ኢትዮጵያን አረንጓዴ ለማልበስ ማቀድና የባህር በር ባለቤት ለማድረግ የተጀመረው እንቅስቃሴ ” ኢትዮጵያዊ ነን” ከሚሉ ወገኖችና አብልታ አጠጥታ በነከሷት የታሪክ እራፊዎች ተግዳሮት ሲገጥመው ማየት ስም ሊወጣለት የማይችል ስሜት ውስጥ ይከታል። የበሉበትን ወጪት ሰባሪዎቹን ትተን የራሷ “ልጆች” እንደሆኑ በሚነግሩንና በሰንደቋ ተጠቅልለው ሌት ከቀን የአዞ እንባ የሚያነቡት ነጋዴዎች ዘመቻ የከፈቱበት አግባብ ግን ለማንም ግልጽ አይደለም።
ቢቢሲ በ21 ታህሳስ 2019 እትሙ በአረንጓዴው አሻራ መርሃ ግብር ዕቅድ ላይ ውሃ ለመቸለስ ” በትግራይ ክልል የተተከሉት አዳዲስ ችግኞች አካባቢው ደረቅ በመሆኑ ሳቢያ ለማደግ እየታገሉ ነው” ሲል ቀደም ብለው የተተከሉትን ችግኞች ፎቶ በማሳየት አብይ አህመድ ትግራይ በተመንደሩና በየኮረብታው እየዞሩ በየቀኑ ውሃ እንዲያጠጡ የመጋበዝ ያህል ጽፏል። ይህ ብቻ አይደለም ” የሳተላይት ፎቶ የሚያጠና ድርጅትም አነጋግረን ነበር። ድርጅቱ አዲስ የተተከሉትና በመጠን አነስተኛ የሆኑትን ችግኞች ከእርሻ መሬት ለመለየት አዳጋች እንደሆነ ገልጾልናል” ሲል ቢቢሲ የችግኝ ቆጠራ ለማካሄድና ኢትዮጵያ ዕቅዷን ማሳካት እንደማትችል ለመዘገብ የሄደበትን ርቀት እንድንታዘብ አድርጎናል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ያስጀመሩት የግሪን ሌጋሲ የችግኝ ተከላ ሳምንት እንዳለፈው ” የችግኝ ተከላ ዘመቻው ሲተዋወቅ፤ የዓለም ክብረ ወሰንን መስበር እንደ አንድ ግብ ተይዞ ነበር። ሆኖም ቢቢሲ ለ’ጊነስ ወርልድ ሬከርድ’ ጥያቄ ሲያቀርብ፤ ገና ማስረጃ እንዳልቀረባቸው ገልጸዋል” ሲል ገና ውጤቱ ሳይታወቅና ኢትዮጵያ በይፋ ሪፖርቷን ሳታስታውቅ ቢቢሲ ጊነስቡክ ደጅ ማደሩን ነግሮናል። ያልነገረን ብዙ እንዳለ ከግምት ውስጥ እናስገባለን።
የችግኝ ተከላ ተቃውሞ ተናብቦ የመሥራት የሰኔ ፕሮጀክት ይሆን ብለን እንድንጠይቅ የሚገፋፋን በብዙ ምክንያት ነበር። ቴዲ አፍሮ እርሱ ከውድ ባለቤቱ ጋር “የአረንጓዴ መሬት” ሃሳብን ሲያራምዱና ችግኝ ሲተክሉ ትክክል ነበሩ። ችግኙ ሚካኤልም እንዲሁ ችግኝ ሲተክል ሕዝብ ይጨፈጨፍ ነበር። ሆኖም ግን የቴዲን የዚያን ጊዜውን ሃሳብ ማንም አልተቃወመም። “ሚካኤል ችግኝ ነው። … ችግኝ ይተክላል” ያለው ቴዲ የሕዝብ ሰቆቃ ድምፅ ነኝ በሚል “ሳር ያለመልማል ዛሬም በእልፍ አእላፍ ሬሳ” ብሎ ቀን ጠብቆ በችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ ዕለት ነጠላ ዜማ መልቀቁን በወቅቱ የዛሬ ሁለት ዓመት ግድም ማለት ነው “ሚዛን ደፊውን ቴዲ ሚዛን ተደፋብህ አስብሎናል” በሚል የቀረበበትን ትችት ዛሬም ድረስ የታሪኩ አንድ ክፍል ነውና የአረንጓዴ አሻራ ጉዳይ ሲነሳ አንረሳውም። ሊንኮቹን ተጭነው አስተያየቶቹን ያንብቡ።
በደርግ ጊዜ ከተከናወኑና እጅግ ከሚያስመሰግኑ ተግባራት ቁንጮውና ዘመን የማይረሳው ድንቅ ተግባር በመሃይመነት ላይ የታወጀው ጦርነት ነው። “መሃይምነት ጥቁር መጋረጃ ነው” በማለት ከገጠር እስከ ከተማ የተሠራው ድንቅ ሥራ ጥቂት የማይባሉ ዜጎችን ለኮሌጅ ሲያበቃ፣ በጣት ይፈርሙ የነበሩ ሚሊዮኖች ግን ስማቸውን በብዕር እንዲጽፉ ያስቻለና ሰብዓዊ ክብራቸውን የመለሰ የኩራትነ ገድል ነው። ይህ የተደረገው ሕዝብ በጦርነትና በረሃብ እንደ ቅጠል በሚረግፍበት ጊዜ ነው። ይህን ታላቅ ስኬትና ገድል ድርግን በመጥላት ማቆሸሽና ገድል መክተት ባይቻልም፣ እንኳን ቴዲ በወቅቱ አልተወለደ ያሉ ብዙ ናቸው። ምክንያቱም በውቀቱ ቴዲ ለዓቅመ ዘፋኝነት ደርሶ ቢሆን ኖሮ ኖሮ “መሃይምነት ይኑርልን ” ብሎ ይቀኝ ነበር። “ዛሬም በሕዝብ ሬሣ” ብሎ ይዘፍን ነበር። እነዚህ ወገኖች ቴዴን “እንኳንም ያኔ ህጻን ሆነ” የሚል ምኞታቸውን ጽፈው ነበር።
ሲጀመር ዘመቻው ብዙ ነበር። የዕድል ጉዳይ ሆኖ “ትናንት እንዲህ ብለህ ነበር፣ ወይም ብላችሁ ነበር” ስለማይባሉ እንጂ የህዳሴውን ግድብ አብይ አህመድ በስልክ እንዲሸጥ ማዘዛቸውን ከነገሩን ጀምሮ ሁሉም ዓይናቸውን አጥበው በአዳዲስ አጀንዳ ይከሰታሉ። የቢቢሲ ኢትዮጵያዊ ሪፖርተሮች፣ ቴዲ አፍሮና አጃባቢዎቻቸው፣ “ነሐሴ 17 በአንድ ጀምበር 600 ሚሊየን ችግኞችን በመትከል አሻራችንን እናኑር” ለሚለው ጥሪ አካፋ ይዘው በይቅርታ ለተከላው ይሰማሩ ይሆን? ውይስ በዘፈን ታጅበው ዛሬም ያልጸደቁትን ችግኞች ለቀማ ይወጡ ይሆን? እናያለን።
ኢትዮጵያ ላይ በስምምነት የቆለፉባትና 120 ሚሊዮን ሕዝብ አንገት አንቀው በቅብብሎሽ በትከሻዋ ላይ “ሲንጋፖርን” ለመሆኑ የተመኙ ተከርበተው ሲያበቁ ኢትዮጵያ የተሰቀለችበትን ገመድ በጥሳ የባህር በር መተንፈሻ እንድታገኝ ጥረት ሲጀመር ከጮሁ ባንዳና የባንዳ አቀንቃኞች ምንም አይጠበቅም።
መንግስትን፣ ባለስልጣናትን፣ ፓርቲን፣ አሰራርን ከብሄራዊ ጉዳይና አጀንዳችን በመለየት መንቀፍ፣ ማረቅ፣ ማውገዝ፣ ማጥላላት እንደ አግባቡ ጤነኛ አካሄድ ሆኖ ሳለ ችግኝ ለምን ተተከለ ብለው እዛና እዚህ የሚሯሯጡትን ክፍሎች ለታሪክ አንገዋሎ ከመስጠት ውጭ ሌላ የሚባል ነገር የለም።
ለማንኛውም በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ተሰምቷል። በአዲስ አበባ ለሚካሄደው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርኃ-ግብር የተለያዩ አይነት ችግኞች ቀርበው ዓርብን እየጠበቁ ነው። ችግኝ የሚያፈሉ ማኅበራትና ተቋማት ዝግጅቱን ይፋ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ” ነሐሴ 17 በአንድ ጀምበር 600 ሚሊየን ችግኞችን በመትከል አሻራችንን እናኑር” ሲሉ አሳቡ ለገባቸው፣ መለምለምን ለሚናፍቁ፣ ብሄራዊ አጀንዳና የፓርቲ ጉዳይን ለየተው ለሚያዩ ዜጎች በጥቅሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዛሬ ላይ ዛፍ መትከል የምርጫ መወዳደሪያና ማሸነፊያ አጀንዳ በሆነበት ወቅት ” ዛፍ መትከልን የብልጽግና ነውር አድርገው ለሚያቀርቡት ሳይቀር በቀረበው ጥሪ፣ “በአንድ መንፈስ በመላው ኢትዮጵያ አሻራችንን እናኑር፤ አንድ ከሆንን ከዚህም በላይ እንችላለን” ሲሉ አብይ አሕመድ የታሪኩ ተጋሪ እንዲሆኑ ጋብዘዋል።
አዋቂዎች ከ20 በላይ፣ ታዳጊዎች ከ10 በላይ ችግኞችን በመትከል ለአገር ያለንን ፍቅር፣ ለትውልድ ያለንን ሥጦታ በተገቢው ሥፍራ እንግለጥ ሲሉ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል።
የተለያዩ ዝርያ ያላቸው አገር በቀል፣ የውበትና ፍራፍሬ ችግኞችን በማዘጋጀት ለከተማው ነዋሪዎችና ለተለያዩ ተቋማት እያቀረበ መሆኑን ስራውን በሃላፊነት እየሰሩ ያሉ ወገኖች ገልሰዋል። እግረ መንገድ ራስን መመገብንም ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የሚከናወነው የሽግኝ ተከላ የችጋር ማራገፊያውን ዋና ስራ እነደሚያቃልለው ባለሙያዎችና ኒውትሬሽን የተማሩ እየገለጹ ነው።
በጥቅሉ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ ነው። በ2015 ዓ.ም በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ችግኞች ተተክለዋል። ሚኒስትሩ በወቅቱ በተካሄደ የዳሰሳ ጥናት ላይ እንዳሉት የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ የጽድቀት መጠናቸውን 90 ከመቶ ማድረስ እንደተቻለም ገልፀዋል፡፡
ለዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ዕቅድ መያዙን ጠቅሰው ለዚህም 7 ነጥብ 2 ቢሊየን ችግኝ መዘጋጀቱን ተናግረዋል። በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ለሚተከሉ ችግኞችም በሀገር አቀፍ ደረጃ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለተከላ መዘጋጀቱንም ትመልክቷል።
ኢትዮጵያ በውይይትና በመነጋገር ልትፈታቸው የሚገባቸው በርካታ ችግሮች ቢኖሯትም በአረንጓዴ አሻራ ዘርፍ የሰራችው ስራ ዓለምን፣ ታላላቅ አገራትንና ተቋማትን ያስደነቀ፣ “ምሳሌ ይሆነናል” ያሰኘ መሆኑን በርካታ የዓለማችን መገናኛዎች እየከፋቸውም ቢሆን ጽፈዋል» እየጻፉ ነው።