የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና ቲቪ ብሪክስ ኢንተርናሽናል ሚዲያ ኔትዎርክ በጋራ መስራት የሚያስችለውን የትብብር መግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
በበይነ መረብ በተደረገው የስምምነት ፊርማ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን በመወከል አምባሳደር ረታ ዓለሙ፣ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኤቭጌኒ ቴርኪሂን እንዲሁም በሩሲያ የኢትዮጵያ ኤምባሲን በመወከል አቶ ግስላ ሻውል ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የብሪክስ ሚዲያ ፎረም የፕሪዚዲየም አባል መሆኑ ይታወቃል።
በዚህም ከብሪክስ አባል ሀገራት አቻ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ጋር በትብብር መስራት የሚያስችለውን ስምምነት ፈጽሞ እየሰራ ይገኛል።
ለአብነትም የብሪክስ ሚዲያ ፎረም ፕሪዚዲየም አባል ከሆኑት ከሩሲያው ስፑትኒክና ከቻይናው ዥንዋ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።
በዛሬው ዕለትም ከቲቪ ብሪክስ ኢንተርናሽናል ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር በጋራ መስራት የሚያስችለውን የትብብር መግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ እና የቲቪ ብሪክስ ኢንተርናሽናል ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጃና ቶልስተኮቫ በበይነ መረብ ፈርመውታል።
በዚሁ ጊዜ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ሕግ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ረታ ዓለሙ፤ የተቋማቱ የትብብር ስምምነት ዓለም አቀፍ መረጃን ለመጋራት መሰረት የሚሆን ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና ቲቪ ብሪክስ ኢንተርናሽናል ሚዲያ ኔትዎርክ የትብብር ስምምነትም መረጃን ለማሳለጥ መሰረት የሚጥል መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ፤ ስምምነቱ ኢትዮጵያ አባል የሆነችበትን የብሪክስ ሚዲያ አባል ሀገራት የጋራ ጥቅሞች በሚያስጠብቅ መንገድ መረጃ ለመለዋወጥና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
ኢዜአ ከሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ስትራቴጂክ ስምምነት በማድረግ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዜና እና ዜና ነክ ዘገባዎችን በማቅረብ ወሳኝ የዜና ምንጭ ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በዚህም ከሩሲያው ስፑትኒክ፣ ከቻይናው ዥንዋ እንዲሁም አሁን ላይ ከቲቪ ብሪክስ ጋር የትብብር ስምምነት በማድረግ ከአፍሪካ ቀዳሚ የዜና ምንጭ ለመሆን ተግቶ እየሰራ የሚገኝ ተቋም መሆኑን አንስተዋል።
ኢዜአ ቀዳሚ ሀገራዊ የመረጃ ምንጭ በመሆኑ ከሩሲያ መገናኛ ብዙኃንና ድርጅቶች እንዲሁም ከብሪክስ አባል ሀገራት የመገናኛ ብዙኃን ጋር በቅርበት ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከቲቪ ብሪክስ ኢንተርናሽናል ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር የተደረሰው ስምምነትም ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ዜና ዜና ነክ መረጃዎችን ለመለዋወጥ ገንቢ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
የቲቪ ብሪክስ ኢንተርናሽናል ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጃና ቶልስተኮቫ፤ ተቋማቱ በአዲስ አበባና ሞስኮ መካከል ያለው ርቀት ሳይገድባቸው ወሳኝ የትብብር ስምምነት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
ስምምነቱም ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በጋራ ተጠቃሚነትና ትብብር ላይ የተመሰረተ ታሪካዊ ወዳጅነታቸውን ማጎልበታቸው በብሪክስ ማዕቀፍ ጎልቶ እየታየ መሆኑን የሚገልጽ ነው ብለዋል።
የቲቪ ብሪክስ ኢንተርናሽናል ሚዲያ ኔትዎርክ በቴሌዥንና ሌሎች 70 የመገናኛ አውታር አማራጮች 20 ሀገራት ጋር በመረጃ ተደራሽነት ላይ በትብብር እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ኢዜአ