በጄኔራል መሃመድ ሃምዳን ደጋሎ ወይም ሂመቲ የሚመራው የሱዳኑ RSF ፈጥኖ ደራሽ ሃይል አል ፋው በተባለ አካባቢ ማረኩዋቸው ያላቸውን በመቶዎች የሚቆጠሩ የትህነግ ታጣቂዎችን የሚያሳይ በቪዲዮ የተደገፈ መረጃ ይፋ አድርጓል።
አብዛኛውን ሱዳንን እየተቆጣጠረ ያለው ይህ ሃይል በTG ገፁ ላይ ይፋ ያደረገውን የቪዲዮ ማስረጃ አስመልክቶ ትህነግም ሆነ የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ለጊዜው የሰጡት አስተያየት የለም።
በጄኔራል መሃመድ ሃምዳን ደጋሎ ወይም ሂመቲ የሚመራውን የፈጥኖ ደራሽ ጦር ክንዳቸውን በአንድ አስተባብረው ከሱዳን ወታደራዊ ሃይል /SUDANESE ARMED FORCES SAF/ ጀኔራል አልቡርሃ ጋር በማበር እየወጉት ያሉትን ጀሃዲስት፣ ቅጥረኞች፣ አሸባሪዎች ወዘተ በማለት እንደሚፈርጃቸው በድረ ገጹ ማስታወቁ ይታውሳል።
ጀነራል ደጋሎ የሚመሩት ይህ ሃይል የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር / ትህነግን ከነዚህ ሃይሎች አንዱ አድርጎ በመፈረጃ ከሱዳን ወታደራዊ ሃይል /SUDANESE ARMED FORCES SAF/ ጀኔራል አልቡርሃ ጋር አብረው እየወጉት እንደሆነ “በቂ መረጃና ማስረጃ” አለኝ ሲል መግለጫ ማውጣቱ የሚታወስ ነው።
በግንቦት 4 ቀን 2024 የወጣው የሃምዳን ዳጋሎ መግለጫ በቀጥታ ትህነግን ወይም ወያኔን የሚመለከት ቢሆንም መግለጫውን ” ፍጹም ሀሰተኛ ነው ” ሲል የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አስተባብሎት ነበር።
ተመድ በበኩሉ የስደተኛ መታወቂያ የያዙ የትህነግ ተዋጊዎች መያዛቸውን ጠቅሶ እያጣራ መሆኑን አመልክቶ ነበር። “የስደተኞች መታወቂያን ይዘው ተገኝተዋል” የተባሉ ታጣቂዎችን ጉዳይ እያጣራ እንደሆነ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የስደተኞች ጉዳይ ኤጀንሲ ያስታወቀው “በሱዳን የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የነበሩና የተመድ ስደተኞች ኤጀንሲ መታወቂያ የያዙ ታጣቂዎች ተገኙ” የሚሉ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲዘዋወሩና በተለያዩ የሚድያ አውታሮች መዘገቡን ተከትሎ ስለ ጉዳዩ በአል ዐይን አማርኛ ጥያቄ ቀርቦለት በላከው የኢ-ሜይል መስልስ ነበር።
በዛው ሰሞን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር በሱዳን አቅጣጫ መጥተው “ሽንፋ የተባለ ቦታን ለመያዝ የተንቀሳቀሱ የቅማንትና ትህነግ ታጣቂዎች መደምሰሳቸውን” ገልጸው በትዊተር ገጻቸው ማጋራታቸው የሚታወስ ነው።
“ሳምሪ” በሚል ቅጽል ስም የሚታወቀው የትህነግ አደረጃጀት ወደ ሱዳን ሸሽቶ ከገባ በሁዋላ በስደተኞች ስም ስልጠና እየወሰደ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ቢገለጽም፣ ጉዳዩ በትህነግ በኩል ውድቅ ሲደረግ ቆይቷል። በቅርቡ ከመንገውስት ጋር በተደረገ ውይይት በሱዳን የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ህይወት አደጋ ላይ መሆኑ ተጠቅሶ መንግስት እንዲታደጋቸው ጥያቄ በአቶ ጌታቸው አማካይነት መቅረቡ ይታወሳል።
ዳዊት ከበደ በፌስ ቡክ ገጹ አቶ ጌታቸው በኤምሬትስ በጄኔራል መሃመድ ሃምዳን ደጋሎ የሚመራውን የፈጥኖ ደራሽ ጦር ሰዎች ጋር መገናኘታቸውን ገልጾ፣ ከተገናኙም በሁዋላ በውይይታቸው ” ከአልቡርሃን ጦር ጋር በመሆን የRSF – የጋማሎን ሃይል የሚወጉት የእኛ ሃይሎች ናቸው” ሲሉ መናገራቸውን ጽፎ ነበር። ዛሬ ላይ አሰላለፉ ከእነ ዶክተር ደብረጽዮን ጋር መሆኑን ይፋ ያደረገው ዳዊት ከበደ ይህ ያለው ሆን ብሎ አቶ ጌታቸውን ለማስተላት ይሁን ለሌላ ዓላማ ስለመሆኑ አይታወቅም። እንዲህ ያለ መረጃ ” ዛሬ የአህዮች ቀን ነው” በሚል ጽሁፉ ሲያወጣ የድምጽም ሆነ የጽሁፍ መረጃ አላቀረበም።
አቶ ጌታቸው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች ያወጡትን ክስና ማስጠንቀቂያ “ትህነግ የፖለቲካ ፓርቲ እንጂ አንድም ሰራዊት የለውም” በሚል በወቅቱ ማስተባበላቸው አይዘነጋም።
ይሁን እንጂ የሱዳኑ RSF ፈጥኖ ደራሽ ሃይል በቪዲዮ አስደግፎ ባሰራጨው ዜና በመቶ የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች የወታደር መለያ ለብሰው በምርኮ መያዝቸውን አሳይቷል።
ጉዳዩን አስመልክቶ የትህነግ አቋም ወይም ምላሽ ይህ እስከታተመ ድረስ አልታወቀም። በታጣቂዎች ስም ኢትዮጵያዊ ተፈናቃዮችና ሱዳን የሚኖሩ ሰማዊ ዜጎች ጥቃት እንዳይደርስባቸው ዜናውን የሰሙ ሰግተዋል።