“ኢትዮጵያዊያን እንዲሞቱ እንጂ እንዲጠቀሙ ሲጠይቁ ድጋፍ የማያገኙ ከሆነ ለብሄራዊ ጥቅማቸው መከበር ሲሉ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስዱ ሊታወቅ ይገባል” ይህ በተደጋጋሚ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት የሚነገር አሁናዊ ቋንቋ ነው። ኢትዮጵያ ውድ ልጆቿን ለሶማሊያ ሰላምና ደህንነት ሲባል ሰውታለች። በአስር ሺህ የሚቆጠሩ የሶማሌያ ተወላጆችንም በክብር አቅፋ በምድሯ እያኖረች ነው። ዳሩ ግን እያገነች ያለችው ምላሽ እጅግ አሳዝኝ ሆኗል።
በዚህ መነሻ የምስላል ኢትዮጵያ ጦሯን ከሶማሊያ ልታስወጣ እንደምትችል አስጠንቅቃ ለሚመለከታቸው አውራ አገራትና ተቋማት በውስጥ መነጋገሯ ተሰምቷል። ከሶማሌላንድ ጋር የጀመረችው የባህር በር ስምምነት በፍጹም እንደማይቀለበስ በግልጽ አስታውቃ፣ ይህ ብሄራዊ ጥቅሟና ክብሯ የማይከበርላት ከሆነ የጀመረችውን የባህር በር ድርድር ለማጠናቀቅ ይጠቅመኛል የምትለውን ሁሉ እንደምታደርግ አስረግጣ ማስታወቋን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ እያመልከቱ ነው።
ሶማሌያ ብቻ ሳትሆን ኤርትራና ግብጽ አንድ ላይ ሆነው ዘመቻ የከፈቱባት ኢትዮጵያ አሁን ድረስ መንገዷን ሳትቀይር አንካራ ደርሳለች። ከአናክራው ንግግር በሁዋላ ለቀጣይ ንግግር ቀጠሮ ቢያዝም ንግግሩ ዋጋ ቢስ እንደሆነ የሶማሌያ ፕሬዚዳንት ባለፈው ቅዳሜ ገልጸዋል።
ይህን የኢትዮጵያ የጠነከረ አቋም አራክሰው የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች አጀንዳ ወደፊት በማምጣት ትውልድ አገራቸው ላይ ዘመቻ የከፈቱ አሁንም የአንካራው ንግግር ዋጋ ቢስ እንዲሆን ያደረገችው ኢትዮጵያ እንደሆኑ በማጉላት ተጠምደዋል። እነዚህን ወገኖች ኤርሚያስ ለገሰ ” ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፉወርቂ የሚረዳቸው በቅርብ የማውቃቸውና አብረወኝ ይሰሩ የነበሩ ጓደኞቼ ” ሲል በይፋ በራሱ ሚዲያ ግብራቸውን ዘርዝሮ ተቃውሟቸዋል።
የሶማሌያ ባለስልጣናት የኢትዮጵያ ጦር አገራቸውን ለቆ እንዲወጣ ፍላጎት እንዳላቸው መናገራቸውን ተከትሎ ለኢትዮ ሪቪው መረጃ የሰጡና ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ እንዳሉት የሶማሌያ ባለስልጣናት ፉከራ ተራ ጩኸት ነው። ይልቁኑም ማስጠንቀቂያ የሰጠችው ኢትዮጵያ እንደሆነች አመልክተዋል።
“ኢትዮጵያ የቀደመውን ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ በአገር ጥቅም ላይ በመመስረት አካሄድ ተክታለች። በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ ልጆቿ ደማቸውንና ህይወታቸውን እየገበሩ፣ ህግና ስርዓት ጠብቃ ጥቅሟን ለማስከበር ስትንቀሳቀስ እንቅፋት የሚገጥማት ከሆነ የራሷን እርምጃ ትወስዳለች። ማስጠንቀቂያውም የዚያው አካል ነው” ሲሉ መረጃውን የሰጡን ክፍሎች ገልጸዋል።
“ግን” አሉ የመረጃው ስዎች፣ ” ግን ይህ የሚሆነው ለኢትዮጵያ ሰላም ስጋት በማይሆንበት አግባብና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ህይወታቸውን እየታደጋቸው ካሉ የሶማሌሊያ ዜጎች ጋር በሚደረግ መግባባት ነው” ሲሉ የሞቃዲሾው መንግስት ጉዳይ ብዙም አሳሳቢ እንዳልሆነ አመልክተዋል።
በቱርክ አንካራ የተደርገውን ውይይት አስመልክቶ አስተያየት እንዲሰጡ ተጥይቀው ” ከሶማሌላንድ ጋር የተደረገው ስምምነት እንዲሰረዝ የትም ቦታ የሚቀርብ ጥያቄ ኢትዮጵያ አትቀበለውም” ሲሉ ውይይቱ ያለምንም መግባባት መጠናቀቁን አመልክተዋል። ይሁን እንጂ አድሮ ተስፋ ሲቆርጡ አሳባቸውን ከቀየሩ በሚል ቀጣይ ውይይት ለማካሄድ መወሰኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የባህር በር ስምምነት ለመድረስ የመግባቢያ ሰነድ መፈረሟ ይፋ ከሆነ በሁዋላ ወደ ጠሯቸውና ወደ ቀረባቸው አገራት ሁሉ ሲበሩ የነበሩት የሶማሌያ ፕሬዚዳንት አሁን ላይ ሰክነዋል።
ጉዳዩን የሚከታተሉ እንደሚሉት ሶማሌያ የባህር በር ለኢትዮጵያ በአነስተኛ ወጪ አቅርባለች። ይህን ስጦታ ስታቀርብ ከሶማሌላንድ ጋር የተጀመረውን ስምምነት ውሉን በመቀደድ እንድታቋርጥ በመጠየቅ ነው። ኢትዮጵያ ግን ይህ እንደማይሆን ያስታወቀችው “ይህ ቦታ አይሆነኝም። የምፈልገው ከሶማሌላንድ ለመረከብ ሂደት ላይ ያለውም ስፍራ ነው” በማለት ነው።
ዝርዝሩን የሚያውቁ ሲያስረዱ ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ፖለቲካ ስትገለል ይህን ያደረጉት የተገንጣይና አስገንጣይ ድርጅት አመራሮችና ያደራጇቸው ወገኖች በቀጠናው “irrelevant” አገር እንድትሆን አድርገዋታል። ይህን ሆን ተብሎ ኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመ ወንጀል ዛሬ ላይ ባሉ መሪዎች እንዲቀለበስ የተፍለገው ከዚሁ ዕልህና የቁጭት መንፈስ ነው።
ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር በሊዝ ውል ለሃምሳ ዓመታት በሰጥቶ መቀበል ለመውሰድ የጀመረችው እንቅስቃሴ ሲጠናቀቅ የምትረከበውና ጦሯን የማታሰፍረው በቀይ ባህር መግቢያ ላንቃ ላይ ነው። ይህ ወደ ታች እስከ ህንድ ውቂያኖስ ወደ ላይ ሙሉ የቀይ ባህርን መስመር ለመቆጣጠር የሚያስችል ስፍራ ነው። ይህ ባለሙያዎች እጅግ ጥልቅና ስትራቲጂክ እንደሆነ የገለጹት ስፍራ ኢትዮጵያን ዳግም በቀጠናው የምትፈለግ አገር እንደሚያደርጋት ቀጠናው ላይ የተለያዩ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች አመልክተዋል።
ከቀን በፊት በአገሪቱ ምክር ቤት የመክፈቻ ንግግራቸው ላይ መንግሥታቸው ዲፕሎማሲያዊ ውጥረቱን ለማርገብ ፍላጎት ቢኖረውም፤ በአዲስ አበባ ያለው መንግሥት ግን ለውይይት ዝግጁ እንዳልሆነ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ መናገራቸውን ተከትሎ አስተያየት የተጠየቁ ለአዲስ አበባው ተባባሪያችን የገባቸውን ገልጸዋል። እነዚሁ ክፍሎች ” ከሶማሌላንድ ጋር የተጀመረው ስምምነት እንደማይቆም በግልጽ ስለተነገረ ታዲያ ምን ይበሉ?” ሲሉ ጥያቄውን በጥያቄ መልሰዋል።
“የሶማሊያ መንግሥት እኛን ከማናገር፣ በየሰፈሩ እየዞረ እኛን መክሰስ መርጧል። እኛን ለመክሰስ አገር ለአገር መሄድ አያስፈልግም፤ አዲስ አበባ መምጣት ይቻላል። ለመነጋገር ዝግጁ ነን. . . ” በሚል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሰሞኑንን በማፓርላማ ውሏቸው መናገራቸው አይዘነጋም። የሃሰን ሼኽ ምላሽም ለዚሁ ንግግር እንደሆነ በርካቶች እየገለጹ ነው።
ኢትዮጵያ ቁርጥ አቋም ይዛ ከሶማሌያ ልትወጣ እንደምትችል ማስጠንቀቋን ተከትሎ ” እንዳታደርጉት” በሚል አውራ አገራቱ በዝግ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር መነጋገራቸውን ያወሱት የመረጃው ሰዎች ዝርዝር የውይይቱን አሳብ ከማብራራት ተቆጥበዋል።
በአንካራ ድርድር ከሶማሌያ በኩል የባህር በር ስምምነቱ ከነሱ ጋር እንዲደረግና ከሶማሌላንድ ጋር የተደረገው ስምምነት እንዲሰረዝ ጥያቄ ቢቀርብም፣ አምባሳደር ታዬ አቅጸሥላሴ እዛው ውድቅ አድርገውታል።
ሃሰን ሼኽ ቅዳሜ ለምክር ቤታቸው ባደረጉት የመግቢያ ንግግር “የአንካራው ንግግር ሳይጀመር ጨንግፏል” ማለታቸው ከዚሁ የኢትዮጵያ አቋም የተነሳ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል። ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያ ችግሩን በድርድር ለመፍታት እንደማትፈልግ ሲያስታውቁ “እኛ የባህር በር እናመቻች። ውል ከኛ ጋር ፈጽሙ። የሶማሌላንድ ጋር የጀመራችሁትን ውል ቅደቅዱ” የሚለውን አቋማቸውን ኢትዮጵያ እንደማትቀበል መግለጿን ቃል በቃል አልተናገሩም።
የመረጃው ምንጮች ” ከሶማሌ ላንድ ጋር የተጀመርውን የባህር በር ስምምነት ለመሰረዝ ፍልጎት ካላትና ሃሰን ሼኽ የሚያዟት ከሆነ ኢትዮጵያ አንካራ ድረስ መሄድ አይጠበቅባትም። ነገሩ ቅዠት ነው። ኢትዮጵያ እንደቀድሞ በታዛዥነት አትሄድም። በጥቅሟ አትደራደርም። ታንቃ የምትኖርበትም ዘመን በቅርቡ ያከትማል” ብለዋል።
ይህ በንዲህ እንዳለ በቅርቡ ሜኖሶታ የተደረገ መንግስትን በህብረት ለመገልበጥ የተደረገው ጥምረት ውይይት አዘጋጅ ሶማሌያ እንደሆነች መረጃ እየወጣ ነው። መንግስትን የሚቃወሙ ነገር ግን በብሄራዊ ጥቅም የማይደራደሩ በቂ መረጃ እንዳላቸው ጠቅሰው ነው መረጃውን በምስል አስደግፈው ይፋ ያደረጉት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሐሙስ ሰኔ 27/2016 ዓ.ም. ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ ላይ ሰለሶማሌያ ጉዳይ ሲናገሩ፤ ሃሰን ሼክ እዛም እዚህም እንደሚዘሉ ከመግለጻቸው በቀር ስለ ሰላም አስከባሪው የኢትዮጵያ ጦር ያሉት ነገር የለም።
የሶማሊያን ስልሳ ከመቶ የሚሆነውን የቆዳ ስፋት ተቆጣጥሮ እየጠበቀ ያለው የኢትዮጵያ ጦር በፈቃደኛነት ያሰማራውን ተጨማሪ ሃይል ከሶማሊያ እንደሚያስወጣ መግለጹ ስጋት ማስነሳቱ ብቻ ሳይሆን ይህ ሊደረግ እንደማይገባ አውራዎቹ አገራት ማስታወቃቸው ታውቋል። ይሁን እንጂ ዝርዝር ጉዳዩ ግን አልታወቀም።
ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የጀመረችውን እንቅስቃሴ እንደሚቀጥልና ማንም ሊያስቆመው እንደማይችል ደጋግም ስትናገር መቆየቷ ይታወሳል። አሁንም ለንግግር በሯ ክፍት ቢሆንም የአቋም ለውጥ እንደማይኖር ይፋ አድርጋለች። ከሶማሌያ ወገን ንግግሩ ከወዲሁ መክሸፉ ቢገለጽም፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተያዘለት ቀነ ቀጠሮ መሰረት በቱርክ ቀጣዩ ውይይት እንደሚደረግ አመልክቷል። የተፈጠረው አለመግባባት በውይይት ይፈታል የሚል እምነት መያዙንም አመልክቷል። ኢትዮጵያ ይህን ብትልም የሶማሌያ ፕሬዚዳንት ለድጋሚ ቀጠሮ የተያዘው የአንካራውን ውይይት “ይራዘምልኝ” ማለቷን ጠቅሰው ለምክር ቤታቸው አስታውቀዋል።
በቅርቡም ስምምነቱ እንደተሰረዘ በማስመሰል የተለያዩ የሃሰት መረጃዎች በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ስም መረጃ መሰራጨቱ አይዘነጋም። ይህንኑ የሃሰት ዜና ተከትሎ ማስተባበያ መሰጠቱና ሁሉም ጉዳይ በተያዘው ዕቅድ መሰረት እየተሰራ መሆኑን አመልክቷል።
ከቅዳሜው የፕሬዚዳንት ሃሰን ንግግር በመነሳት አስተያየት የሰጡ ” ኢትዮጵያ የፈርመችውን ውል ሳትቀድ ንግግር ብሎ ነገር የለም ሲሉ የነበሩት ሰውዬ ዛሬ ኢትዮጵያ በንግግር መፍትሄ ለመፈለግ ዝግጁ አይደለችም ማለታቸው በዲፕሎማሲው ሽንፈት መጎባጻእፋቸውን የሚያሳይ ነው” ብለዋል።
ኤርትራ፣ ግብጽና ከዛም ካታር ሲመላለሱ የነበሩት ሃሰን ሼህ የወቅቱን ሩጫቸውን “የስኒ ማዕበል” በሚል ያቃለሉ ወገኖች “ዛሬ የስኒው ማዕበልም የለም” ብለዋል። ከፕሬዚዳንት ኢሳያስም ሆነ ግብጽ የሚፈልጉትን ማግኘት ያልቻሉት ሃሰን ሼክ አድሮ ምን እንደሚያሰሙ ባይታወቅም፣ ኢትዮጵያ በአሸናፊነት ስልመውጣቷ ብዙም ጥርጥር እንደሌለ አመልክተዋል።
ወታደር እያሰለጠኑ በሶማሌያ በኩል ሲያፈሱ የነበሩት ኢሳያስ አፉውርቅም አሁን ላይ የማያዋጡ እንደሆነ ከሶማሌያ በኩል መረዳቱ እንዳለ በአውሮፓ የሚኖሩ አክቲቪስቶች እያስታወቁ ነው።