በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር መድኃኒት ያቆሙ ከ8 ሺህ 700 በላይ የኤች አይ ቪ ኤድስ ህሙማንን እንደገና መድኃኒት ማስጀመሩን ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡
በክልሉ ለአንድ ዓመት ያክል የዘለቀው የፀጥታ ችግር ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ሰብዓዊ እክሎችን ፈጥሯል፡፡ በርካታ ተቋማት በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን መደበኛ አገልሎትን ለማስቀጠል ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡
በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት መሠረታዊ ክፍተት ከፈጠረባቸው ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት መካከል የክልሉ ጤና ቢሮ አንዱ ነው፡፡ የመድኃኒት አቅርቦት እና ሥርጭትን ጨምሮ የህክምና ቁሳቁስ እጥረት የክልሉ የጤና ቢሮ ፈተና ኾኖ እንደቆየ በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል፡፡
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የቲቪ፣ ስጋ ደዌ እና ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር ዳይሬክተር ገብሬ ንጉሴ በክልሉ የተፈጠረውን የሰላም እጦት ተከትሎ የኤች አይ ቪ ኤድስ እና ቲቢ መከላከል እና መቆጣጠር ሥራው ፈተና ገጥሞት ቆይቷል ብለዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ የፀጥታ ችግሩ የመመርመሪያ መሣሪያዎች እጥረት እንዲያጋጥም፣ ህሙማን ምርመራ እንዳያደርጉ እና መድኃኒት እንዲያቋርጡ ምክንያት ኾኗል፡፡
በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር እና የፀጥታ ችግሩን ተከትሎ በተፈጠሩ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ችግሮች መድኃኒት ያቋረጡ ከ8 ሺህ 700 በላይ የኤች አይ ቪ ኤድስ ህሙማን መገኘታቸውን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
በፀጥታው ችግር ያቆሞቱን እና ቀደም ብለው መድኃኒት አቁመው የነበሩ ከ11 ሺህ በላይ ህሙማን እንደገና መድኃኒቱን እንዲጀምሩ መደረጉንም ነግረውናል፡፡
የጤና ተቋማት በፀጥታ ችግር ውስጥም ኾነው የማኅበረሰቡን የጤና አገልግሎት ለማሳካት ባደረጉት ጥረት 138 የስጋ ደዌ ህሙማንን ወደ ህክምና ማዕከል ማስገባት ተችሏል ብለዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ 30 ሺህ 442 የቲቢ ህሙማንን መርምሮ መድኃኒት ለማስጀመር ታቅዶ ነበር ያሉት ዳይሬክተሩ 64 በመቶ የሚኾኑ ህሙማን ተመርምረው መድኃኒት መውሰድ መጀመራቸውን ነግረውናል፡፡
በችግር ውስጥም ኾኖ በትብብር እና በቅንጅት መሥራት ከተቻለ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ያሉት ዳይሬክተሩ አጋር አካላት፣ ተባባሪ አካላት እና ማኅበረሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ባሕር ዳር: ሐምሌ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ)