ሃብታሟ አገር ዩናይትድ ኢምራትስ ከፈረንሳይ 80 የጦር ጀቶችን መግዛት የሚያስችል ስምምነት አስራ እንደነበር ያስታወሱ ሚዲያዎች የዚህን ውል መቋረጥ የዘገቡት በሰበርም ጭምር ነው።
ይህ ከበድ ያለ የኢምሬት ውሳኔ የተሰማው ፈረንሳይ ሰሞኑን የቴሌግራሙን መስራችና ባለቤት የሆነውን ትውልደ ሩሲያውን ፓቨል ዱሮቭን ማሰሯን ተከትሎ ነው። ምንም እንኳን የቴሌግራም መስራችና ዋናው ስራ አስኪያጅ ፓቨል ዱሮቭ ፍርድ ቤት ቀርቦ በ5 ሚሊዮን ዩሮ ወይም 5.56 ሚሊዮን ዶላር ዋስ ተለቆ ጉዳዩን እንዲከታተል፣ ከፈርንሳይ ሳይወጣ በሳምንት ሁለት ጊዜ ለፖሊስ ሪፖርት እያደረገ የፍርድ ሂደቱን እንዲከታተል መወሰኑ ቢሰማም ኢምሬትስ አምርራለች።
በፈረንሳይ ውሳኔ እጅግ የተቆጣችው ኢምሬት ተግባሩን በዝምታና በቀላሉ እንደማታልፈው ይፋ አድርጋለች። የዓለማችን ሀብታሟ አገር ዩናይትድ አረብ ኢሚሬትስ በፈረንሳይ ላይ እርምጃዎችን በመውሰድ ቁጣዋን የምትገልጽበትን ውሳኔ ጀምራለች።
በዚህም መሰረት ከፈረንሳይ ጋር ቀደም ሲል አስራው የነበረውን የ 20 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸውን 80 የጦር ጄቶች ስምምነቷን መሰረዟን በይፋ አስታውቃለች። ውሳኔውም ፈረንሳይን ከማስደንገጥ አልፎ ምላሽና ማብራሪያ እስከመስጠት አስድርሷል።
በጉዳዩ ላይ የተደናገጠቺው ፈረንሳይ በፕሬዚዳንቷ ማኑኤል ማክሮን በኩል “የዱሮቭ እስር ፖለቲካዊ አይደለም” ብትልም ኢማራት ግን አልተቀበለቺውም። እናም ፈረንሳይ በአስቸኳይ ፓቨል ዱሮቭን የማትለቅ ከሆነ እርምጃዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል ኢማራት ፍንጭ ሰጥታለች።
ፓቨል ዱሮቬ ከሩሲያ ከተሰደደ በሗላ የፈረንሳይ ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ዜግነት ቢኖረውም አሁን ላይ ዋና ሀገሩ አድርጎ የመረጣት ኢምሬትን ነው። ኢምሬትስ በአሁኑ ሰአት የቴሌግራም ዋና መቀመጫ ሆናለች።
ፈረንሳይ ፓቨል ዱሮቭ የቴሌግራም ዋና መቀመጫን ፈረንሳይ እንዲያደርግ ብዙ ግፊት ስታደርግ ብትቆይም ሳይሳካላት ቀርቶ ዱሮቭ ኢምሬትን መርጧል። አንዳንድ ሚዲያዎች ለፓቨል እስራት አንዱ ምክንያት የፈረንሳይን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉ እንደሆነ እየገለጹ ነው። በዚሁ ብስጭትና ቂም ዜጋዋ የታሰረባት ኢምሬትስ ፈረንሳይ ላይ የወሰደችውን እርምጃ የሚከተሉ አገራት ለጊዜው ይፋ ባይሆኑም በተከታታይ አቋማቸውን ይፋ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።