር ጥሬ ገንዘብ ተገኝቷል።
ሴናተሩ ሙስና ተቀብለው የግብፅ መንግሥት በሚሊዮን ዶላሮች የሚገመት የአሜሪካ መንግሥት ወታደራዊ ድጋፍ እንዲያገኝ ረድተዋል ተብለው ተከሰዋል።
ሴናተሩ ግብፃውያን ከሆኑ የንግድ ባለቤቶች ጋር የጥቅም ትስስር ነበራቸው ተብሏል።
ሴናተሩ በሙስና የወንጀል ክሶቹ ጥፋተኛ መባላቸውን ተከትሎ ዴሞክራቶች ከኮንግረሱ እንዲሰናበቱ እየጠየቋቸው ነው።
ሴናተሩ ግን ጥፋተኛ ከተባሉም በኋላ በሰጡት አስተያየት ሕዝብን በቅንነት ለማገልገል የገባሁትን ቃለ መሃል አላፈርስኩም ብለዋል።
የሴናተሩ ጠበቆች ሜኔንዴዝ የተቀበሏቸው ስጦታቸዎች እንደ ጉቦ መታየት የለባቸውም ሲሉ ተከራክረዋል። ዐቃቤ ሕግ ሴናተሩ ለተቀበሏቸው ስጦታዎች ምላሽ ይሆን ዘንድ የዋሉት ውለታ ስለመኖሩ ማረጋገጫ የለውም ሲሉ ጠበቆች ተከራክረዋል።
በዚህ የሙስና የወንጀል ክስ ትውልዳቸው ሌባኖስ የሆኑት የሴናተሩ ባለቤት ናዲን ሜኔንዴዝ ጭምር ተከሰዋል። ይሁን እንጂ በቅርቡ የካንሰር ቀዶ ሕክምና ያደረጉት ናዲን ከህመማቸው እስኪያገግሙ ድረስ የክስ ሂደታቸው በይደር እንዲቆይ ተደርጓል።
የሴናተር ሜኔንዴዝ ጠበቆች ግን የቀረበውን የሙስና ወንጀል በናዲን ላይ ለማላከክ ሞክረዋል። ጠበቆቹ “የገንዘብ ችግር ያለባት ግለሰብ፤ በተቻላት መንገድ ጥሬ ገንዘብ እና ንብረት ማግኘት የምትሻ ሴት” ነች ሲሉ ገልጸዋቸዋል።