“እጅግ በጣም ልብ ሰባሪ ክስተት” የተባለለት የመሬት መንሸራተት ቀብሮ ያስቀራቸው አደጋውን ለመታደግ በነብስ አድን ስራ የተሰማሩትን ጭምር ነው። ፖሊሶችና ሌሎች ሰብአዊ አገልግሎት ለመስጠት የተረባረቡትን ናዳው አስቀርቷቸዋል።
የመሬት መንሸራተት የደረሰው ጎፋ ዞን ነው። በዚሁ ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ146 በላይ መላቁን የዞኑ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ይፋ አድርጓል።
እንደመረጃው ይህ እስከተዘገበ ድረስ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት ሴቶችና ሕጻናትን ጨምሮ በጥቅሉ ከመቶ አርባ ስድስት በላይ አስከሬኖች ሊገኝ ችሏል። የዞኑ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ፣ የፖለቲካ፣ ሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊና የአስቸኳይ የአደጋ ጊዜ መልሶ ማቋቋሚያ እንዳስታወቀው የሟቾች ቁጥር ከዚህም ሊበልጥ ይችላል።
አደጋው የደረሰው ሌሊቱን በጣለው ዝናብ በሦስት መኖሪያ ቤቶች ላይ የተጫነውን ናዳ ለማንሳት ጥረት እየተደረገ ባለበት ተጨማሪ ደራሽ ናዳ በመከሰቱ መሆኑን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ምስክር ምትኩ ለዶቼ ቬለ ከተናገሩት ለመረዳት ተችሏል።
የመጀመሪያው አደጋ በሦስት ቤተሰቦች ላይ መከሰቱን የገለጹት አቶ ምስክር “እነሱን ለማትረፍ ብሎ የወጣ ሕዝብ” ላይ ሁለተኛው አደጋ ከረፋዱ 4:00 ሰዓት አካባቢ መከሰቱን ገልጸዋል። አቶ ምስክር አደጋው ከደረሰበት ቦታ “ከ30 በላይ አስከሬን” መውጣቱን ለዶይቼ ቬለ ቢናገሩም ቆየት ብሎ የሟቾች ቁጥር በከፍተኛ መጠን አሻቅቧል።
የዞኑ የሠላም እና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳግማዊ ዘሪሁን “ከ55 በላይ አስከሬን መገኘቱን” እንደገለጹ የጎፋ ዞን የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጽህፈት ቤት አስታውቋል። ይሁን እንጂ አሁን ላይ የሟቾቹ ቁጥር ከ146 ልቋል።
ከሟቾቹ መካከል ለህይወት አድን ተግባር ተሰማርተው የነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች እና የወረዳው ፖሊስ አባላት እንደሚገኙበት የጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው የአስክሬን ፍለጋ እና የነፍስ አድን ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረው ነበር።
አደጋውን “እጅግ በጣም ልብ ሰባሪ ክስተት” ያሉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ “በተፈጠረዉ የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት የውድ ወገኖቻችንን ህይወት አጥተናል” ብለዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎችን ከተናደ አፈር ውስጥ ቆፍረው ሲያወጡ እና ወደ ሌላ ቦታ ሲያዘዋውሩ በማኅበራዊ ድረ ገፆች የተሰራጩ ምስሎች አሳይተዋል።