ኢትዮጵያ በዚህ አመት በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ 1 ነጥብ 43 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ፤ ይህ ገቢ ካለፉት አመታት ሁሉ የተሻለ መሆኑን በማመላከት፤ በተጠናቀቀው በጀት አመት ቡና ኢትዮጵያ ወደ ዉጭ ገበያ ከላከቻቸው ምርቶች ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ገልጸዋል።
ይህ መሆኑ አሁንም ቡና ምን ያህል ለሀገሪቷ ገቢ አስፈላጊ ምርት እንደሆነ የሚያሳይ ነው ብለዋል። የዘንድሮ ምርት በአይነትም ሆነ በቁጥር ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረውም ማስታወቃቸውን ሚኒስትሩን ጠቅሶ አዲስ ሪፖርተር አመልክቷል።
በትናንትናው እለት የአፍሪካ ህብረት ቡናን በአህጉሩ ስትራቴጂክ ምርት አድርጎ መመዝገቡን እና በነፃ የንግድ ቀጠናውም ለግብይት የሚቀርብ የመጀመሪያው ምርት መሆኑንም ይፋ አድርጓል።
በአህጉሪቱ ቡና አምራች ሃገራት ምርቱን እሴት ጨምረው ለገቢያ ባለማቅረባቸው እ.ኤ.አ በ2023 በዓለም ላይ ምርቱ ከተገበያየበት 495 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ አፍሪካ ያገኘችሁ ድርሻ ከ1 በመቶ በታች መሆኑን ያመላከቱት ሚንስትሩ፤በቀጣይ ይህንኑ ችግር ለመቅረፍ ምርቱ ለአህጉሪቱ ነጻ የንግድ ቀጠና መመረጡ እጅግ አስፈላጊ መሆኑም አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣይ ጊዜያት ከተጠናቀቀው በጀት አመት የተሻለ ስራዎችን በመስራት ምርቶቿን በነፃ የንግድ ቀጠናው ላይ በስፋት ለማቅረብ እንደምትሰራ ተመላክቷል፡፡