በሽተኞች፣ አውሬዎች፣ በቀሪው ዘመናቸው ለአገርና ማህበረሰብ ጠንቅ የሚሆኑ አረመኔዎች፣ የህጻናትን ነብስ የሚበሉ ደም መጣጮች፣ የማንዝራ መንፈስ የሰፈረባቸው የሳጥናዔል ሽንቶች፣ መርገምት የመርገምት ዘሮች … ለወንጀላቸው መስፈሪያ የማይገኝላቸው እንዴት እየተመዘኑ ፍርድ እንደሚሰጥ ህዝብ ሊገባው አልቻለም።
በተከታታይ እርጥብ ህጻናትን ጾታ ሳይመርጡ የሚደፍሩ አውሬዎች ዜና ሲቀርብ ከወንጀሉ ጋር የማይጣጣም፣ ለሌሎች አውሬዎች ትምህር የማይሰጥ የቅጣት ውሳኔ ሲተላለፍ ይሰማል። ለአብነት ቲክቫህ ከዘገባቸው የቅርብ ወራት ወንጀሎች መካከል የሚከተሉትን ወስደናል።
- ” የ11 ዓመቷን ልጅ የደፈረው አባት 16 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት ተቀጣ። “
- ” አንገቷን አንቆና አፏ ውስጥ ጨርቅ ጠቅጥቆ የ14 ዓመቷን ልጅ የደፈረው እና ሕይወቷ እንዲያልፍ ያደረገው ግለሰብ በ19 ዓመት ተቀጣ። “
- ” የ5 ዓመቷን ህፃን የደፈረው የ17 ዓመት ወጣት በ6 ወር እስር ተቀጣ። “
- ” የ10 አመቷን ህፃን ልጅ አስገድዶ የደፈረው ግለሰብ በ14 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጣ። “
- ” የ4 አመቷን ህጻን አስገድዶ የደፈረው ግለሰብ በ17 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ። “
- ” የ8 አመት ህፃናትን አስገድዶ የደፈረው የ41 አመት ጎልማሳ በ10 አመት ፅኑ እስራት ተቀጣ። “
- ” እጅግ አረመኔያዊ በሆነ ሁኔታ ሁለት የ16 እና የ17 ዓመት ልጆቹን በአልኮል አደንዝዞ አስገድዶ የደፈረው አባት በ21 አመት ተቀጣ። “
ይህን ግራ የሚያጋባ የፍርድ ውሳኔ ማስታወስ የተፈልገው በአሰቃቂ ሁኔታ ተደፍራ የተገደለችው የሰባት ዓመቷ ህጻን ሔቨን ታሪክ የበርካቶችን ልብ የሰበረ ጉዳይ ሆኗል።
ይህ ድርጊት የተፈጸመው ከዛሬ አንድ ዓመት በፊት በባህርዳር ከተማ ሲሆን፣ እናት ዛሬም ድረስ መሪር ሀዘን ውስጥ ናት። እናት ” ኢዮሃ ” በተሰኘ የማህበራዊ ሚዲያ ላይ ቀርባ እንዳለችው ህጻን ሔቨን የተደፈረችው ተከራይተው ይኖሩበት በነበረ ግቢ አከራይ ነው። የተደፈራትም ህጻኗ ወደ ሽንት ቤት ስትሄድ ጠብቆ ወደ ቤቱ በማስገባት ነው። ድርጊቱን የፈጸመበት አግባብ ደግሞ እጅግ በጣም አሰቃቂ ነበር።
ህጻን ፌቨንን የደፈረው ወንጀለኛ ሴጣናዊ ድርጊቱን ሲፈጽም አንገቷን አንቆ ፤ አፏን አፍኖ ነው። ለሰባት ዓመት ጨቅላ ሙሉ ሃይል ተጠቅሞ ድርጊቱን የፈጸመው ግፈኛ አውሬነት የተላበሰውን ወነጀሉን ከፈጸመ በሁዋላ ወድቃ የሞተች ለማስመሰል ደሟን አንጠባጥቦ በር ላይ ጥሏት መሄዱን እናት እያነባች ታስረዳለች።
እናት ልጇን ብቻ አይደለም ያጣችው ፤ እናት ፍትህ ስትጠይቅ ለፍትህና ለርትዕ ከመቆም ይልቅ ይህንን ግፍ ሰምተው እንዳልሰማ የሆኑ ጎረቤት እና ቤተሰቦች መንቀሳቀሳቸው ልቧን ሰብሮታል። በጥቅም ወንጀለኛውን ነጻ ለማስወጣት መሮጣቸው ሃዘኗን ድርብ አድርጎታል። እናትን ጭምር ተባብረው ወንጀለኛውን ለማስጠፋት ረጅም ርቀት ተጉዘዋል። ማስፈራሪያ ደርሷቸው ቃላቸውን ከመስጠት የጠፉ ሁሉ ለእናት ፈተና ሆነውባታል።
ይህም ሆኖ ጥቂት የሚባሉ (የሴቶች እና ህጻናት ወንጀል መሪማሪ ፖሊሷ፤ የሴቶችና ህጻናት ቢሮ) አንዳንዶቹ ማስፈራሪያ ጭምር እየደረሳቸው አግዘዋት ከብዙ መከራ በኋላ ድርጊቱን የፈጸመው ግለሰብ ሃያ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት ተፈርዶበታል። ይህም ቢሆን ግን እናት ዛሬም ትኩስ ሀዘን ላይ ነች። ሃዘን እየጠበሳት መኖሯ አንሶ ሥራ እየሰራች መኖር አልቻለችም።
ወንጀለኛው ነገ ከእስር ሲለቀቅ እሷንም ጭምር ለመግደል እንደሚፈልግ ፤ ለዚህም ደግሞ ዳግም ሥራ ከጀመረችበት ቦታ ቤተሰቦቹ ተከታትለዋት ስላስቸገሯት ስራዋን ጥላ ለመውጣት መገደዷን እናት አመክታለች። ልጇን የተነጠቀችው ሳያንስ ዛሬም እውነተኛ ፍትሕ አጥታ ትንከራተታለች። ትባትታለች። በግፍ ላይ ግፍ ይሏል ይህ ነው።
ክፉና ደግ ባለለየች አንድ ፍሬ ሃጻንን በአሰቃቂ ሁኔታ የደፈረ አውሬ፣ አውሬነቱን ለመሸፈን በወንጀል ላይ ወነጀል ደርቦ ህይወቷን የበላ ደም መጣጭ እንዴት 25 ዓመት ብቻ ይፈረድበታል? የተመጣጣኝ ፍትህ ጥያቄው ቢዘነጋ እንኳ ይህ አውሬ ተመልሶ ማህበረሰቡ ውስጥ ሲቀላቀል ምን አልባትም የፍርድ ሰጪ አካላቱን ቤተሰብ ልጆች ዳግም እንደማይበላቸው እርግጠኞች ናቸው? ይህ ፍርዱን ተከትሎ የሚሰማ የህዝብ አቤቱታ ነው። የሔቨን ታሪክ የብዙ ህጻናት ታሪክ ጭምር መሆኑን በማስታወስ “የፍትህ ያለህ” የሚሉ ወገኖች ጩኸት በርክቷል። በተደጋጋሚ እንደታየው ሴቶችን፣ ህጻናት ጭምር በሚቀጥፉ ወነጀለኞች ላይ የሚተላለፈው የፍርድ ውሳኔ ህዝብ የሚያስቆጣ ነው። አሁን ብሶበታል።
ዛሬም በምክንያት የፍትህ ያለህ ሲባል፣ ፍትህ ከነጭራሹ ያላገኙ፣ ጭራሹኑ ፍትህ ዘንድ መድረስ ያልቻሉ፣ በነብስም በአካልም የከሰሙትን ማሰብ እጅግ ይጨንቃል። ያሳዝናል።
ሃያ አምስት ዓመት የፍርድ ውሳኔ ተወስኖበት በእስርቤት የሚገኘውን ወንጀለኛ በይግባኝ ለማስፈታት እየተሞከረ ነው። ከዚሁም ጎን ለጎን የሟችን ህፃን እናት የወንጀለኛው ወዳጆች የተባሉ አላስወጣ አላስገባ ብለው እያሰቃዩዋት ነው። በአሁኑ ሰዓት ጠበቆች በነፃ እንዲለቀቅ ከላይ ታች ማለታቸው ብቻ ሳይሆን የእናትና የሟች ታናሽ እህት እጣ ፈንታ አሳሳቢ ሆኗል።
በህፃን ሄቨን ላይ በተፈፀመው ወንጀል በተሰጠው ውሳኔ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰራ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቋል።
ይህ በንዲህ እንዳለ የህዝብንና የእናትን ጩኸት ተከትሎ በህፃን ሄቨን ላይ በተፈፀመው ዘግናኝ የሆነ ኢ ሰብአዊ ወንጀል የተሰጠው ዉሳኔ አስመልክቶ ይግባኝ ለመጠየቅ የሚኬድበት አግባብ ባለመሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰራ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የህፃናትን መብት በማስጠበቅ ረገድ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የተለያዩ ተግባራትን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በህፃናት መብት ጥበቃ ላይ በተለየ መልኩ የፖሊሲ አቅጣጫዎች እንዲቀመጡና የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት የሚፈፀሙ ጥቃቶች የሚመዘገቡበትና ተገቢ የሆነ ሁሉን አቀፍ አገልግሎት እንዲያገኙ የህፃናት የመረጃ አያያዝ ሰርዓት እንዲዘረጋ እና የቅንጅት ስራዎች እንዲጠናከሩ እየተደረገ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለችውን ህፃን ሄቨን በተመለከተም በደረሰው ዘግናኝ የሆነ ኢ-ሰብአዊ ወንጀል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተሰማውን ሀዘን ገልፆ ይህንን አይነት የህፃናት ጥቃት ሚኒስቴር መስሪያቤቱ በፅኑ እንደሚያወግዝ አስታውቋል፡፡
በተፈፀመው ወንጀል ዙሪያም የተሰጠውን ዉሳኔ አስመልክቶ ይግባኝ ለመጠየቅ የሚኬድበት አግባብ ባለመሆኑ ከፍትህ አካላት እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሚሰራ እና እንደሚከታተል አረጋግጧል፡፡
በተመሳሳይ ዜና በሕፃን ሔቨን ጉዳይ የተጀመረው የሚዲያ ዘመቻ እንዲቆም የአማራ ክልል ዳኞች ማህበር ጠየቀ፡፡
ከሰሞኑ የአማራ ክልል መዲና በሆነችው ባህር ዳር ከተማ የሰባት ዓመት እድሜ ያላት ህጻን ሔቨን የአስገድዶ መደፈር ወንጀል ከተፈጸመባት በኋላ ህይወቷ እንዳለፈ የህጻኗ እናት ለተለያዩ ሚዲያዎች ተናግራለች፡፡
በርካቶችን ያስቆጣው ይህ ድርጊት ወንጀሉን ፈጽሟል የተባለው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውሎ በተፋጠነ ምርመራ ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ የ25 ዓመት እስር እንደተላለፈበትም ተገልጿል፡፡
ይህን ተከትሎ ጥፋተኛ የተባለው ግለሰብ ላይ የተላለፈበት ውሳኔ በቂ ካለመሆኑ በላይ ግለሰቡ ፍርዱ እንዲቀነስለት ይግባኝ ማለቱም ተነስቷል፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት ሐምሌ 25 ቀን 2015 ዓ.ም እንደተፈጸመ የተገለጸው ይህ ወንጀል ጉዳዩ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ከፍተኛ ትኩረት የሳበ ሲሆን ተቋማት ሳይቀር በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫዎችን በማውጣት ላይ ናቸው፡፡
የአማራ ክልል ዳኞች ማህበር በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው በሕፃን ሔቨን ላይ በተፈጸመው ዘግናኝ ወንጀል ማዘኑን ገልጾ ድርጊቱም ከሃይማኖትና ከባሕል ያፈነገጠ በመሆኑ በጥብቅ አወግዛለሁ ብሏል።
ይሁንና በኢትዮጵያ ወንጀል እና ወንጀለኛ የሚዳኝበት ሕግና ስርዓት እያለ እና ጉዳዩም በዳኝነት አካሉ በይግባኝ እየታየ ባለበት ሁኔታ የዳኝነት ነጻነት እና የሕግ የበላይነት መርህን የሚጥስ የሚዲያ ዘመቻ መደረጉ ስህተት መሆኑን አስታውቋል፡፡