መሮጥ፣ በሩጫ ጀግና መሆን፣መልካም ባህሪና ተወዳጅነት ቢደመሩ የአመራር ጥበበን ሙሉ ክህሎት አያላብሱም፤ አመራር የራሱ የሆነ ዕውቀትና የደረጀ ልምድ ይጠይቃል። ስለዚህ በትምህርትና በእውቀት የማይደገፍ የተፈጥሮ እውቅት ብቻውን የተሳካ መሪ አያደርግም። በለሌላ አነጋገር መሮጥ ጥሩ የሩጫ ፌዴሬሽን አመራር አያደርግም። ነብሳቸውን ይማረውና አቶ መለስ ” ዘበኛም ቢሆን” በሚል ለፓርቲ ታማኝ ከሆነ እንደሚሾሙ በጠራራ ጸሃይ ያለ አንዳች ሃፍረት ነግረውናል። ቆየት ብለው ደግሞ ካድሬዎቻቸው “ዲግሪ አላቸው” እንዲባል ” ከዲግሪ የወፍጮ ተቋማት” በግዢ እንዲታደሉ አደረጓቸው። ለውጡ ሲመጣና የሁሉም ደጅ ሲከፈት “የተማሩ” የተባሉት ሴክተሩ ሁሉ የካድሬ ጉሮኖ መሆኑ ታጋለጠ። መጠነኛ መሻሻል ቢታይም ዛሬም ያው ነው። ከላይ ተፈቅዶ ስለነበር አገሪቱ በፎርጂድ ዲግሪና ዲፕሎማ ተዋጠች።
በአሰግድ ተፈራ July 26, 2021 የተጻፈና ዳግም የታተመበኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ውስጥ ለዓመታት ሲሰራ የነበረው ህገወጥነት ስፍር ቁጥር የለውም። አንዳንዱ ከማሳዘን አልፎ ህሊናን የሚፈትን ነው። የአትሌቶቹን የዕውቀት ደረጃና አቅም ያገናዘበ ክፉ ተግባር ይፈጸም ነበር። ቤቱ በካድሬ፣ ቱባ ባለስልጣናትን ተገን ባደረጉና የተባሉትን በሚፈጽሙ ባሪያዎች የሚመራ ነበር። ዛሬም በመጠኑ ቅርጹ ቢቀየርም በኮታ የተሰገሰጉ የሚያንቦጫርቁት ቤት ነው። መቶ አለቃ ዱቤ ጅሎና ደራርቱ ቱሉ (ጥላ እስከወታችበት ቀን ድረስ)የአትሌት ተወካይ ሆነው አትሌቲክ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ውስጥ በሚወሰነው ውሳኔ ሁሉ ድምጽ እየሰጡ ረዥም ዓመታት ስለሰሩ በቂ ምስክርና ሰነድም ናቸው። ወደ ህሊናቸው የተመለሱ ዕለት እውነቱን ይመሰክራሉ ወይም…
ሲዘረፍ፣ አድልዎ ሲደረግ፣ ያለ አግባብ አትሌቶች ሲንገላቱ፣ ከህግ ውጭ ውድድር ሲከለከሉ፣ ውድድር ሜዳ ከገቡ በሁዋላ በአንድ ስልክ ከውድድር ሜዳ እንዲታደጉ መመሪያ ሲሰጥ ከትራክ ላይ በፖሊስ እንዲባረሩ ሲደረግ የአትሌት ድምጽ የነበሩት ሻለቃ ደራርቱና “የተከበሩ” ዱቤ ጅሎ ያዩ፣ ይሰሙና አብረው ይወስኑ ነበር። ይህ ሃቅ ነው። ይህን ሃቅ ለዓመታት በሪፖርተር ጋዜጣ በተከታታይ ስዘገበው ነበር። በወቅቱ እጅግ ልብ የሚነኩና በከፍተኛ ደረጃ ሊያስጠይቁ የሚችሉ ጥፋቶና ወንጀሎች ቢፈጸሙም ተቆጣጣሪ አካሉ ደንታ አልነበረውምና ቤቱ ከመሻሻል ይልቅ እየጨቀየና እየሸተተ ሄደ። በዚያው መጠን በውስን አትሌቶች ውጤት ተሸፍኖ የኖረው ቤት እድሜ እየቆጠረ ገበናው ይፋ ይሆን ጀመር። ዛሬ የታጨደው ከቀድሞ ሲንከባለል የኖረው ድምር እንጂ ዛሬ እንደሚሰማው ጫጫታ የአንድ ኦሊምፒክ ዘመን ችግር ውጤት አይደለም።
ቀደም ሲል አትሌቶች ላይ ከዘር ልዩነት ጀምሮ ሲፈጸም የነበረው ጸያፍ ድርጊት በመበርከቱ፣ ሰሚና ፍትህ ሰጪ አካል በመጥፋቱ፣ ምርጥ አትሌቶች አገር ጥለው ኮበለሉ። በሸተተ አሰራርና ግልሙትና በተጠናወተው አስተዳደር ሳቢያ የተሰደዱ አትሌቶች ለሌላ አገር ባንዲራ ቆመው አይናችን እያየ ወርቅና ክብር ነጠቁን። ወደፊትም ይነጥቁናል።
በየቀኑ የሚሰማው ግፍና በደል እየባሰ፣ ምሬቱም እየጠነከረ፣ ስደቱም እየበረከተ ሲሄድ ከመጻፍ በተጨማሪ ተደራጅቶ መታገል አስፈላጊ እንደሆነ ከአንዳንድ በሳል አትሌቶች ጋር ስምምነት ደረስን። በዚሁ መሰረት እኔ አስተባባሪ ሆኜ አዲስ የአትሌቶች ማህበር ተቋቋመ። ሃይሌ፣ብረሃኔ፣ ስለሺ፣ ጌጤ፣ አሰፋ መዘገቡ፣ ገዛኸኝ አበራ … ያሉበትና በሃይሌ ገብረ ስላሴ ሰብሳቢነት የሚመራ ማህበር ተመስርቶ ስራ ጀመረ። ከፍትህ ሚኒስቴር እውቅና ተሰጠን። ዜናው መነጋገሪያ ሆነ። አትሌቶች ተደሰቱ። እነ መሰረት ደፋርን ጨምሮ ጥቂት ዱቤ የሰበሰባቸው ካልሆኑ በስተቀር ዜናውን ተቀባበሉት። የስልክ ጥሪውና ምስጋናው ጎረፈ። እነ ዱቤ ጅሎና ከመንግስት ከፍተኛ መሪዎች ጋር ቅርብ የሆኑት ስራ አስፈሳሚዎች ዛቻ አሰሙ። ማህበሩ ስራውን ቀጠለ።
ሃይሌ ከዓለም ሲኒማ ቤቱ ግርጌ ጊዜያዊ ቢሮ ፈቅዶ ስራውን የጀመረው የአትሌቶች ማህበር ለዓለማአቀፉ የአትሌቶች ማህበር ደብዳቤ ላከ። ማህበሩ “እንኳን ደስ አላችሁ” ሲል ወዲያው ምላሽ ሲሰጥ። ይህን ጊዜ እነ ዱቤ ጅሎ ጦር ሰበቁ። ፌዴሬሽኑ አካኪ ዛራፍ ብሎ መግለጫ ሰጠ። አትሌቶችን ሰብስቦ “ከአዲሱ ማህበር ጋር ብትተባበሩ የውጭ ጉዞ አግዳለሁ” ሲል አስጠነቀቀ። አስፈራራ።
አዲሱ ማህበር ማስፈራሪያውን “ወግድ” ብሎ በአራራት ሆቴል ስብሰባ ጠራ። በዚሁ ስብሰባ በርካታ አትሌቶች ተገኝተው አዳራሹን ሞሉት። በደላቸው በየተራ ተናገሩ። ስብሰባ ፍርድ ቤት እስኪመስል በደል እንደ ጉድ ወረደ። አትሌቶቹ በየተራ ሲናገሩት የነበረው በደላቸው በዚያ ደረጃ ሞልቶ ሲፈስ ለአትሌቶች መብት እንዲከራከሩ፣ እንዲሟገቱ ተመርጠው የነበሩት መቶ አለቃ ዱቤ ጅሎ የሚመራው፣ ሻለቃ ደራርቱ ቱሉ ምን ያደርጉ ነበር? ለአትሌቶች መብት እንዲቆም ታስቦ የተቋቋመውና አፍታም ሳይቆይ ራሱን ወደ “ተለጣፊነት” የቀየረው የአትሌቶች ማህበር በድን መሆኑ በታየበት በዚያ ስብሰባ አዲሱ አመራር በቁርጠኛነት ለመስራት ቃል ገባ።
ለማህበሩ መቋቋም የመጨረሻ እርሾ የሆነው የብርሃኔ አደሬ ጉዳይ ነበር። ” የኢትዮጵያ ህዝብ ብራስልስ ለቅሶ ተቀምጫለሁና ድረሱልኝ” ስትል ብርሃኔ አደሬ በእንባ ከብራስልስ ያሰማችው ጩኸት በሪፖርተር እሁድ ጋዜጣ የግንባር ዜና ሆነ። ዜናው እጅግ ልብ የሚነካ በመሆኑ ዕሁድ ቀን አለቃዬ ሳይቀር ስልኩ ፋታ ማጣቱን ገለጸልኝ። ዜናው በቋፍ ላይ ያለውን አትሌት ረበሸ። በወቅቱ ብርሃኔ በመልካም አቋም ላይ ስለነበረችና ከአቴንስ ኦሊምፒክ አሰናብተው በምትኳ ደራርቱን ስላስገቡ ብርሃኔ ብራስልስ ሮጣ ካሸነፈች ደራርቱን ለግፋት ስለሚገደዱ ነበር ይህን አቋም የያዙት።
ብርሃኔ ስለመታገዷ ምንም መረጃ ስለሌላት ድምጿን አጥፍታ ብራስልስ አቀናች። ድምጿን አጥፍታ የሄደችው በውድድሩ ተሳትፋ በማሸነፍ ያለ አግባብ ከአቴንስ ኦሊምፒክ መባረሯ አግባብ ባለመሆኑ ፍትህ ለመጠየቅ ተጨማሪ ማስረጃ ለማግኘት ነበር። ነገር ግን ፌዴሬሽኑ ጉዳዩ ስለገባው ብራስልስ ደርሳ፣ ልብስ አውልቃ፣ አሟሙቃ፣ የመወዳደሪያ ትራክ ውስጥ ከገባች በሁዋላ በስልክ መልዕክት እንደ ሌባ ተጎትታ እንድትወጣ አስደረጋት። የዛኔ ነበር ብርሃኔ በቅጽበት እየለቀሰች ” ብራስልስ ለቅሶ ተቀምጫለሁ። የኢትዮጵያ ህዝብ ለቅሶ ድረሱኝ” ስትል በሪፖርተር በኩል በስልክ ሃዘኗን የገለጸችው። ይህን ተከትሎ ዱቤና ደራርቱ የሚመሩት ተለጣፊ ማህበር ያለው ነገር የለም። ይልቁኑም ደራርቱ የችግሩ ምንጭ ነበረች። ሰዓት ሳይኖራት፣ ወቅታዊ ብቃትም እንደሌላት እያወቀች ብርሃኔ ወጥታ እሷ እንድትገባ አስደርጋለች። ደራርቱ ቢያንስ በዚህ ጉዳይ አደባባይ ወጥታ ይቅርታ አልጠየቀችም።
ሪፖርተርን ተከትሎ ዜናው ዓለም አቀፍ መነጋገሪያ ሆነ። የብርሃኔ ጩኸት ሁሉም በሆዱ ይዞት የነበረውን ብሶት ፈነቀለው። በአራራት ሆቴል ተደርጎ በነበረው ስብሰባ ብሶት የወለደው ጉድ ተዘረገፈ ። ይህ ሁሉ ሲሆን ዱቤ ጅሎና ደራርቱ “የኢትዮጵያ አትሌቶች ተወካይ” ተብለው በፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ እኩል ድምጽ ይዘው ይወስኑ ነበር። እንግዲህ አዲስ ማህበር ለማቋቋም መነሻው ይህና ይህን መሰል በርካታ ችግሮች ነበሩ።
የአቴንስ ኦሊምፒክ ሃፍረታችን

በ2004 የአቴንስ ኦሊምፒክ የሴቶች አስር ሺህ ሜትር ውጤት እንደማይመጣ አስቀድመው በሪፖርተር ማስጠንቀቂያ ለሰጡ አካሎች ዱቤ ብቻ ሳይሆን የውቀቱ የስፖርት ሚኒስትር አቶ መላኩ ጴጥሮስ እብሪት የተሞላበት ምላሽ ሰጥተው ነበር። ሚኒስትሩ ” አብረን ብንሮጥ ብርሃኔንን እኔ እቀዳማታለሁ” በማለት ዕብለት የተሞላው ምልሽ የሰጡት የብርሃኔ አደሬ ከምርጫ መውጣት ፍትሃዊ እንዳልሆነ ተጠይቀው ነው። አቶ መላኩ እጅግ አራክሰውና አናንቀው ፍትሃዊውን ጥያቄ ምናምንቴ ጉዳይ ለማስመሰል ቢሞክሩም ቀኑ ደረሰና ነገሩ ሁሉ እርቃኑ ወጣ።
ደራርቱ ቱሉ ፣ እጅጋየሁ ዲባባና እግረ ቅጭኗ ወርቅነሽ ኪዳኔ ኢትዮጲያን ወክለው በአስር ሺህ ሜትር ተሰለፉ። ውድድር ተጀምሮ እስኪያልቅ በሚባል ደረጃ ወርቅነሽ ዙሩን አክርራ ስትመራ እጅጋየሁና ደራርቱ አአላገዟትም ነበር። ሶስት ዙር አካባቢ ሲቀር ለመውጣት ብትሞክርም ብቻዋን ዙሩን ስታከር ስለነበር አልሆነላትም። ወርቅነሽ ዙሩን አክርራ ሌሎችን በሙሉ ስለቆረጠች ፉክክሩ በአምስት አትሌቶች መካከል ነበር። ደራርቱና እጅጋየሁ የመጨረሻውን ዙር ፍጥነት ጨምረው መሮጥ ባለመቻላቸው እርስ በርስ እየተጠባበቁ ሲሮጡ አንድ አስገራሚ ክስትት ተፈጠረ። ፣ የቻይናዋ አትሌት Xing Huina እየተራመደች ሄዳ ወርቅ ነጠቀች። በዚህ ሃፍረት የተሞላበት ሽንፈት የተጠየቀ፣ የተሞገተ፣ ወይም ስልጣኑንን ያጣ አንድም አካል የለም። አልነበረም። ይልቁኑም በተቃራኒው ሹመት ተሰጥቷል። ብርሃኔ ሳምንት ሳይቆይ በርቀቱ ሌላ ውድድር አድርጋ እየተምዘገዘች በድንቅ ብቃት ስታሸንፍ ታየ። በዚህ ሃፍረት፣ ግፍና በደል የተቀጣጠለውና አዲስ ማህበር ያዋለደው ፍትህ ፈላጊና አዲስ አመራር ተማማሉ። ፌዴሬሽኑ እንዲጠራ፣ ፍትህ እንዲሰፍን ለመታገል አቋም ተያዘ።
የሃይሌ ማፈግፈግ
በአገራችን በመረጃ መሞገትና በአመክንዮ ማሰብ ያልተለመደ በመሆኑ ብዙ ጊዜ ስማቸው የገነኑ ሰዎችን መንካት አግባብ እንዳልሆነ ይታሰባል። እነሱም ይህን ሰለሚያዉቁ ስማቸው በሚነሳበት ጉዳይ ላይ ሳይሆን ባልተባሉት ጉዳይ ማንባትና የተተቹበትን ጉዳይ ትተው ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት በሌለው መንገድ ትችቱን ሳይሆን ተቺውን ለማሳጣት ይመርጣሉ። አንዳንዴም ማልቀስ ሁሉ አለ። ምንም ይባል ምን እውነቱን ከስር እዩት።
ሃይሌ ይህ ማህበር ሲቋቋም መሪ ነበር። ሃላፊነቱን በትልቅ ስሜት ሲረከብ ከትልቅ ሞገስ ጋር ነበር። እንደ አንጋፋ አትሌት ጉዳዩ ስለሚመከተው ማህበሩ ገና ከጅምሩ እጅግ ተስፋ ተጥሎበት ነበር። የማውቃቸው የውጭ ሚዲያ ሰራተኞች ሳይቀሩ መረጃ ሲጠይቁኝ ተስፋዬ ከፍተኛ እንደነበር ስገልጽም ነበር። ስራ አስፈጻሚዎቹ እጅግ ጥልቅ በሆነ ቁጭት ስሜት ነበር የሚሰሩት። ጉጉታቸው አሁን ድረስ ፊቴ ላይ አለ። ሚስቱ እልፍነሽ አለሙ ከማራቶን እንድትወጣ ስትደረግ አትሌት ገዛኸኝ ” ለእልፍነሽ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም አትሌቶች በደል እንቆማለን” ሲል በድፍረት መግባቱን ሳስብ ያ ማህበር በሚል ዛሬ ድረስ ያመኛል።
በዚህ ስሜትና ጉጉት ሩቅ አልሞ፣ ለታላቅ ለውጥ ወገቡን አስሮ የተነሳው የአዲሱ ማህበር አመራሮች ያልጠበቁት ድንገተኛ መርዶ ተሰማ። የፌዴሬሽኑ ባሪያ የሆነው የአትሌቶች ማህበር ሊቀመንበር፣ የቴክኒክ ክፍል ሃላፊ፣ የፌዲሬሽኑ ስራ አስፈጻሚና የአትሌቶች ማናጀር ሆኖ የሚሰራው ዱቤ ጅሎ ” የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ታግዶ ፈቃዱ ይነጠቃል” ሲል መግለጫ ሰጠ። ዜናው በማለዳ ከተማውን ሞላው። የመንግስት ሚዲያዎች ደጋገመው ዜናውን ሄዱበት። መከረኛ የውጭ ጉዞ ስላለ ዜናው ተወቀጠ። ሃይሌ ከዛን ቀን ጀምሮ አዲሱን ማህበር ትቶ ጠፋ። ማህበሩንም አፈረሰው። የሰተውን ጊዜያዊ ቢሮ ዘጋው።
ዱቤ ከመግለጫው ባሻገር ሃይሌን አግኝቶ እንዳናገረው፣ ማህበሩም እንደሚፈርስ በግል ነገረኝ። በፍጹም መተማመን ማህበሩ እንደማይቀጥል አስረግጦ ነገረኝ። ስራ አስፈሳሚዎቹን በግል ለማነጋገር ሞከርኩ ግራ መጋባት እንጂ ይህ ነው የሚባል ምክንያት ማግኘት አልቻሉም። ሁሉም አዘኑ። ሃይሌም “ነብሱ እኔ ጭቅጭቅ አልወድም” ምናምን ብሎ ስቆ አለፈ።
ስለ ታላቁ ሩጫ ሲነሳ ሃይሌ ለምን እንደሚደነብር በግልጽ ባይገባኝም የራሴ ምልከታዎችና “ትርፍ አልባ” ድርጅት ተብሎ በፍትህ ሚኒስቴር ከመመዝገቡ ጋር ተያይዞ “አትራፊ” ድርጅት እንደሆነ የሚናገሩ አሉ። ታላቁ ሩጫ ከውጭ አገር የሚያገኘውን ገቢ በውጭ አገር የሂሳብ አካውንት እንደሚያከማች ፌዴሬሽኑ እንደሚያውቅ ዱቤ ሹክ ብሎኝ ነበር። እዛው ታላቁ ሩጫ ውስጥ ተዋንያን የነበሩም በተመሳሳይ “ጉዳዩ ብዙ ነው” ብለውኛል። ምንም ይሁን ምን ሃይሌ ማህበሩ እንዲፈርስ ያደረገው ታላቁ ሩጫ ስሙ ተነስቶ ዱቤ ማስፈራሪያ ስለሰጠ ነው። ዱቤና ሃይሌም የማይበጠስ ወዳጅነታቸው የተቋጠረው በዚህ አጋብብ እንደሆነ በቅርብ የሚያውቁ ይገልጻሉ።
ከዛ ምን ሆነ?
የስፖርት ቤተሰቡን በመቀራረብና በውጭ ጉዞ ላይ በተመሰረተ ግንኙነት የተሳሳተ መረጃ ሲሰጡት ከነበሩ ሚዲያዎች ጋር ግብግብ የመፍጠር ያህል በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቆሸሸ አሰራር ሪፖርተር ብዙ ሲዘግብ ነበር።በሪፖርተር በግል እኔ ብቻ ሳልሆን መላው የድርጅቱ ሰራተኞች ከትንሽ እስከ ትልቅ አትለቲክስን አስመልክቶ በሚሰሩ ዘገባዎች ተሳትፎ ነበራቸው። ለድል ዜና ዕርዕስ ስነመርጥ እንኳን የነበረው ተሳትፎ የምረሳው አይደለም። ሪፖተር በወቅቱ ስፖርቱ ዙሪያ የከረረ ርዕሰ አንቀጽ እያያዘጋጀ አቅጣጫ ያሳይ ነበር። በስፖርት ዘገባ አቅራቢነት ሪፖርተር ላይ በሰራሁባቸው ዓመታት ለአትሌቲክስ ስፖርት ባበረከትኩት አስተዋጾ፣ ድምጽ አልባ ለሆኑ አትሌቶች ድምጽ በመሆን በሰራሁት ስራ ሁሌም ኩራት ይሰማኛል። ሪፖርተርም እንደ ሚዲያ ክብር ይገባዋል።
በወቅቱ ስለ አትሌቶች አበክሮ ይሟገት የነበረው ሪፖርተር መሰረት ደፋር እንዳትመረጥ ተደርጎ ስለነበር ከባለሙያዎች በተሰባሰብ መረጃ ሙግት አድርጓል። መሰረት ደፋር አቴንስ ሄዳ በ5000 ሜትር መሮጥ እንዳለባት መረጃና ማስረጃ በመያዝ ሶስት ወራት ተከራክረናል። ዶክተር ወልደ መስቀል አቋማቸውን እንዲያርሙ ደጋግመን ወቅሰናል። ጉዳዩን አገራዊ አጀንዳ በማድረግ መሰረት አቴንስ ሄዳ ትራኩ ላይ ተንሳፋ በ5000 ሜትር ወርቅ እንድታገኝ የጸና አቋም በመያዝ በሰራሁት ስራ ወደር የሌለው ደስታ ተሰምቶኛል። ይህን ማስታወስ ለዛሬ ሃሳቤ አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘሁት እንጂ ስለ እራሴ ለመጻፍ ፈልጌ አይደለም። መሰረት ደፋር አገሯን አንግሳ አዲስ አበባ እንደገባች በመኖሪያ ቤቷ ከሪፖርተር ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ ” የወርቅ ሜዳሊያው ለሪፖተር ነው” ማለቷ ብቻ ሳይሆን ነብስ ይማርና አስቀድመው ስህተት ሰርተው የነበሩት ዶክተር ወልደምስቀል በገሃድ ይቅርታ ጠይቀዋል። ዛሬ መሰረት ይህን ረስታው ሊሆን ይችላል ግን እውነት ነው። ፋይል ሆኖ ኖሯል።
ይህንና ይህን መስለ ችግሮች አዝሎ በጥቂት ውጤታማ አትሌቶች ስምና ዝና ሲያዘግም የኖረው አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተወርቶ የማያልቅ፣ ተዝቆ የማይጠራ ሽንፍላ የሆነ ቤት ነው። በተለይም ስለ ዱቤ ጅሎ ሲታሰብ በርካታ ገሃድ የሚታዩ የህግ ጥሰቶች ይስተዋላሉ። በአትሌት ተወካይነት የራ አስፈሳሚ ኮሚቴ አባል፤ የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ በሁዋላም የቴክኒክ ክፍሉ ተቀጣሪ ሃላፊ የሆነበት አግባብ የቤቱን ሽንፍላነት የሚያሳይ ነው። ከዚህ በላይ ደግሞ ይህን ሁሉ ሃላፊነት ተሸክሞ የአትሌቶች ማናጀር ሆኖ ዶናዶኒ ከሚባል ጣሊያናዊ ማናጀር ጋር ይሰራል። አስራ አምስት በመቶ ኮሚሽን ከተወዳዳሪዎች ይሰበስባል። አስቡት ለጉዞ የፈቃድ ሰነድ የሚሰጥ ሰው፣ የቴክኒክ ሃላፊ የሆነ ሰው እንዴት ብሎ ነው ከሰመጠበት የጥቅም ባህር ውስጥ ሆኖ ስለ አገራዊ ውድድርና ፍትሃዊ አስተዳደር የሚያስበው? ይህን ለመታገል የተቋቋመው ማህበር መፍረሱ እንደ ቁስል የሚጠዘጥዘው ለዚህ ነው። ለምን ቢባል አሁንም የአትሌት ተወካዮች ተብለው ከስራ አስፈጻሚ ጋር ልክ እንደ ድሮው የሚሰሩ መኖራቸው ብሶት የወለደው ማህበር በመፍረሱ ነውና።
አቶ ዱቤ እንኳን በሹመት ስፖርቱን ሊመሩ ቀርቶ በወንጀል ሊጠየቁ የሚገባቸው፣ በህግ በሚከለከል ተግባር ተሳትፈው የአትሌቶች ማናጀር በመሆን ከያንዳንዱ አትሌት የአሸናፊነት ክፍያ አስራ አምስት በመቶ ሲዘርፉ የኖሩ ናቸው። አቶ ዱቤ ( ተከበሩ የፓርላማ አባል) የአትሌት ማናጀርነቱን ስራ ሲሰሩ የነበሩት በፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ክፍል ዳይሬክተርነት ወንበር ላይ ተቀምጠው ሲሆን የንግድ አጋራቸው ደግሞ ዶናዶኒ የሚባሉ ጣሊያናዊ ነበሩ።
አብረዋቸው የሚሰሩት ጣሊያናዊው ማናጀር ዶናዶኒ የያዛቸው አትሌቶች ቅድሚያ አበራታች መድሃኒት በመቃም ተጥርጥረው ምርመራ ሲደረግባቸው እንደነበር፣ ለዚህ ሪፖርት አያመችም እንጂ ሌሎችም ከመድሃኒት ጋር የተያያዙ አጉል ድርጊቶች ሲፈጸሙ ዱቤ አያውቁም ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው ። አትሌቶቹ ሲያሸንፉ ለሚገኘው ጥቅም በማሰብ መድሃኒት ማለማመዱ ኢትዮጵያን በማትታወቅበት የዶፒንግ ሊስት ውስጥ አስገብቷት ምን ያህል ፈተና እንዳጋጠመን የመንግስት ሚዲያዎች ሳይቀሩ ሲዘግቡ ነበር።
ዱቤ የብቃታቸውም ጉዳይ ቢሆን እጅግ መነጋገሪያ ነው። ይህንኑ ጉዳይ ማታ ማታ ኮተቤ የሚያስተምሯቸው፣ ቀን ቀን እሳቸው የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው የሚጠርንፏቸውና በረድፍ የውጭ አገር እድል የሚሰጧቸው መምህራን የሚያውቁት ሃቅ በመሆኑ አልፈዋለሁ። ስለዚህ እንደ ዱቤ ጅሎ አይነት ሰው የኢትዮጵያን ስፖርት እንዲመራ የፈቀዱ ሁሉ ሊያፍሩ ይገባል የሚል እምነት አለኝ። በሩጫም ቢሆን ይህ ነው የሚባል ታሪክና ልምድ የሌለው፣ በበረሃ ውድድሮች ለማድመቂያ የሚሳተፍ ከመሆኑ በዘለለ ሌላ ገድልም. ልምድም፣ ዝናም የለውም።
ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን እንዲመራ የተሰየመው ልክ ማህበሩ ሲቋቋም እንደሆነው አትሌቶች ግንባር ፈጥረው ባደረጉት ትግል ነው። አዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገ ስብሰባ ሃይሌ ወደ ፌዴሬሽን አመራር ሲገባ አንድ ሁለት ተብሎ በአደራ የተነገረውና ቅድሚያ ሰጥቶ ሊወጣቸው የሚገባቸው ተግባራት ነበሩት።
ብሄራዊ የአትሌቲክስ ብድን በየኢቨንቱ ወይም ሩጫው ዓይነት እንዲያቋቁም፣ የአሰልጣኖች ምደባን ፍትሃዊ እንዲያደርግ፣ የአትሌቶች ምርጫና የውጭ ጉዞ ላይ ያለውን አሰራር ግልስ አድርጎ ቤቱን ከሮሮ እንዲያጸዳ ታልቅ ሃላፊነት ወስዶ ነበር። ወደ ሃላፊነት በመጣ ሁለት ዓመት ጊዜ በነበረው አሰራር ከመቀጠል ውጭ ይህ ነው የሚባል አዲስ አሰራር ይፋ ያላደረገው ሃይሌ ሱሉልታ በተደረገ አገር አቋራጭ ውድድር ላይ “ፍትህ ለአትሌቶች፣ ሃይሌን አንፈልግም፡ ማናም የሚሉ ትንሻ አትሌቶች ስለተንጫጩ ወንበሩን ለሻለቃ ደራርቱ አስረክቦ ፌዴሬሽኑንን እንደተለየ አስታወቀ። ይህ ውሳኔው ሁለተኛ ጥፋቱ እንደሆነ ይሰማኛል።
ፌዴሬሽኑ ላይ ሽንጡን ገትሮ ለውጥ ያመጣል የተባለው ሃይሌ ጥሎ ሲሄድ የቀጠለው እንደወትሮው ነበርና ለወትሮውም ውጤቱ እየተመናመነ የሄደው አትሌቲክስ ይባስ መሳቂያ እንደሚያደርገን ከወዲሁ እየተነገረ ነው። ለገንዘብ ሲባል በየስራቻው ሳይቀር ለሚደረጉ ውድድሮች የባንዲራን ክብር እየተፈታተኑ ነውና ማን ይድረስ? የሚለው የፍርሃት ጥያቄዬ ነው።
አቶ ቢልልኝ መቆያ የዳርት ፌዴሬሽን ፐሬዚዳንት ናቸው። በተመሳሳይ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጸሃፊ ናቸው። ሻለቃ ደራርቱ ይህ ታውቃለች። ዱቤም ይህን ጠንቅቆ ያውቃል። ታዲያ ሁለቱ የረዥም ጊዜ ወዳጆች እንዴትና ለምን ህግ ሲጣስ ዝም አሉ? ዱቤ በምን ድፍረት ህግ እየተጣሰ መሆኑንን እያወቀ የአቶ ቢሊልኝን ፐሬዚዳንትነት በሚኒስትር ዳኤታ ማዕረጉ ያጸደቀው? አትሌቲክስ ውስጥ እያለ ምን ግንኙነት ስለነበራቸው ነው ህግ እንዳያስከበር ያነቀው? ይህ ሰፊ ማብራሪያ የሚፈልግ ጉዳይ ነው። ሻለቃ ደራርቱም ለዚህ ጉድይ ምላሽ ልትሰጥ ግድ ይላታል። ሃይሌ ቢያንስ ይህን እንኳን አላስተካከለም።
ሰሞኑንን የተፈጸመውን አሳዛኝ ታሪክ ለማንሳት ያለውፈውን እንደማሳያ አነሳሁ እንጂ ጉዳዬ ወዲህ ነው። ለሜቻ ግርማ በዶክተር አያሌው ውሳኔ ከቶኪዮ ኦሊምፒክ መሰናበቱን እንደሰማሁ ግለ ታሪኩን አየሁ። አትሌቱ በዓመት ጊዜ ውስጥ ከአርሲ ተነስቶ ስሙ ዓለም ላይ የገነነ ብቁና ድንቅ አቋም ያለው ሯጭ ነው። የሚሮጠው አስቸጋሪውን የ3000 መሰናክል ውጣ ውረድ ያለበት የሩጫ አይነት ነው።
ሌላ ሰው ለማስገባት አሰልጣኞቹ ወግዱ ተብለው በህክምና ውሳኔ ከዋናው የቶኪዮ ቡድን የተቀነስው ለሜቻ በውሳኔው ንዴት ተንደርድሮ ሞናኮ በመሄድ አዲስ ክብረወሰን አስመዝግቦ ሲያሸንፍ ዶክተር አያሌውን ” አፍረሃል” ብሎ የጠየቀ ሚዲያ አልነበረም። ፌዴሬሽኑን ሲያስጠነቅቁ የነበሩ አሰልጣኖችን አስተያየት የጠየቀ፣ አትሌቱንም ያናገር ስለመኖሩ አልተሰማም። እንደ ስፖርት የበላይ ሃላፊ ዱቤ ጅሎ ” ነገሩ እንዴት ነው?” ማለቱ አልተሰማም። ሻለቃ ደራርቱም ብትሆን ስለያዘችው አቋም ያሳበቀችን ወፏ የለችም።
በዚህ ሁሉ ፍትጊያ ውስጥ አልፎ በአኖካና በኦሊምፒክ ኮሚቴ ትንቅንቅ ለሜቻ ከዋናው የቶኪዮ ልዑክ ዝርዝር ውስጥ መካተቱ ሲሰማ እአቴንስ ኦሊምፒክ ወቅት ራሳችን በራሳችን ላይ ያወጅነው ሃፍረታቸን ታወሰኝ። ዛሬ ይህን ስጽፍ የ800 እና 3000 መሰናክል ተወዳዳሪዎች ቶኪዮ መግባታቸውን ስምቻለሁ። ለሜቻም አለ።ስነልቦናውን የጎዱት ለሜቻ ባይሳካለት ተጠያቂው ማን ይሆን? አስቡበት። ዛሬው ቶኪዮ በገባው ልዑክ ዶክተር አያሌው ግን የሉም። “ለምን ዛሬ አብሬ ከነ ለሜቻ ጋር አልሄድኩም” እያሉ እያለቀሱ ነበር። እንደውም በብስጭት ከአቶ ቢልልኝ ጋር ሆነው ሰልፍ ለማደረጃት እየሰሩ መሆኑ ተሰምቷል። እዛ ላላቹህ የሚዲያ ሰዎች መረጃ ለማቀበል ያህል ነው።
የቶኪዮ ኦሊምፒክ በኮቪድ 19 መጋኛ ምክንያት አገሮች ኮታ አላቸው። የሚገቡ ሲኖሩ የሚለቁ ይኖራሉ። በዚህ ምክንያት የዶክተር አያሌው ተራ በ27 እንደሆነ መረጃው ያሳያል። ከዚህ ውጭ ያለው ሩጫ ሁሉ ትርፉ መላላጥ ነው። ለመስከረሙ መንግስት ምስረታ ያድርሰን ዱቤን ጨመሮ መርካቶች ወደ እርሻና ጥቃቅን ንግዶች ይመለሳሉ እንበልና እንመኝ!!
ይህ የተጻፈው እንደ ነጮቹ አቆጣጠር ጁላይ 16 ቀን 2021 ነው። ዛሬ ደግሜ ያተምኩት የፓሪሱን ውድድር አስመልክቼ በስፋት በስፍራውም ሆኜ የታዘብኩትን፣ ከዛው ያነጋገርኳቸውን፣ ከዓለም ዓቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ያገኘሁትን መረጃ አሰባስቤ በቀጣይ ለምጽፈው ጽሁፍ ግብአት እንዲሆን ነው።
- “ ንስሃ ገብቻለሁ እስካሁን የዋሸሁት ይበቃኛል ፤ ሲያፈገፍጉ የተረሸኑ ታጋዮች አሉ ” አቶ ጌታቸው ረዳየትህነግ ቃል አቀባይ በመሆን ጦርነቱን በፕሮፓጋንዳ ሲያቀጣጥሉት የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ አሁን ላይ የሆነው ሁሉ እረፍት እየነሳቸው ያሉ ይመስላል፡፡ በጦርነቱ… Read more: “ ንስሃ ገብቻለሁ እስካሁን የዋሸሁት ይበቃኛል ፤ ሲያፈገፍጉ የተረሸኑ ታጋዮች አሉ ” አቶ ጌታቸው ረዳ
- ለምህላቸው ከሚኖሩት መካከል – ሰርጉን ጥሎ ነብስ የታደገው ሐኪምሰሞኑን ከሚሰማው የሐኪሞች የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ ጎን ለጎን የተሰማው ዜና ሰፊ አድናቆት እየተቸረው ነው። ዶክተር ብሩክ ወይሻ ሙሽራነቱን አቋርጦ ነብስ… Read more: ለምህላቸው ከሚኖሩት መካከል – ሰርጉን ጥሎ ነብስ የታደገው ሐኪም
- ፕሮፌሰር ክንድያ የደብረፅዮንን ቡድን “ካለፈ ስህተቱ የማይማር ተቸካይ ” አሉት፤ ፋኖ የደቦ አመራር ሰየመበጦርነቱ ወቅት ቁልፍ ሚና የነበራቸው ፕሮፌሰር ክንድያ ገብረህይወት “የደብረፅዮን ቡድን ከተደጋጋሚ ስህተቱ የማይማር ተቸካይ ነው” ሲሉ አጣጣሉት። ፋኖ አስራ ሶስት… Read more: ፕሮፌሰር ክንድያ የደብረፅዮንን ቡድን “ካለፈ ስህተቱ የማይማር ተቸካይ ” አሉት፤ ፋኖ የደቦ አመራር ሰየመ
- The Wars We Still Can StopCameron Hudson (New York TimesMay Opinion Mr. Hudson is a senior fellow in the Africa program at the Center for… Read more: The Wars We Still Can Stop
- ዩናይትድ ለፍጻሜ አለፈ ቶተንሃምን ይገጥማልእየተንገዳግደ የፕሪማየር ሊጉን ዋናጫ ባያነሳም ኤፍ ኤ ካፕን ጨምሮ ሌሎች ዋንጫዎችን መውሰድ የቻለው ማንችስተር ዩናይትድ ለዩሮፕያን ሊግ ፍጻሜ ከቶትንሃም ጋር… Read more: ዩናይትድ ለፍጻሜ አለፈ ቶተንሃምን ይገጥማል