ግብራቸውን በታማኝነት የከፈሉ ግብር ከፋዮች ክብራቸውን የሚመጥን ልዩ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ገለጸ፡፡
የወርቅ ተሸላሚ ግብር ከፋዮች በኢትዮጵያ አየር መንገድ የልዩ አገልግሎት እንዲያገኙ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ዛሬ ውይይት ተካሂዷል፡፡
የወርቅ ተሸላሚ ግብር ከፋዮች በኢትዮጵያ አየር መንገድ የልዩ ቦታ አገልግሎት እንዲያገኙ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ነው ዛሬ ውይይት የተካሄደው፡፡
በውይይቱ የተገኙት የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ ግብራቸውን በታማኝነት እና በወቅቱ ለሚከፍሉ ግብር ከፋዮች ከፍተኛ ክብር እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡
ግብራቸውን በታማኝነት የከፈሉ ግብር ከፋዮች ለሀገራቸው በታመኑት ልክ ክብራቸውን የሚመጥን አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋልም ነው ያሉት፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ አየር መንገዱ ለእነዚህ የሀገር ባለውለታዎች ክብራቸውን የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት ማቀዱ ሊያስመሰግነው እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡ ሌሎች ተቋማትም ይህንን አሠራር ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
በመድረኩ አየር መንገዱ ስለሚሰጠው አገልግሎት ገለጻ ያደረጉት በኢትዮጵያ አየር መንገድ የቢዝነስ እና ልማት ዳይሬክተር ቃኘው ፍሰሃ ግብራቸውን በታማኝነት በመክፈል ለወርቅ ተሸላሚ ግብር ከፋዮች አየር መንገዱ የተለያዩ አገልግሎቶችን አዘጋጅቶ ለመስጠት መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለእነዚህ ግብር ከፋዮች ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች ውስጥ፡-
✍️ከቤት እስከ አየር መንገድ እንዲሁም ከአየር መንገዱ እስከ ቤት ድረስ በምቹ መኪናዎች አገልግሎት መስጠት
✍️ በሌላ አየር መንገድ ትራንዚት ለሚያደርጉ ግብር ከፋዮች እዚያው ተርሚናል ውስጥ ጉዞን የማመቻቸት
✍️ሰልፍ የሌለው አሠራር እንዲሁም ሌሎች በጣም ጊዜ ቆጣቢ አገልግሎቶች መኾናቸውን የጠቀሱት ደግሞ የአየር መንገዱ የቪአይፒ ተርሚናል ቡድን መሪ ምኞት ተስፋየ ናቸው፡፡
አስተያየታቸውን የሰጡት ግብር ከፋዮች በበኩላቸው በአየር መንገዱ ለመስጠት የታሰበው አገልግሎት ለግብር ከፋዩ ክብር የሚሰጥ እና በቀጣይ የግብር ከፋዮችን የሕግ ተገዥነት ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ያሳድጋል ማለታቸውን ከጉምሩክ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
Via ባሕር ዳር: ሐምሌ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ)