የህዝባችንን ኑሮ ለመቀየርና ሠላምን ለማስፈን ሌት ተቀን ያለ እረፍት እየሰሩ የነበሩት ጀግና ታታሪ ወንድማችን ክቡር አቶ አህመድ አሊ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ በከሚሴ ከተማ ከሚገኘው መስጅድ ጁምአ ሶላት ሰግደው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ የሠላም እና የአንድነት ፀር በሆኑ ፅንፈኞች በተተኮሰባቸው ጥይት በ39 ዓመታቸው መስዋዕት ሆነዋል፡፡
አቶ አህመድ አሊ ፅንፈኝነትን አምረው የሚታገሉ፣ በተሰማሩበት ሁሉ የህዝብን ጥቅም የሚያስከብሩ ወንድማማችነትንና አብሮነትን ለማጠናከር ያለ እረፍት የሚሰሩ ታላቅ ሰው ነበሩ፡፡
ፅንፈኝነት መሪዎችን በመግደል የሚያሸንፍ ቢመስልም የበለጠ ትግላችንን መራርና ፈጣን በማድረግ እንደ ብረት የሚያጠነክረን እንጅ ወደ ኋላ የሚመልሰን አይደለም፡፡ ፅንፈኝነት ህዝብን ከህዝብ ለማባላት ያገኘዉን አጋጣሚ ሁሉ ቢጠቀምም በህዝባችን ትግልና አስተውሎት እንዲሁም እንደ ክቡር ወንድማችን አቶ አህመድ አሊ ባሉ ጀግኖች እየተቀበረ የመጨረሻውን የአልሞት ባይ ታጋይነት ተግባሩን ሲወተረተር ይታያል፡፡
ልበ ቅን መሪዎቻችንን ብናጣም የጀመሩትን ትግልና ትልም ከጫፍ ለማድረስ የበለጠ እንደ ብረት ጠንክረን የህዝቦችንን አንድነት እናስቀጥላለን፡፡ ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን በብሔራዊ ገዥ ትርክት ላይ በማፅናት በየትኛዉም ቦታና ጊዜ ፅንፈኝነትን እንቀብረዋለን፡፡
“የወንድማችንን ነፍስ ፈጣሪ ይማርልን!”
ለወንድማችን አቶ አህመድ አሊ ወዳጅ ቤተሰቦችና ለትግል አጋሮቻቸው ሁሉ መፅናናትን እንመኛለን!!
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት
ሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም፣ ባህርዳር