በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አምስት ሚሊዮን የኢትዮጵያ “ኮደሮች” መርሐ ግብርን ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። አምስት ሚሊዮን የኢትዮጵያ ‘ኮደሮች’ መርሐ ግብር ከተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ ጋር በመተባበር የሚተገበር ነው። የሥልጠና መርሐግብሩ ለሦስት ዓመታት የሚተገበር ሲሆን፤ አምስት ሚሊዮን ዜጎች ዘመኑን በዋጀው በዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በአርተፊሻል ኢንተለጀንስና በተያያዥ የዲጂታላይዜሽን ክህሎቶች ተጨባጭ ዕውቀት የሚያገኙበት መሆኑ ተገልጿል።
አምስት ሚሊዮን የኢትዮጵያ ‘ኮደሮች’ መርሐግብር ኢትዮጵያ ለምታደርገው የቴክኖሎጂ ሽግግር ያለው ጠቀሜታ ምንድን ነው?
በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው ወጣቶችን ከማፍራት አንጻር የሚያበረክተው አስተዋፅዖ ምን ይመስላል? በዲጂታል ቴክኖሎጂ አቅምና አጠቃቀም የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ምን ያሳያል፤ ኢትዮጵያስ ምን መማር አለባት? በሚሉት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ላነሳቸው ጥያቄዎች የዘርፉ ምሑራን ምላሽ ሰጥተዋል።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ አብዮት ባዩ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ በአሁኑ ወቅት የዲጂታል ክህሎትና እውቀት ለሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ወሳኝ ነው። በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርና እና በማንኛውም መስክ የሚሠሩ ሥራዎች የዲጂታል ክህሎትን ይፈልጋሉ። የመግባቢያ፣ የመገልገያ እና የማምረቻ መሣሪያዎችም በዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረቱ ናቸው።
በዚህም ማንኛውም ሰው ሥራውን ለማከናወን የዲጂታል ክህሎት ያስፈልገዋል። የዲጂታል እውቀትና ክህሎት በሌለበት ሁኔታ የሀገርን ኢኮኖሚ ሊደግፍ የሚችል የሰው ኃይል ማፍራት ከባድ ነው ሲሉ ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ በዲጂታል ክህሎት ወደኋላ ቀርታለች የሚሉት አብዮት (ዶ/ር)፤ አሁን ላይ አምስት ሚሊዮን ወጣቶችን በዲጂታል ለማሠልጠን እየተደረገ ያለው ጥረት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ ነው። በርከት ያሉ ወጣቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ማሠልጠን ካልተቻለ የሀገሪቱ የዲጂታል ክህሎት ክፍተት እያደገ ስለሚሄድ የአምስት ሚሊዮን ኮደሮች ሥልጠናን ሁሉም ትኩረት በመስጠት ሊጠቀምበት ይገባል ይላሉ።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ ብቻ ሳይሆን ከጎረቤት ሀገራቶችም አንጻር ወደኋላ ቀርታለች ብሎ ያስቀምጣል። ኢትዮጵያን በዲጂታል ክህሎት ከሌሎች ሀገራት ጋር ተወዳዳሪ ለማድረግ በርከት ያሉ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎት ሥልጠና ቀርጾ መተግበር እንደሚገባ ስትራቴጂውን ዋቢ አድርገው ይገልጻሉ።
ለዚህ ደግሞ የአምስት ሚሊዮን ዲጂታል ክህሎት ፕሮግራም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን እውን ለማድረግ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን በመግለጽ፤ በቀጣይም የዲጂታል ክህሎት ያላቸው ዜጎችን ለማፍራትና መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ በአፅንዖት ያስረዳሉ።
የዲጂታል ክህሎት በዋናነት መሠረታዊ የኮምፒውተር እውቀት፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ ሥራ መሥራት መቻልንና መተግበሪያዎችን ማልማትን ያጠቃልላል የሚሉት አብዮት (ዶ/ር)፤ መሠረታዊ የኮምፒውተርን ክህሎትን ሁሉም ሰው ሊያውቀው ይገባል። በዚህም አብዛኛው ሀገራት ዜጎቻቸው መሠረታዊ የኮምፒውተር ክህሎት እንዲኖራቸው እያደረጉ መሆኑን ያመላክታሉ።
ወደሥራ የሚሠማራው የሰው ኃይል ውጤታማ ሥራን ማከናወን የሚችለው ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ሲጠቀም በመሆኑ፤ የዓለም ሀገራት የትምህርት ሥርዓት የዲጂታል ክህሎትን ያካተቱ ናቸው። በዚህም ማንኛውም ሰው በሚያልፍበት የትምህርት ተቋማት በቂ የዲጂታል ክህሎት አግኝቶ እንዲወጣ እያደረጉ ስለመሆኑ ይናገራሉ።
ሀገራት ራሳቸውን ለመጠበቅ፣ ጥቃት ለመከላከል እና ኢኮኖሚያዊ እድገታቸውን ለማፋጠን አዳዲስ መተግበሪያዎችን የሚያለሙ እና በቂ የዲጂታል ክህሎት ያላቸው ዜጎችን ማፍራት ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያ ለዘመናት ስትከተለው የቆየችው የዲጂታል ፖሊሲ፣ መሠረተ ልማት አለመስፋፋቱ እና ኢትዮ ቴሌኮም በገበያ የሚመራ ባለመሆኑ ወደኋላ እንድትቀር ምክንያት መሆኑን በመግለጽ፤ አሁን ላይ ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ ለማድረግ የቴሌኮም ሴክተሩን ለገበያ ክፍት የማድረግ፣ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን ወደገበያ የማስገባት፣ ሥርዓተ ትምህርቱን (ካሪኩለሙ) የመቀየር፣ በመንግሥት አሠራር ዲጂታል አሠራርን አስገዳጅ ማድረግ፣ የዲጂታል ክፍያዎችን በዲጂታል የማድረግ እና ሌሎች በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። በቀጣይም እነዚህን እና ሌሎች ሥራዎችን ትኩረት በመስጠት መተግበር ከተቻለ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ካደጉ ሀገራት ተርታ መሰለፍ ትችላለች ሲሉ ያብራራሉ። ።
የአምስት ሚሊዮን ኮደሮች ሥልጠና መርሐግብር ተጠቃሚዎች መሠረታዊ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎትን ለማግኘት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ሌሎች በርካታ ጥቅሞችን የሚያስገኛቸው በመሆኑ ትኩረት ሰጥተው ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ያሳስባሉ።
ፕሮግራሙን ለማስፈጸም በፌዴራል እና በክልል የሚመራ ኮሚቴ መቋቋሙን ገልጸው፤ ወጣቶች ሥልጠናውን በአግባቡ እንዲወስዱ ድጋፍና ክትትል የማድረግ ሥራ ይሠራሉ ይላሉ። በአምስት ሚሊዮን ኮደሮች መርሐ ግብር ኦላይን የሚሰጡ ትምህርቶችን መከታተል የሚችል ማንኛውም ወጣት መሳተፍ የሚችል ሲሆን እስካሁን ከ92 ሺህ በላይ ወጣቶች ተመዝግበው ሥልጠናውን እየከታተሉ መሆኑን ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ የሚገኙትን በርካታ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድሎች በአግባቡ በመጠቀም ካደጉ ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ በትብብር መሥራት ይገባል ይላሉ።
ኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ካደጉ ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ እያደረገች ያለው ጥረት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ማቋቋሟ፣ አምስት ሚሊዮን ‘ኮደሮች’ ይፋ መሆኑ፣ በፖሊሲ የታገዘ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ስትራቴጂ መፅደቁ እና ሌሎች በርካታ ሥራዎች መሥራታቸው የሚበረታታ መሆኑን ያስረዳሉ።
የግልና የመንግሥት ተቋማት የዲጂታል ዳታ ክምችትን በአግባቡ በማስቀመጥ፣ ልምድና ተሞክሮ በመለዋወጥ፣ አገልግሎት አሰጣጣቸውንና መረጃ አያያዛቸውን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ሀገሪቱ የምታወጣውን የጊዜና የሀብት ብክነት እንደሚገባም ያስረዳሉ።
ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥና መረጃ አያያዝን ዲጂታላይዝድ ማድረግን እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግ በእቅዳቸው ውስጥ በማካተት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ሁሉም ተቋማት ከኋላ ቀር አሠራር በመውጣት በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የሚመለከተው ባለድርሻ አካል በፖሊሲ ሊደግፋቸው ይገባል ሲሉ በአፅንዖት ይናገራሉ።
የዓለም ሀገራት የቴክኖሎጂ ዘርፍን የመወዳደሪያ መስፈርት አድርገው በትኩረት እየሠሩበት ነው የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ግብርና፣ ጤና፣ ፋይናንስ እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎችን ከቴክኖሎጂ ጋር በማዛመድ አገልግሎት አሰጣጣቸውንና መረጃ አያያዘቸውን በማዘመንና በማቀላጠፍ ምርትና አገልግሎታቸውን ማሳደግ ችለዋል ሲሉ አብራርተዋል።
የቴክኖሎጂ አጠቃቀም አቅምን በማሳደግ፣ አሠራርን ለማዘመን፣ ሀብትና ጊዜን ከብክነት ለመታደግና ለሥራ ዕድል ፈጠራ የኮደሮች ሥልጠናው ከፍተኛ ፋይዳ አለው ሲሉ ይገልጻሉ።
አምስት ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የኮደር ሥልጠና በሀገሪቱ ያሉትን ዳታዎች ዲጂታላይዝድ ለማድረግ ከፍተኛ ፋይዳ አለው የሚሉት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የብሔራዊ ኔትዎርክ ማሳለጫ ፕሮጀክት መሪ አቶ ዳንኤል አድኖ ናቸው።
እንደ አቶ ዳንኤል ገለጻ፣ ሀገሪቱ ለቴክኖሎጂ የምታወጣውን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ በሀገር ውስጥ ለማስቀረትና የሥራ ዕድልን ለመፍጠር ይረዳል። በሥልጠናው የሚለሙ መተግበሪያዎችን የሚጠቀሙ ብቻ ሳይሆን መተግበሪያዎችን የሚያለሙ፣ በዲጂታል ክህሎትና እውቀት ያላቸው ዜጎችን ለማፍራት ያስችላል ይላሉ።
በአሁኑ ወቅት በርካታ የዓለም ሀገራት በወረቀት ከሚሠሩ ሥራዎች በመውጣት ዲጂታላይዜሽን እና ሰው ሠራሽ አስተውሎትን እየተገበሩ ይገኛል። ኢትዮጵያም አምስት ሚሊዮን ዜጎቿን ኮዲንግ ካሠለጠነች ዓለም በቴክኖሎጂ የደረሰበት ደረጃ መድረስ ትችላለች ሲሉ ያስረዳሉ።
የአምስት ሚሊዮን የኮደር ሥልጠናው ኢትዮጵያ ለምታደርገው የቴክኖሎጂ ሽግግር ድልድይ መሆኑን በመግለጽ፤ የቴክኖሎጂ ሽግግሩ በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ሲሠራ የበለጠ ውጤታማ ያደርጋል። የኢንዱስትሪ፣ የሚዲያ፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የግብርና እና ሌሎች ተቋማት ከቴክኖሎጂ ጋር ጥብቅ ትስስር ያላቸው በመሆኑ ሀገሪቱ በርካታ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችን ማፍራት ለነገ የማይባል ተግባር መሆኑን ያስረዳሉ።
እንደ አቶ ዳንኤል ገለጻ፣ የሕንድ፣ የቻይና እና የሌሎች ሀገራት ኢኮኖሚ ከቴክኖሎጂ ጋር የተሳሰረ ነው። አንዳንድ ሀገራት በቴክኖሎጂ ከማደጋቸው የተነሳ ከሌሎች ሀገራት ጋር በሚጋጩበት ወቅት የሚያደርሱት የሳይበር ጥቃት ነው ይላሉ።
ሄለን ወንድምነው አዲስ ዘመን ነሐሴ 7/2016 ዓ.ም