በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይፋ ያደረገው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያ ለኢኮኖሚ ዕድገት ከሚያበረክተው አስተዋፅኦ ባሻገር ጥቁር ገበያን ሊያጠፋው እንደሚችል ምሁራን ይገልጻሉ፡፡
ለመሆኑ የጥቁር ገበያ መጥፋትስ ለሀገር ኢኮኖሚ ምን ፋዳ ይኖረዋል?
ትይዩ ገበያዎች በተለይ በማደግ ላይ ባሉ ኢኮኖሚዎች ላይ ሊያሳርፉ የሚችሉትን ተጽዕኖ አስመልክቶ የዓለም ባንክ ባወጣው መረጃ ጥቁር ገበያ ይፋዊ የኢኮኖሚ መረጃን በማዛባት ፖሊሲ አውጪዎች ትክክለኛውን የኢኮኖሚ ሁኔታ ለመገምገም እንዲቸገሩ ያደርጋል ሲል ያትታል፡፡
ከኦፊሴላዊው ሥርዓት ውጪ ከፍተኛ መጠን ያለው የገንዘብ ልውውጥ ሲደረግ የገንዘብ አቅርቦቱን፣ የዋጋ ግሽበትን እና ሌሎች ወሳኝ የኢኮኖሚ አመልካቾችን በትክክል ለመለካት አስቸጋሪ እንደሆነም አመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል ጥቁር ገበያ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን ከመደበኛው እና ታክስ ከሚከፈልበት ኢኮኖሚ በማራቅ የመንግሥትን ገቢ ያዳክማል ይላል፡፡
የውጭ ምንዛሪ ሁኔታን በተመለከተ፣ በሕጋዊ መስመር ሊወጣና ታክስ ሊከፈልበት የሚችል ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ እንደሚገበያይና ይህ የገቢ መጥፋት የመንግሥት እና የሕዝብ አገልግሎቶችን እንዲሁም መሠረተ ልማትን ለመደገፍ እንቅፋት እንደሚፈጥር ይጠቅሳል፡፡
ከዚህም ባሻገር የጥቁር ገበያ ሰው ሠራሽ እጥረትን በመፍጠር እና የዋጋ ንረት በመጨመር የኑሮ ውድነትን ሊያባብስ እንደሚችል መረጃው ይዳስሳል፡፡
ሆኖም ጥብቅ ደንቦችን በማክበር እና የገንዘብ ልውውጥን በመከታተል መንግሥታት ሕገወጥ የገንዘብ ልውውጥን መቆጣጠር እንደሚችሉ ያነሳው መረጃው፤ ይህ በናይጄሪያ በግልጽ መታየቱን ለአብነት ይጠቁማል፡፡
በሀገራቱ የማዕከላዊ ባንክ የጥቁር ገበያ ግብይትን ለመግታት የተወሰደው ርምጃ፣ ከመደበኛው የምንዛሪ ተመን ሥርዓት ማሻሻያ ጋር ተዳምሮ የጥቁር ገበያ እንቅስቃሴን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ ማድረጉን ይጠቅሳል፡፡
የፐብሊክ ፖሊሲና ምጣኔ ሀብት ምሁሩ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋም እንደሚሉት፤ በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይፋ ያደረገው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያው ጥቁር ገበያን የሚያዳክም መሆኑን እና ለዘለቄታውም ሊያጠፋው እንደሚችል ይናገራሉ፡፡
የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓቱ የውጭ ምንዛሪ ተመን በባንኮችና በደንበኞቻቸው መካከል ወደሚወሰንበት የገበያ ሥርዓት መሸጋገሩና ሰዎች ዶላርን ቀጥታ በባንክ የሚመነዝሩበት አግባብ መኖሩ፤ ይህም ከጥቁር ገበያው በተለየ አስተማማኝ መሆኑ ጥቁር ገበያን የሚያዳክም ነው የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፤ ይህ ዳግም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና አለው ሲሉ ነው የሚገልጹት፡፡
እስካሁን ሰዎች ወደ ጥቁር ገበያ የሚሄዱት ባንክ ውስጥ ገንዘብ በማጣታቸው እንደነበር ጠቅሰው፤ የምንዛሬ ሕግ ቢወጣም ባንኮች ብዙ ዶላር መሰብሰብ አልቻሉም ነበር፡፡ አሁን ግን ባንኮች በከፍተኛ ደረጃ ምንዛሪ የሚያሳድጉበት ደረጃ ላይ ናቸው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
ይፋ በተደረገው እና ወደሥራ በገባው ማሻሻያ መሠረት ከዳያስፖራው የሚመጣውን ገንዘብ የትም ባንክ በመሄድ መመንዘር እንደሚቻል በመጥቀስ፤ ባንኮች በቂ ዶላር ሲኖራቸውና የውጭ ምንዛሪ አገልግሎትን በሙሉ አቅም መስጠት ሲጀምሩ ሰዎች ወደ ጥቁር ገበያ አይሄዱም ይላሉ፡፡ በዚህ መንገድም ጥቁር ገበያው ይዳከምና ይጠፋል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
ለዚህም እንደ ኬንያ፣ ዩጋንዳና ታንዛኒያ ያሉ ሀገራት ማሳያ መሆናቸውን አንስተው፤ በእነዚህ ሀገራት ይህ አይነት ፖሊሲ ተግባራዊ በመደረጉ ጥቁር ገበያ የሚባል ነገር አለመኖሩን በማሳያነት ያስቀምጣሉ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎችን ለመክፈት የሥራ ፈቃድ ማመልከቻዎችን መቀበል መጀመሩም ለጥቁር ገበያው መጥፋት ወሳኝ ሚና ካላቸው ጉዳዮች አንዱ እንደሆነ በመጥቀስ፤ በዚህ መልኩ የምንዛሪ ተደራሽነት መስፋት ጥቁር ገበያውን እንደሚያጠፋው ነው የሚናገሩት፡፡
የጥቁር ገበያው መጥፋት፣ መደበኛ ባልሆነው የምንዛሪ ዋጋ ምክንያት የሚፈጠሩ የሰው ሠራሽ የዋጋ ግፊቶች ተወግደው የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር እንደሚያግዝ በመጥቀስ፤ ይበልጥ የተረጋጋ ምንዛሪ ከውጭ ለሚገቡ እቃዎች ዋጋ እንዲቀንስ ሊያደርግ እንደሚችል፤ ይህም ሸማቾችን እና የንግድ ድርጅቶችን እንደሚጠቅም ያነሳሉ፡፡
የኮንትሮባንድ ንግድ የሚስፋፋው በጥቁር ገበያ አማካኝነት በመሆኑ፤ ኢትዮጵያ ገበያ መር ወደሆነው የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት መሸጋገሯ ይበጃታል ሲሉ ይመክራሉ፡፡ ጥቁር ገበያው ሲጠፋ የኮንትሮባንድ ንግዱም በዛው እንደሚዳከም ጠቁመዋል፡፡
በትክክለኛ የቁጥጥር ርምጃዎች በመታገዝ፣ ጥቁር ገበያን በውጤታማነት ማፍረስ እንደምትችል፤ ይህ ሽግግር ኢኮኖሚውን ከማረጋጋት ባለፈም ሥራው ሕጋዊነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የመንግሥትን ገቢ እንደሚያሳድግ፤ በፋይናንሺያል ተቋማት ላይ መተማመንን እንደሚያድስ፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ለዘላቂ የኢኮኖሚ ልማት መሠረት እንደሚጥል እና ወጣቶችንም ወደ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂ እንደሚስብ ነው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ያስገነዘቡት፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ፍቃዱ ድጋፌ በበኩላቸው፤ የትይዩ ገበያ በመደበኛው ገበያዎች ለሚጠየቀው ጥያቄ በቂ ምላሽ ሳይሰጡ ሲቀር የሚፈጠር እንደሆነ ያስገነዝባሉ፡፡
በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ትይዩ ገበያ የተፈጠረው በዚህ የተነሳ መሆኑን በመጠቆም፤ በተለይ መደበኛ ገበያው ከማሻሻያው በፊት የነበረው በገበያ ተመን ሳይሆን በውሳኔ በመሆኑ በትይዩ ገበያው ውስጥ ብልጫ መወሰዱን ያብራራሉ፡፡
በማሻሻያው መሠረት አቅርቦትን ያገናዘብ የዋጋ ተመን ሲደረግ ከትይዩ ገበያ ጋር የመቀራረብ እድል እንደሚፈጥር ጠቅሰው፤ ይህም የጥቁር ገበያውን ዋጋ እያሳነሰ እንደሚመጣ ተናግረዋል፡፡
የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች መከፈትም ጥቁር ገበያውን እንደሚያዳክመው እና ይህም ዘላቂነት ላለው የኢኮኖሚ ግንባታ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን የአዲስ ዘመን ዘገባብ ያስረዳል።