አስመራ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራን የከለከለችበት መግለጫ ከመውጣቱ በፊት አንድ ቁልፍ ቀጣናዊ ሁነት ተከስቶ ነበር። ጉዳዩ በዋናነት ከአሁናዊው የቀይ ባሕርና የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ-ፖለቲካዊ ልውጠቶች ጋር የተያያዘ ነው። በተለይም የአልቡርሃን መንግስት ከኢራን ጋር ተቋርጦ የቆየውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማስቀጠል ቴህራን ከአልቡርሃን ጋር አምባሳደሮቻቸውን መሾማቸው ነው።
በተመሳሳይ(የሰአታት ልዩነት ውስጥ) በፖርት ሱዳን የተገኙት ጠቅላይ ምኒስትር ዓቢይ ከአል ቡርሃን ጋር ቆይታ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
በተከታዮቹ ጥቂት ሰዓታት ውስጥ ሪፖርቱን ይዞ የወጣው የአልጄዚራው የአረቢኛ ዘርፍ በተለዬ እንዳስነበበውም፣ ኤርትራ የእስራኤልን ጦር በተመረጡ ደሴቶቿ ላይ አስፍራለች ሲል ይዘረዝራል።
የአረብኛው አልጄዚራ እንደፃፈው እስራኤል በኤርትራ ዳህላክ ደሴቶች በተለይም ደሴይ፣ ዳሁም እና ሹሚ ደሴቶች -እንዲሁም በባሕር ዳርቻዋ የምፅዋ ከተማ የባህር ኃይል ጦር ሰፈር አላት ሲል ቀደም ባሉ ጊዜያት ያቀረበውን የጥቆማ ዘገባ አዳብሮ ሪፖርቱን አስፍሯል። እስራኤል ከዚህም ባለፈ ኤምባ – ሶይራ ተራራ በተባለው የኤርትራ ክፍል በሚገኝ የምልከታ መሬት ላይ ሌላ ወታደራዊ ጣቢያ ማቋቋሟን የአልጄዚራ ዘገባ ያትታል።
ከዚህ ቀጥሎ ባሉት ሰዓታት ውስጥ ነው፣ ፕሬዝደንት ኢሳያሳ የአል-ቡርሃኑን የሱዳን አምባሳደር ማባረራቸው የተዘገበው። አሻርቅ አል-አውሳት የመረጃውን ሰበር ይዞ በወጣበት በዚህ ሪፖርት አስመራ የሱዳኑ አምባሳደር ካሊድ አባስ በ 72 ሰዓታት ውስጥ ግዛቷን ለቅቆ እንዲወጣ ትዕዛዝ ሰጥታለች።
በሚቀጥሉት ጥቂት ሰዓታት በኋላ መሆኑ ነው፣ የኢሳያስ መንግስት የኢትዮጵያውን አየር መንገድ ከልክየሃለሁ በማለት መግለጫ ያወጣው። [ በነዚህ ክስተቶች መሃል የዬመኑ ሁቲ በእስራኤል እምብርት ቴላቪቭ ላይ የድሮን ጥቃት ማድረሱ፣ በአፃፋውም የእስራኤሎቹ አሜሪካ ሰራሽ F-35 የጦር ጄቶች በዬመን ሁዴይዳ ወደብ ላይ ድብደባ መፈፀማቸውን እዚጋ ልብ ይሏል። ]
ጉዳዩን በጣም ለማሳጠር፣ በምንገኝበት የአፍሪቃ ቀንድ ቀጣና ኢራን በአል-ቡርሃን በኩል ወደ ሱዳን ተከተስታለች። ይህ ለአቡ ዳቢ ትልቅ የማንቂያ ደወል ነው። ይህን ተከትሎ ደግሞ ግብፅ ከሱዳን ሽግግር ፖለቲካዊ ኃይሎች በተለያዩ ጎራዎች የሚገኙ ተወካዮችን ካይሮ ላይ ባሰናዳችው ጉባዔ ላይ አወያይታለች። በትላንትናው ዕለት ደግሞ የኳታር ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን ተቀብሎ ያነጋገረው አል-ቡርሃን ወታደራዊ ክንፋቸው በኳታር ሙሉ ድጋፍ እንደሚደረግለት ልዑካኑ አረጋግጠውልኛል ሲል በቃል አቀባዩ በኩል አስታውቋል።
በነዚህ ሰሞነኛ ሁነቶች ላይ በጉልህ የተስተዋለው ጉዳይ ጋዛ ውስጥ እልፍ ህይወትን የቀጠፈው የእስራኤል አይመርጤ ወታደራዊ ድብደባ እየተጎተተ ወደ አፍሪቃ ቀንድ መድረሱን ነው። እስካሁንም ሚስጥራዊ የሆነው በኤርትራ የእስራኤል ወታደራዊ ጣቢያ ጉዳይ ከአል ቡርሃን እና ከኢራን መወዳጀት ጋር በተፃራሪ ተወድሮ ይቆም ዘንድ ግድ ብሎታል። ከአቡ ዳቢው የቢን ዛይድ መንግስት ጋር ስትራቴጂክ ትብብር ያላቸው ጠ/ሚ ዓብይ አል-ቡርሃን ጋር መገናኛኘታቸው ለአስመራውን አገዛዝ እንቅልፍ የሚነሳ ድርጊት ሊሆን ችሏል።
በቀጣናችነ የቴላቪቭ እና ቴህራን ማዶ ለማድ መፋጠጥ በጂኦ ፖለቲካዊ አሰላለፉ ላይ የሚፈጥሩት ልውጠት ሳይታለም የተፈታ ቢሆንም በዚህ ደረጃ ኢሳያስን ከአልቡርሃን አቀሳስሮ አዲስ አበባን ከፖርት ሱዳን ማቀራረቡ ከግምትም በላይ ሊባል የሚችል ሁነትን ሊከስት ችሏል።
በአጠቃላይም፣ በአፍሪቃ ቀንድ ጓደኛሞችን ፀበኛ ያደረገ፣ በፀብ የሚፈላለጉትን በአጋርነት ጎራ ያሰለፈ ወቅታዊ እውነታ ተከስቷል። የነገሩ እጅግ መወሳሰብ መፃኢው የአሰላለፍ እውነታ አይገመቴ ይሆን ዘንድ ከተገለፀውም በላይ ከባድ የከባድ ከባድ የሚያደርግ ነው።
ወዲ አፎም በፓን አፍሪካዊው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ይፋ ያደረጉት እገዳ ቂም-በቀል ከወለደው ስም ማጥፋት ጋር ተቀሽሮ የቀረበውም በዚሁ ከመካከለኛው ምስራቅ ኢምፖርት በሆነው ሰሞነኛ የአሰላለፍ ለውጥ የተነሳ ነው። ‘በቀጣይስ ምን ይሆናል?’ የሚለው መጠይቅም ሊመልሱት ከባድ ይሆን ዘንድ ከላይ የተጠቃቀሱት የተፃራሪ ሃገራት ፍላጎቶች ወደ ቀጣናችን ዘውውው ብለው መግባታቸው ምላሹን ጊዜ የሚመልሰው እንጂ ሊገምቱት አዳጋች እንዲሆን አድሮጎታል።
እስሌማን ዓባይ