በመላው አገሪቱ በተለያዩ ምክንያቶች የማስተማር ስራቸውን ካቆሙ 5430 ትምህርት ቤቶች መካከል 4,178 ትምህርት ቤቶች የሚገኙት በአማራ ክልል መሆኑ ተሰማ። ከተጠቀሰው አሃዝ ውስጥ ሰማኒያ ዘጠኝ በመቶ የሚሆኑት ትምህርት ቤቶች የተዘጉት ምስራቅና ምዕራብ ጎጃም እንዲሁም ደቡብ ጎንደር መሆኑ ዜናውን አስደንጋጭ አድርጎታል።
በደቡብ ጎንደር 26 ሺህ የሚገመቱ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ የሉም። ተማሪዎቹ ከትምህርት የተለዩት በድርቅና በአካባቢው በተነሳው የሰላም ችግር ሳቢያ መሆኑንን ኦቻ ዩኒሴፍን ጠቅሶ ያቀርበው ሪፖርት ያስረዳል። በክልሉ በጥቅሉ በክልሉ 4.1 ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ተለይተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ከ1.7 ሚሊዮን በላይ ህጻናት በተለይ በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች የትምህርት ቁሳቁስ የሚያስፈልጋቸው እንደሆኑ በሪፖርቱ ተመልክቷል። ከ56,000 በላይ መምህራን እና የትምህርት ሰራተኞች የስነ ልቦናና ማህበራዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልግቸው ሪፖርቱ አመልክቷል። ይህ አስደንጋጭ ዜና አሁን ድረስ መፍትሄ አልተበጀለትም።
በምዕራብ ጎንደር ያለው ሰብአዊ ሁኔታ በአቅምና ተደራሽነት ውስንነት የተነሳ ድጋፉን ውስን እንዳደርገው በሪፖርቱ ተመልክቷል። ከዚህ በተጨማሪ ካለፈው ዓመት ሚያዝያ ጀምሮ የሱዳናውያን ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች መጉረፋቸውን ተከትሎ የውሃ፣ እንዲሁም ጤናን ጨምሮ የህዝብ መሰረታዊ አገልግሎቶች ለማሟላት ከአቅም በላይ መሆኑ ችፍሩን አባብሶታል።
የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና መውሰድ ከሚገባቸው 200 ሺ በላይ ተማሪዎች መካከል 96 ሺህ ብቻ ፈተናውን መውሰዳቸው የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል። እስከ መስከረም ነገሮች ተስተካክለው ተማሪዎቹ ለፈተና እንደሚቀመጡ እንደሚደረግ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ጨምሮ አመልክቷል።
በአማራ ክልል ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ በሚደረግ ማስፈራራት፣ ቦንብ በመወርወርና በተለያዩ ጫናዎች ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ መቸገራቸውን በተለያዩ የውይይት መድረኮች ማስታወቃቸው አይዘነጋም።
4.1 ሚሊዮን ተማሪዎች ትምህርት እንዳይማሩ ተደርገው ሳለ፣ የክልሉ ተወላጅ ያልሆኑ ተማሪዎች በአውቶቡስ ሲጓዙ ተያዙ የሚለው የክስ ዜና ለአማራ አክቲቪስቶች፣ ተከራካሪ ነን የሚሉ ሚዲያዎችና ማህበራዊ መደረኮች የዜናዎች ሁሉ ቁንጮ ሆኖ ሰንብቷል።
በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ታገቱ የተባሉትና አብዛኞቹ ከወለጋ አካባቢ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ተማሪዎች ዝርዝር ባልተነገረ ኦፐሬሽን ከእግት መለቀቃቸውን፣ የቀሩት ከሶስት እስከ ሰድስት የሚሆኑ ተማሪዎች መሆናቸውን የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢያስታውቅም “ሃሰት ነው” በሚል ክርክር የገቡት ሚዲያዎችና የማህበራዊ አውድ እድምተኞች በአማራ ክልል 4.1 ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት እንዲለዩ ተደርገው ቤት መቅረታቸው ዜናቸው አለመሆኑ በርካቶችን አስገርሟል።