ነፃ ገበያ በስም ፍጹም ይምሰል እንጂ በተግባር ፍጹም ሆኖ አያውቅም፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ልትሰራበት የተያያዘችውን ዓይነት አሠራር ምዕራባውያንን ጨምሮ በርካታ አገራት የሚሰሩበት የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ነው፡፡ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ አዲስ የሚሆነው ለመጀመሪያ ጊዜ ስራ ላይ ሲያውሉት፣ በአጭር ጊዜ የተለያዩ የማክሮና የማይክሮ ቀውሶችን የሚያስከትል ስለሚመስል/ስለሚሆን ነው፡፡ ይህ አጠቃላይ እይታ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ የወቅቱ የውጪ ገንዘብ ምንዛሪ የገበያ አካሄድ (floating exchange rate) ሊያስከትል የሚችለው የገበያ ቀውስ ቀለል ሊል የሚችልባቸውን ባሕሪያዊና አስተዳደራዊ ሁኔታዎች/ምክንያቶች
በስንታየሁ ገብረጊዮርጊስ – ነጻ አስተያየት
- እንደ መንደርደሪያ
ነፃ ገበያ ማለት በአቅርቦትና በፍላጎት የሚመራ ገበያ እንደሆነና፣ በአቅርቦትና በፍላጎት ላይ ተመስርቶ በሚሰራ ገበያ ውስጥ ደግሞ ሰዎች (አምራቾች፣ ሻጮችና ሸማቾቸ) ትርፍና ኪሳራቸውን (ጥቅምና ጉዳታቸውን) አስልተው ምክንያታዊ (rational) በመሆን የሚገበያዩ መሆናቸውን ስታንዳርድ ኤኮኖሚክስ (Standard Economics) ያስተምራል፡፡
ለአንድ ሸቀጥ ከፍተኛ ፍላጎት ባለበት ሁኔታ አቅርቦቱ ከፍላጎቱ ካልተመጣጠነ/አነስተኛ ከሆነ የሸቀጡ ዋጋ ከፍ እንደሚል የኤኮኖሚክስ ትምህርት ሀሁ ነው፡፡ በሌላ በኩል አቅርቦቱ ከፍላጎቱ ከበለጠ የሸቀጦች ዋጋ ሊቀንስ እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ ፍላጎታቸው የቀነሰ ምርቶች የመሸጫ ዋጋቸው ከማምረቻ ወጪያቸው እጅግ በጣም ቀንሶ የተሸጡ/የተወገዱ መሆኑን መስማትና ማየት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ አቅርቦትና ፍላጎት የአንድ “ነፃ ገበያ” ገዢ መርሆዎች እንደሆኑ መደበኛ ኤኮኖሚክስም ሆነ ባሕሪያዊ ኤኮኖሚክስ (Behavioral Economics) የሚያስተምሩት ጉዳይ ነው፡፡
ከዛሬ ሃምሳና ስልሳ ዓመታት ወዲህ ባሕሪያዊ ኤኮኖሚክስ (Behavioral Economics) የሚባል፣ በመደበኛ ኤኮኖሚክስ ትምህርት ላይ የተመሰረተ፣ ይሁን እንጂ የሰዎችን ኤኮኖሚያዊ ውሳኔዎች ምክንያታዊነት የሚያጠይቅ የመደበኛ ኤኮኖሚክስ ትምህርት አቻ አለ፡፡ ዘርፉ የመደበኛ ኤኮኖሚክስ (Standard Economics) ዕውቀትን የግድ የሚል ከመሆኑም በላይ፣ የስነ ልቡና እና የማሕበረሰብ አኗኗር ዕውቀት ግንዛቤንም ይጠይቃል፡፡
ባሕሪያዊ ኤኮኖሚክስ ሰዎች የሚወስኗቸውን ውሳኔዎች ሁሉ ጥቅምና ጉዳታቸውን በመመዘን ብቻ የሚወስኑ አይደሉም፤ እንደውም ኢምክንያታዊ የሆኑ ውሳኔዎችን የሚወስኑባቸውና አንዳንዴ ከኤኮኖሚ ሕግጋት የተጣረሱ እርምጃዎችን የሚወስዱባቸው ወቅቶች ቀላል አይደሉም በማለት አሟጋች ሀሳብን ይከተላል፡፡ የሰዎች (አምራቾች፣ ሻጮችና ሸማቾቸ) ውሳኔን የሚወስኑበት ባሕሪ ከተለያዩ ኤኮኖሚያዊ ካልሆኑ የሰዎች ባሕርያት ሊመነጩና ተጽእኖ ሊፈጥሩ እንደሚችሉም ያስረዳል፡፡
ሰዎች ያሉበት ሕብረተሰብ ባሕል፣ የኤኮኖሚ ደረጃ፣ እምነት፣ የትምህርት ደረጃ፣ የአካባቢ ተጽእኖ፣ ወዘተ ውሳኔዎቻቸውን ለማድረግ/ለመወሰን፣ በውሳኔያቸው እንዲጸኑ ወይንም እንዲዋልሉ ስለሚያስገድዷቸው ኢምክንያታዊ የሆኑ ውሳኔዎችን እንዲፈጽሙ ያደርጓቸዋል በማለት ጥቆማ ሊሆኑ የሚችሉ ምርምሮችን ባሕሪያዊ ኤኮኖሚክስ በምሳሌ ያቀርባል፡፡ የተለያዩ ሰዎች ሊገዙ ወስነው ወደ ገበያ የወጡባቸውን ምክንያቶችን ለውጠው ሌላ ውሳኔ በመወሰን ያላሰቡበትን አድርገው ሊመለሱ ይችላሉ፤ … የሚለውን ሀሳብ በምን ትተነትኑታላችሁ?
በተለይ በኢትዮጵያ ሁኔታ ከመደበኛ ኤኮኖሚክስ ይልቅ ባሕሪያዊ ኤኮኖሚክስ የበለጠ የኤኮኖሚውን እንቅስቃሴና የሰዎችን (አምራቾች፣ ሻጮችና ሸማቾቸ) ውሳኔ የሚገዛ/የሚያሳይ ሊሆን እንደሚችል በግሌ ግንዛቤን ወስጃለሁ፡፡ በመደበኛ ኤኮኖሚክስ ትምህርት የተገኘ ግንዛቤን በሥራቸው ውስጥ እምብዛም የማይቀላቅሉ የልምድ ነጋዴዎችን ታሳቢ በማድረግና፣ የኤኮኖሚ ቲዎሪ ሁሌም ባሰበው መንገድ ሊከወን እንደማይችል (ቴዎሪና ተግባር ለየቅል የሚሆኑበት ሂደት እንደሚኖር) በመገመት፣ በወቅቱ መንግሥት ለመከተል የወሰነውን የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ፖሊሲ ለየት ባለ ዕይታ መቃኘት ተገቢ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ከዚህ አኳያ ነው በወቅቱ ያለውን የውጭ ገንዘብ ምንዛሪ አስተዳደር በአገሪቱ ኤኮኖሚና በሕዝቡ የመግዛት አቅም ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ሂደትና ውጤት ለማየትና ለመገምገም ጥረት የማደርገው፡፡
ባሕሪያዊ ኤኮኖሚክስ፤ የሰው ልጆችን የዕለት በዕለት ውሳኔዎች ባህሪያትን፣ በኤኮኖሚክ ቲዎሪዎችና እሳቤዎች ላይ አስመርኩዞ በሙከራ እየፈተነ የሚተነትን መስክ በመሆኑ ትንተናው ቀላል አይሆንም፡፡ ቀላል የማይሆነው እያንዳንዱ የኤኮኖሚ ባሕሪያዊ ውሳኔ በሙከራ በተፈተነ ማስረጃ መደገፍ ስላለበት በመደበኛ ኤኮኖሚክስ በተቡ ምሁራን እይታ ቀላል የማይባል ሙግት ሊገጥመው መቻሉ አንዱ ነው፡፡ ብቸኛ ምክንያት ግን አይደለም፡፡ ዋናው ምክንያት የሰዎች (የአምራቾች፣ የአቅራቢዎችና የሸማቾች) ባሕሪያት የተወሳሰቡና ምርምር/ጥናት የሚሹ መሆናቸው ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ በዚህ አጭር ጽሑፍ አልፎ አልፎ በትንሷ የሻይ ማንኪያ በድፍረት ጨልፌ መከላለሴ አይቀረም፡፡
2. በውጪ ምንዛሪው አስተዳደር ላይ የሚሰሙና የሚታዩ ብዥታዎች
በወቅቱ እየተከናወነ ያለውን የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር የተለያዩ ሰዎች በተለያየ መነጽር እየተመለከቱት መሆኑን መረዳት ችያለሁ፡፡ የብርን መዳከምና (Devalue መሆን ወይንም የመግዛት አቅም መቀነስ)፣ በአንጻሩ የውጭ ምንዛሪን መጠንከር አጉልቶ በማቅረብ ሰዎች (አምራቾች፣ ሻጮችና ሸማቾቸ) በተለያዩ ውዥንብሮች ላይ መውደቃቸውን አይቻለሁ፡፡ አንዱ ችግር በኤኮኖሚው ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ አካላት (ለምሳሌ፣ ነጋዴዎች) ስለኤኮኖሚክስ፣ በጥቅሉ ስለማክሮ ኤኮኖሚው አሰራር በቂ ዕውቀት ያላዳበሩ መሆናቸውና በወሬ የሚመሩ መሆኑ ይመስለኛል፡፡ ሌላው፤ ማክሮ ኤኮኖሚው የገባበትን ችግር በነፃ ገበያ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትና ፍላጎት (Floating Exchange Rate) ግብይት ለማስተካከል የተወሰደውን ውሳኔ፣ ብርን የማዳከም (Devalue) እርምጃ አይደለም፤ ነው በሚለው እሰጥ አገባ ውስጥ ሁሉም የተጠመደ መሆኑ ነው – በተለይ ኤኮኖሚስቶቹ፡፡ ብር እንዲዳከም አልተደረገም፤ እየተደረገ ያለው ሕጋዊ የውጭ ምንዛሬውን (በባንኮች በኩል የሚካሄደውን) ከኢ-ሕጋዊው (ጥቁር ገበያው) የውጭ ምንዛሬ እኩል ለማድረግ/ለማመሳሰል ነው በማለት መግለጫ መስጠትም ዝም ብሎ ተራ ምክንያት ለመፍጠር መሞከር ነው፡፡ ምን ጊዜም በነፃ ገበያ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትና ፍላጎት (Floating Exchange Rate) ግብይት ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባር ላይ ሲውል የአገር ውስጥ ገንዘብ (ለምሳሌ፣ ብር) የመግዛት ኃይሉን መቀነሱ አይቀርም፡፡ ያ ማለት ግን ብር ዲቫልዩ ተደርጓል ማለት አይደለም፡፡
የብር ዲቫሉዌሽንና የውጭ ምንዛሪ በነጻ ገበያ አቅርቦትና ፍላጎት (Floating Exchange Rate) ግብይት እንዲካሄድ መደረጉ የሚያደርሰው የብር የመግዛት አቅም መዳከም አንድ አይደሉም፡፡ ሆኖም፣ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር/ልውውጥ በመንግሥት ጣልቃ ገብነት የተነሳ መድረስ ከነበረበት የገበያ የምንዛሪ ጣሪያ ታፍኖ ፍላጎትና አቅርቦት በተዛቡበት ሁኔታ ውስጥ (የውጭ ምንዛሪ እጥረት መኖሩ አንዱ ምክንያት በሆነበት)፣ በነጻ ገበያ የፍላጎትና አቅርቦት ሂደት አማካኝነት ምንዛሪው እንዲካሄድ ሲደረግ የብርን የመግዛት አቅም የሚሸረሽረው/የሚያዳክመው መሆኑ እሙን ነው፡፡ ብር እንዲዳከም መንግሥት በመሥራቱ ሳይሆን፣ የምንዛሪ የነፃ ገበያ ሂደት የግድ ብሎት የብር የመግዛት አቅምን እንዲዳከም ያደረግዋል፡፡ ይህ የኤኮኖሚ ሕግ ነው፡፡ በማብራሪያ ወዲያ ወዲህ ቢያዟዙሩት ፋይዳ የለውም፡፡
አገሪቱ በዕዳ ጫና ውስጥ መሆኗን ሁሉም ያውቃል፡፡ ቢያንስ ባለስልጣናት በብዙኃን መገናኛ የሚገልጡትን አዋጅ ሁሉም በሚባል ደረጃ ይሰማዋል፡፡ ገበያው በከፍተኛ የዋጋ ግሽበት/ንረት (ኢንፍሌሽን) ውስጥ እየዳከረ መሆኑን ሸማቾች በየዕለቱ ከሚሸምቱት ምርት የዋጋ ንረት ይረዱታል፡፡ በውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች ዋጋቸው ከፍተኛ መሆኑን ሸማች የሆነ ሁሉ ያውቀዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪን የሚሹ የአገር ውስጥ ምርቶች/ግብዓቶች አቅርቦት በመቀነሱ፣ የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው በማምረት ከውጭ የሚገባውን ምርት ሊተኩና ዋጋን ሊያረጋጉ እንዳልቻሉ ግንዛቤ አለ፡፡ እንደውም ቀላል የመይባሉቱ እያመረቱ አይደሉም፡፡ ያም ይታወቃል፡፡ አገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የሸቀጦች ፍላጎት አለ፡፡ የሸቀጦች አቅርቦት ግን በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያትም ይሁን የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅም ባለማምረታቸው በጉልህ የሚታይ ነው፡፡ የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችም በሙሉ አቅም ያለማምረታቸው ጉዳይ ምክንያቱ፣ በውጪ ምንዛሪ እጥረት መኖር የተነሳ የምርት ግብዓት በሚፈለገው መጠን ባለመኖሩ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡
በየትኞቹ ምርቶች? ምን ያህል ፍላጎት አለ? የሚለው በውል ተጠንቶ የተጠናቀረ መረጃ አላየሁም፡፡ በውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ የምርት አቅርቦት ሊመናመን ይችላል፡፡ አቅርቦት ሳይኖር አምራች፣ አቅራቢና (ነጋዴ) ሸማች የሚኖራቸው ጠባይ ይለያያል፡፡ ለዕቃው/ሸቀጡ የገበያ ፍላጎት ካለ፣ አምራች ብዙ አምርቶ ለገበያ በማቅረብ ይጠቀማል፡፡ በገበያው ላይ የሸቀጥ ፍላጎት ኖሮ አቅርቦት በመጓደሉ ሳቢያ ሸማቹ የሚፈልገውን ዕቃ (ቋሚም ይሁን አላቂ የእለት ፍጆታ ሸቀጥ) በውድ ዋጋ ከአምራቹም ይሁን ከነጋዴ/አቅራቢ ለመግዛት መገደዱ ግልጽ ነው፡፡ ይህንን የትኛውም ሸማች የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡
3. የሸቀጥ ፍላጎትና የመግዛት አቅም
የመግዛት አቅም ማለት የገንዘብንና የሸማቾችን አቅም ጠቅልሎ ያያዘ ሀሳብ ነው፡፡ ፍላጎት ስላለ ብቻ ለገበያ የቀረበ ሸቀጥ ሁሉ ይሸጣል ማለት አይደለም፡፡ የመግዛት አቅም ያስፈልጋል፡፡ አንድ ድሀ ሰው የመግዛት አቅም የለውም ማለት፣ ሸቀጡን ለመግዛት የተጠየቀው ገንዘብ የለውም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሊሸምት አይችልም፡፡ የሸቀጥ ፍሰት (flow) ገንዘብ/ገዢ ወዳለበት አቅጣጫ ነው፡፡ የመግዛት አቅም በሌለበት ሁኔታ፣ ምርት የማምረት አቅም ቢኖር እንኳን መሸጥ አይቻልም፡፡ የመግዛት ፍላጎት በሌለበት ወይንም የመግዛት አቅም በጎደለበት ሁኔታ ውስጥ፣ አምራቹና ሻጩ (ነጋዴ/አከፋፋይ) ምርትን/ዕቃን ለገበያ ቢያቀርቡ ትርፋማ አይሆኑም፡፡ አምራቹ በጥቂት ለማምረት፣ ሻጩም (አምራቹ በቀጥታ ካልሸጠ) በጥቂቱ ለገበያ በማቅረብ ላይ መወሰናቸው ግልጽ ነው፡፡ ምርት፣ አቅርቦት፣ ፍላጎትና የመግዛት አቅም/ገንዘብ የተቆራኙ መሆናቸው ለዚህ ነው፡፡
በሌላ በኩል የሸማች ባሕሪ የሚከተለው የተለየ አካሄድ አለው፡፡ የሸማች ባሕሪ ከአምራችና ከአቅራቢ (ነጋዴ) ጋር የሚገናኝባቸውና የሚለያይባቸው መስመሮች በርካታ ናቸው፡፡ በውሳኔ አሰጣጥም ይሁን በምኞት (ፍላጎት) ረገድ ይለያያሉ፡፡ አምራቹም ሆነ አቅራቢው (ነጋዴው) በብዙ ጎናቸው ሸማቾች ናችው፡፡ ነጋዴ ወይንም አምራች የሆነው ሰው በሸማችነቱ የሚከተለው ባሕሪ ከሌላው ሸማች አይለይም፡፡ በርካሽ ዋጋ መሸመት ይሻል፡፡ አምራቹና ነጋዴው ከተራ ሸማች የሚለዩት፣ ያላቸው የመግዛት አቅም በፈጠረላቸው ጠባይ/ዕድል ላይ ተመስርተው መሸመታቸው ነው፡፡ ያም ሆኖ፣ በርካሽ ዋጋ ለመግዛት ጥረት ማድረግ የሁሉም ሸማች ባሕሪ ነው፡፡ አምራችና አቅርቢ/ነጋዴ ሲሆኑ ደግሞ ሌላ ጠባይ ይላበሳሉ፡፡ ከዚህ ተነስቼ የኢትዮጵያውያንን ጥቅል የሸመታ ባሕሪ ልነካካው፡፡
ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን ከቢዝነስ ባህል ይልቅ ያላቸው የዳበረ የመተሳሰብ (compassionate) ባሕል ነው፡፡ በግሌ ቢዝነስና የቢዝነስ ኤቲክስ ባሕል (ከሸማች ጋር የመተሳሰብ ባሕል) አብረው መሄድ ያለባቸው የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው በማለት አምናለሁ፡፡ “ንግድ ንግድ ነው (business is business)” ከሚለው፣ “አንተም አትርፈህ ሌላው እንዲኖር አግዘው” የሚል የመተሳሰብ ግብረገባዊ አካሄድ ለኢትዮጵያውውን ባህሪ የሚቀርብ ነው፡፡ ኤቲካል (ethical) ሆኖ በመነገድ ሀብታም መሆን ይቻላል፡፡ 1000 ብር ታተርፍ እንደሆነ 850 ብር አትርፍና ሸማቹም ያትርፍበት የሚለው የቢዝነስ አካሄድ ለእኔ ይጥመኛል፡፡ የቢዝነስ ኤትክስ በሰፈነበት ሁኔታ የሸማችን/ደንበኛን እምነት እያተረፍክ መነገድ ትችላለህ፡፡ በትንሽ ቀንሰህ ሸማችን ማስደሰትና እምነትን ማትረፍ ማለት ነው፡፡ ትርፍህ በአንጻራዊነት ይቀንስ እንደሆነ እንጂ በምንም ዓይነት አትከስርም፡፡ ራስክን ብዙ ትርፍ ከሚያግበሰብሰው ጋር ካነጻጸርክ ኤቲካል አትሆንም፡፡ልኩ ራስህን መሆን ነው፡፡ የንግድ ዓላማ ሳይከስሩ በመቆየት ንብረት/ሀብትን ማፍራት ነው፡፡ የገበያ ግንኙነት ሀሳብ፣ ቅንነትና ዕውቀትን በመያዝ የተሟላ ሰው ይኮናል የሚለውን አብሮ ማሰብ ነው፡፡ ካለዕውቀት መበልጸግም ይቻላል፡፡ በዚህ አልከራከርም፡፡ ለማሳየት የምሞክረው የገበያ ግንኙነት የሰዎችን ባህሪ ሊወስን (በአንጻሩ ባሕሪው ግኙነትን ሊያሳድግ) የሚችል መሆኑን ብቻ ነው፡፡ ዝርዝር ውስጥ መግባት ሳያስፈልግ፤ በወቅቱ በውጭ ምንዛሬ ግብይት ምክንያት በአምራች፣ ነጋዴና ሸማች መካከል የተከሰተው ውዥንብር (በኤኮኖሚስቶች የሚናፈሰው ሟርት ጭምር) ከሰዎችና ከገበያ ባሕሪያት የሚመነጩ ናቸው፡፡
3 የኤኮኖሚስቶችና የኤኮኖሚው ችግሮች
በ2009 እኤአ (2008/2009) በዓለም ዙሪያ የፋይናንስ ቀውስ (mortgage and financial markets’ meltdown) ተከስቶ ነበር፡፡ ቀውሱ የተከሰተው አንቱ የሚባሉ የኤኮኖሚክስ ሎሬቶችና ዕውቅ ኤኮኖሚስቶች በዓለም ዙሪያ በነበሩበት ሁኔታ ነው፡፡
ጊዜያዊ ትርፍን ዓላማ ያደረጉ የፋይናንስ ሴክተሩ ተዋንያን [(የሪል ስቴት ባለሀብቶች፣ ደላሎች፣ ነጋዴዎችና መዛኝ ኤጄንሲዎች (Rating Agencies)] በወቅቱ ትረፋቸውን ወደ ኪሳቸው በማድረግ ሸማቾችን ዘርፈው አክስረዋል፡፡ እነሱ ግን በልጽገዋል፡፡ ችግሩ ሲከሰት ተጎጂ የሆኑት ሚሊዮኖች ሸማቾችና የአገር ኤኮኖሚ ሆነው ተከሰቱ፡፡ ከዚያ ቀደም ብሎም ይሁን በዚያን ወቅት ዕውቅ ኤኮኖሚስቶች እንኳን የፋይናንስ ችግሩ እንደሚከሰት ምንም እውቀቱ አልነበራቸውም፡፡ የመደበኛ ኤኮኖሚክስ ቲዎሪ ዕውቀታቸውም አልረዳቸውም፡፡ ዓለም በፋይናንስ ሴክተሩ መመሳቀል ተጎዳች፡፡ ቤት ገዝተው የነበሩ ተወረሱና ከሰሩ፡፡ ኤኮኖሚው ተንኮታኮተ፡፡ የዓለም ባንክና አይ ኤም ኤፍ ያኔም ነበሩ፡፡ ለአገራት የሚያቀርቧቸው የዕድገት ሚዛን መለኪያዎችና ከችግር መላቀቂያ መንገዶቻቸውም አብረዋቸው ነበሩ፡፡ የእነሱ ዝግጁነት ያንኑ የሚያውቁትን አሮጌ መመሪያ በደላላነት መሸጥ ነውና፣ ለዓለም ሸማቾችና ለየአገራቱን ኤኮኖሚ ድቀት በፍጥነት መድረስ አልቻሉም፡፡ በወቅቱ፣ የከሰሩ ግዙፍ ባንኮችን ደጉመን ከችግራቸው እናላቃቸው የሚል መፍትሔ ብቻ ነው ይዘው የቀረቡት፡፡ የአሜሪካን መንግስት ያንን በማድረግ ትላልቅ ባንኮችን ከውድቀት ታድጓል፡፡ በሂደቱ ሸማቹም ይጠቀማል የሚል እሳቤን ይዞ ባንኮችን ያገዘ መሆኑን ልብ በሉ፡፡ በዓለም ላይ ለሸማቹ ቀጥታ የሚደርስለት መንግሥት አናሳ ነው፡፡
ዩናትድ ስቴትስን አስመልክቶ፣ በወቅቱ የአሜሪካን እጩ ፕሬዜዳንት የነበሩት ባራክ ኦባማ በማርች 27፣ 2008 እኤአ ባደረጉት ንግግር “የእኛ ነፃ ገበያ ያገኘኸውን ሁሉ እንደፈለግኸው ለመውሰድ ነፃ ላይሰንስ አይደለም” , “Our free market was never meant to be a free license to take whatever you can get; however you can get it.” ብለው ነበር፡፡ የምዕራቡ ዓለም የፋይናንስ ገበያ ምንኛ የአገራትን ኤኮኖሚ ለማመሳቀል የታጠቀ እንደሆነ የሚጠቁም አነጋገር ነበር፡፡
በወቅቱ የገረመኝ ነገር ነበር፡፡ እንዴት አንድ እንኳን ኤኮኖሚስት የ2008ቱ የፋይናንስ ቀውስ እንደሚከሰት ብልጭ ሳይልበት ቀረ? እንደማስታውሰው አንድ እውቅ ኤኮኖሚስትም ይሁን የፋይናንስ ኤክስፐርት የፋይናንስ ቀውሱ የት ድረስ እንደሆነ ለማወቅ የቻለ አልነበረም፡፡ አንዳንዶች (ለምሳሌ፣ የፌዴራል ሪዘርቭ ሰብሳቢ የነበሩት አለን ግሪንሰፓንና ሌሎችም) ምንም ያልጠረጠሩት ቀውስ በድንገት አንገታቸው ድረስ እንደዋጣቸው ቃላቸውን ሲሰጡ በትዝብት አድምጫለሁ፡፡ አይገርምም?
ለመሆኑ በዓለም ላይ ያሉት የተቀናጁ የኤኮኖሚ ቲዎሪዎች (harmonious Economic Theories) ለዓለም (ለአገራት) የኤኮኖሚ ችግሮች እንደየአገሩ ሁኔታ (የባሕል፣ የአስተሰሰብ፣ የኤኮኖሚ ደረጃ፣ ድሕነት፣ የሃይማኖት፣ የባሕሪ፣…) የተቀየሰ መፍትሔ/ሞዴል አላቸው? የላቸውም፡፡ ስለሌላቸውም የሚያቀርቡት አንድ ዓይነት መፍትሔን ብቻ ነው፡፡ ከተሳሳትኩ እታረማለሁ፡፡ አለማወቄን በይቅርታ እለፉት፡፡
በወቅቱ በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየሆነ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ፖሊሲም የዚሁ አንድ ዓይነት መፍትሔ አካል ነው፡፡ ይህ ነው በአምራቾች፣ በአቅራቢዎችና በሸማቾች መካከል ጊዜያዊ ውጥረትን ለመፍጠር ምክንያት የሚሆነው፡፡ ብዙ ጊዜ ሰው የሚያየው ሩቁን አይደለም፡፡ በአጭር ጊዜ የሚመለከተው በየዕለቱ በገበያ ላይ ሊታይ የሚችለውን የሸቀጦች የገበያ ዋጋ ውጣ ውረድን፣ የውጪ ምንዛሪ እየናረና የአገሪቱ መገበያያ ገንዘብ የመግዛት አቅሙ እየተዳከመ መሄዱን ነው፡፡ ያ ያሰጋዋል፡፡ ስለሚሰጋም የለመደው ኑሮ የሚያሽቆለቁልበት መሆኑ እየተሰማው ይሸበራል፡፡ የገበያው ጸባይ ሲለወጥ የእሱም ጸባይ ይለወጣል፡፡ ማን በማን ይፈርዳል? የሰዎች ባሕሪ ነው፡፡
የሰዎች ባህሪና ተግባር/ውሳኔ በኤኮኖሚ እንቅስቃሴዎች (interactions) ውስጥ ውስብስብ የሆነ ሚና አለው፡፡ እያንዳንዱ ትንበያ (forecast) ሁሌም መላምታዊ/አቦሰጥ (guesswork) ይበዛበታል፡፡ መላምት ደግሞ ሊሆንም ላይሆንም የሚችል አካሄድ ነው፡፡ እንዳይሆን ከሰራችሁበት አይሆንም፡፡ እንዲሆን ስትጥሩበት ሊሆን እስከሚችለው ድረስ ይጓዛል እንጂ እናንተ የተመኛችሁትን ያህል ርቀት አይሄድም – በታሳቢ (assumptions) ስለሚታቀድ፡፡ አቦሰጥን አብዝታችሁ ከሰራችሁበት ወደ አረፋ (bubble) ይቀየራል፡፡ ቀጥሎ ወደ ውዥንብር ይለወጣል፡፡ ይህ ውዥንብር በሰዎች አእምሮ ውስጥ ስለሚፈጠር በሚወስኑት ጉዳይ ላይ (በምርት፣ በሽያጭና ግዢ…) ላይ ተጽእኖውን ያሳርፋል፡፡ ውዥንበር ውስጥ የገባ ሰው ምክንያታዊ (rational) አይሆንም፡፡ የሚሆነው ኢምክንያታዊ (irrational) ነው፡፡ በወቅቱ ገበያ ውስጥ ማየት የምትችሉት ያንን ነው፡፡ ይህ የውዥንብር ሁኔታ የአጭር ጊዜ እንደሚሆን ተስፋ አለኝ፡፡
በእንዲህ ዓይነት ምክንያታዊነትና በኢምክንያታዊነት ስሜት መካከል የሚፈጠር አንድ አዲስ ሁኔታ (new normal) መኖሩ አይቀርም፡፡ ያ ግድ ነው፡፡ ይህ አዲስ ሁኔታ መጪውን የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚገዛ አዲስ መሰረት ሆኖ፣ ሌላ መንገጫገጭ እስኪፈጠር ድረስ የተረጋጋ የመምስል ባሕሪ አለው፡፡ እዚያ ላይ ለመድረስ እንደየአገሩ ሁኔታ ጊዜ ይጠይቃል፡፡ ትዕግስትና ማስተዋል እንጂ መሸበርና በወሬ መደናገር መፍትሔ አይሆኑም፡፡
የዓለም የፋይናንስ ቢሮዎች በኤኮኖሚስቶች የተሞላ ነው፡፡ የዓለም ባንክና የአይ ኤም ኤፍ ሞዴል ምንጊዜም አንድ ነው፡፡ የበለጸጉ አገራትን ጥቅም የሚያስከብረውን ሞዴል አገራት እንዲተገብሩ ማቅረብ ነው፡፡ ብድሩ፣ እርዳታው፣ “መደጎሚያው”፣… ዝም ብሎ የከረመን ጠጅ ማር አልሶ እንዲጠጣ የማድረግ ስልት ነው፡፡ ከብዙ መጥፎ አማራቾች ውስጥ ትንሽ የተሻለውን መጥፎ የመምረጥ ያህል ነው፡፡ የድሀ አገሮች አማራጭ በጣም ውስን ነው፡፡ ለማኝ መራጭ ሆኖ አያውቅም፡፡ መፍትሄው ከልመና ለመውጣት ጠንክሮ በመስራት አበዳሪ መሆን ነው – እንደ ቻይና፡፡
የፋይናንስና የሸቀጦች ገበያ (goods’ markets) የተለያዩ ናቸው፡፡ የፋይናንስ ገበያ በአመዛኙ በአጭር ጊዜ ውጤቶች (መውጣትና መውረዶች/ከፍታና ዝቅታ) ላይ የሚያተኩር ባሕሪ አለው፡፡ በዚህ ረገድ የኬኒዥያንና የኒዮክላሲካል ኤኮኖሚስቶች አንድ ላይ ጥምረት ፈጥረው በመስማማት የፋይናንስ ችግሮችን እንደየአገሩ ተጨባጭ ሁኔታ የሚፈታ ሞዴል ቢያቀርቡ ጥሩ ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ የፋይናንስ ችግር በማንም አገር የኤኮኖሚ ጤንነት ማጣት ላይ በአንደኛ ደረጃ አስተዋጽዖ ይኖረዋልና ነው “የማይስማሙ ኤኮኖሚስቶችን” እንዲስማሙና ለችግር/ለቀውስ ጊዜ አንድ ወጥ መፍትሔ እንዲያፈልቁ መመኘቴ፡፡ በወቅቱ ግን ሁለቱም እንደ 2008/2009 የተከሰተውን ዓለም ዓቀፍ የፋይናንስ ቀውስ (financial meltdown) ይቅርና፣ አንድ ድሐ አገር የሚያጋጥማትን የገንዘብ (liquidity) ችግር የሚፈቱበት አካሄድ ያው በተለመደው የውጭ ምንዛሪን (foreign exchange management) አቅርቦትና ፍላጎት ያመጣጥነዋል በሚሉት አስተዳደር ዘዴ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪው በገበያው (አቅርቦትና ፍላጎት) ላይ የተመሰረተ ምጣኔን (floating exchange rate ) አንዲከተል ትዕዛዝ ይሰጣሉ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ በዕውቀት ላይ ተመስርቶ ኑሮን መምራት እንጂ በወሬ ተመርቶ መደናገርና ገበያው እንዳይረጋጋ ማድረግ ሸማቾችን መበደል ነው፡፡ በገበያ ውጣ ውረድ የመጀመሪያ ተጠቂ ሸማቹ ነው፡፡ ነጋዴው የሸቀጡን ዋጋ የሚያሰላው በጥቁር ገበያ ምንዛሪ መሰረት በመሆኑ፣ ተጎዳሁ ይበል እንጂ መቼም ተጎድቶ አያውቅም፡፡ ወጪዎቹን በሙሉ ደምሮ የሚያስተላልፈው ወደ ሸማቹ ነው፡፡ በነፃ ገበያ እመራለሁ የሚል ማንኛውም መንግሥት በነጋዴው፣ በሸማቹና በመንግሥት (ፖለቲካ) ፍላጎት መካከል ተወጥሮ የሚንገዋለለው አንዱም ለዚያ ነው፡፡ ፍሎቲንግ (floating) ማለት በራሱ እኮ መረጋጋት የሌለበት ተንሳፋፊ ሁኔታ ነው፡፡ ቃሉ በራሱ አያረጋጋም፡፡ እናንተ ግን ለመረጋጋት ሞክሩ፡፡ ጥያቄው መቼ ይረጋጋል? ነው እንጂ፤ መረጋጋቱ አይቀርም፡፡ የምሰጠው ምክር ይህንኑ ነው፡፡
4 የውጭ ምንዛሬን በነፃ ገበያው ፍላጎት የመወሰን ጉዳይ
ሰዎች በማክሮ ኤኮኖሚው ማሻሻያ አሰራር የገንዘባቸው የመግዛት አቅም ሲቀንስባቸውና (ለምሳሌ፣ በብር 58 ሲገዙት የነበረው አንድ ዶላር አሁን በ90 ብር የሚገዙት ከሆነ የመግዛት አቅማቸው በብር 32 ይቀንስባቸዋል/ይዳከማል ማለት ነው፡፡ ቀድሞ ሲገዙበት ከነበረው ዋጋ ብር 32 ጨምረው እየገዙ ነውና)፤ በእጃቸው የሌለ የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ሲንርባቸው ደግሞ፣ ለክፉ ቀን ያጠራቀሙትን ገንዘብ የመግዛት አቅም እንደሚያመነምንባቸው በመስጋት ውዥንብር ውስጥ መውደቃቸው አይቀርም፡፡ ይህ ከሰዎች የኤኮኖሚ ጥቅም ወይንም ሳይጎዱ ከመኖር ባህሪ አኳያ የሚጠበቅ ስጋት ነው፡፡
እንደ ሸማች ሆኜ የማውቀው፣ እናንተም የምታውቁት አንድ ጉዳይ አለ፡፡ የዕቃዎችን ዋጋ እንደማወዳድርና በተቻለኝ መጠን በአነስተኛ ዋጋ (floor price) ብሸምት ፍላጎቴ ነው፡፡ የማንም ሰው ፍላጎትና ጠባይ ያ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ነጋዴው ደግሞ ያቀረበውን ዕቃ በከፍተኛ ዋጋ በመሸጥ ከፍተኛ ትርፍ ለማግኘት እንደሚተጋ አውቃለሁ፡፡ ያንን ነጋዴውም አይክድም፡፡ ሁሉቱ ቅራኔ አለባቸው? የለባቸውም፡፡ የነጋዴና የሸማች ጠባያት ናቸው፡፡
ለነጋዴው ፍላጎት (interest) የሚሰራው ነጋዴው እንጂ ሸማቹ አይደለም፡፡ ለሸማቹ ፍላጎት መስመር/መሟላት ግን ሁለቱም ያገባቸዋል፡፡ ሸማች ንጉሥ ነው (“consumer is a king”) የሚባለው በባዶ ሜዳ መሰላችሁ? ሸማች ከሌለ ነጋዴ የለም፡፡ ነጋዴ ከሌለ ግን ሸማች ከአምራች ሊሸምት ይችላል፡፡ በእርግጥ ነጋዴ የሸቀጥን አቅርቦት አውታሮችን ለመዘርጋትና ለማቀላጠፍ ጠቃሚ ነው፡፡ አምራች ብቻ አይጥፋ፡፡ አምራችን ማበራከት የሁሉም የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ ቁልፉ ጉዳይ የሆነው አንዱም ለዚያ ነው፡፡ ነጋዴ ሪስክ ቴከር ነው ይባላል፡፡ እርግጥ ነው፣ መሸጥ አለመሸጡን ሳያውቅ አስቀድሞ ሸቀጥን በገንዘቡ ገዝቶ በማከማቸት ያለመሸጥን (ሸ ይጠብቃል) ሪስክ ተሸክሟል፡፡ ከዚያ ውጪ ግን በኤኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ታሳታፊ የሆነ አካል ሁሉ ሪስክ ቴከር ነው፡፡ ኤኮኖሚክስ የእጥረት አስተዳደር መሆኑን አትዘንጉ፡፡ ይህ ማለት ኤኮኖሚክስ ሪስክ ያለባቸውን የሕይወት/ኑሮ ውጣ ውረድና ተለዋዋጭ ሁኔታዎች አስተዳደር ነው ወደ ሚለው ሊወስዳችሁ ይችላል፡፡ ገብቶኝ ይሆን ያልኩት?
በወቅቱ ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለችው ብርን የማዳከም ሥራ ነው፤ የለም የውጭ ምንዛሪን አቅርቦትና ፍላጎት ማስተዳደር ነው የሚሉ ሁለት አስተያየቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ዋናው ጉዳይ የአገሪቱ ብር ከውጭ አገር ገንዘብ አንጻር ሊኖረው የሚችለውን የምንዛሪ ዋጋ በነፃ ገበያው ግብይት በመወሰን የማክሮ ኤኮኖሚውን ጤና መርምሮ ማከም ላይ ነው የሚያተኩረው፡፡ ቀድሞ በ10 ብር ስትገዙት የነበረውን ዕቃ አሁን በ20 ብር ከገዛችሁት፣ ዋጋው ጨምሯል ወይንም የገንዘቡ የመግዛት አቅም/ኃይል ቀንሷል ሊባል ይችላል፡፡ ይህ ምኑ ያከራክራል? የፖሊሲ እርምጃው ምን ላይ ያተኩራል? መቼ ይረጋጋል? በሚለው መሠረታዊ ጉዳይ ላይ አስቡ፡፡
በወቅቱ መንግሥት የወሰደው እርምጃ ልክ ነው አይደለም? በሚለው ጥያቄ ውስጥ መግባት አካዳሚሽያን መሆን ነው፡፡ አካዳሚሽያንና በተግባር ውስጥ ቀጥታ የሚሳተፍ የኤኮኖሚ ባለሙያ ይለያያሉ፡፡ እርምጃው ዘግይቷል፤ መደረግ የነበረበት ከዛሬ 30 ዓመታት በፊት125 ግራም ክብደት ያለው አንድ ዳቦ ተቆጥሮ፣ 10 ዳቦዎች በአንድ ብር በሚገዙበት ጊዜ ነበረ እንጂ ዛሬ 80 ግራም የሚመዝን አንድ ትንሽ ዳቦ ከ7-8 ብር በሚሸጥበትና የዋጋ መጋሸብ በሁሉም መስክ ጣራ በነካበት ወቅት አልነበረም ማለትም አንድ የአስተያየት ዘርፍ ነው፡፡ የኋለኛው የብዙ ዜጎችና ኤኮኖሚስቶች ምኞት ነው፡፡ ሁሉንም ማስተናገድ መልካም ቢሆንም፣ ለዛሬው የሚጠቅም ሀሳብ አይሆንምና መተዉ መልካም ነው፡፡
የኤኮኖሚው ችግር እየጠነነ በመሄዱ ግን፣ ለችግሩ መፍትሔ በመሆን ማክሮ ኤኮኖሚውን በረጅም ጊዜ ያረጋጋል የሚለውን እርምጃ መንግሥት ወስዷል፡፡ ፖለቲካ ብቻ አድርገን አንመልከተው፡፡ ኤኮኖሚና ፖለቲካ መቼም ተነጣጥለው አያውቁም፡፡ አሁን የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ምን እያደረገ ነው? ለምን? እንዴትና መቼ የዋጋ መረጋጋት ይፈጠራል? የሚሉትን አንስቶ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ድንጋጤና ግራ መጋባት ላይ ያለውን አምራች፣ አቅራቢና ሸማች ማረጋጋት መልካም ነው፡፡ ብድርን በተመለከተ ዩናይትድ ስቴትስ እንኳን የ35 ቲሪሊዮን ባለዕዳ ነች፡፡ በየዕለቱ ከ5 ቢሊዮን ዶላር ያህል ትበደራለች፡፡ ድሀ ሀገር ብድር ቢኖርበትና የመክፈል ችግር ቢያጋጥም አያስደንቅም፡፡ ከዚህ አንጻር የብር መዳከምና የዶላር መናር በሚሉትና በነጋዴዎች ስጋት ላይ አንዳንድ ነገሮች ልበል፡፡
ኢትዮጵያ እስከ ሐምሌ 22 ቀን 2016 (July 29, 2024 እኤአ) ድረስ ስትከተለው የነበረው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት በነፃ ገበያ ውድድር ላይ የተመሰረተ (floating) ሳይሆን፣ በመንግሥት ውሳኔ ጣልቃ ገብነት ያለበት በየዕለቱ ትንሽ በትንሽ (marginal) ዕድገት በሚያሳይ መልኩ (በከፊል ቁጥጥር) የሚካሄድ ነበር፡፡ ይህ ማለት የውጭ ምንዛሪው መነሻ በመንግሥት (ብሔራዊ ባንክ) ተወስኖ፣ በእጁ ባለው የውጭ ምንዛሪ ክምችት (stock) መጠንና የተጠቃሚዎችን (የአምራች፣ ነጋዴና ሌሎች ተጠቃሚዎች) ፍላጎት ለማስታረቅ ጥረት የሚደረግበት አካሄድ ነበር፡፡ ይህ አካሄድ የብርን የመግዛት አቅም በማይፈታተን አኳኋን የውጭ ምንዛሬ አቅም በአንጻራዊነት እየጨመረ የሚሄድበት አሰራር ስለነበር፣ የብር የመግዛት አቅም መዳከም ለአምራቾች፣ ለነጋዴችና ለሰፊው ሸማች በፍጥነት እንዲሰማቸው አላደረገም፡፡ የፈጠረው ነገር ቢኖር የውጭ ምንዛሪን ጥቁር ገበያ ነው፡፡ መንግሥት አሁን የወሰደውን እርምጃ ላለመውሰድ በብዙ የታገለ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ በመጨረሻ አልቻለም፡፡ ለምን የሚለውን ጥያቄ መመለስ በአጠቃላይ ወደ ማክሮ ኤኮኖሚው ድክመትና የወጪና የገቢ ንግድ አለመመጣጠን ሁኔታዎች ውስጥ ስለሚከተን ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ እዚያ ውስጥ አልገባም፡፡
አሁን ግን የኢትዮጵያ የብር ምንዛሪ ከዶላርና ከሌሎች የውጭ ገንዘቦች አንጻር በነፃ ገበያው እየተመራ በፍላጎትና አቅርቦት እንዲካሄድ ሥራ ተጀምሯል፡፡ በወቅቱ ሥራ ላይ እየዋለ የሚገኘው የውጪ ገንዘብ የምንዛሪ አስተዳደር የሚካሄደው እንደቀድሞው በመንግሥት ጣልቃ ገብነት ሳይሆን፣ በገበያው አቅርቦትና ፍላጎት (floating exchange rate) ነው፡፡ ያም ሆኖ መንግሥት የዜጎቹን ሸክም ለማቅለል በተለያዩ መንገዶች መጠነኛ ጣልቃ ገብነት አያደርግም ማለት ግን አይቻልም፡፡ ጣልቃ አይገቡም የሚባሉት እንደ ዩናይትድ ስቴትስ የበለጸጉ አገራት እንኳን አምራቾችን፣ ነጋዴዎችንና ሸማቾችን ለማገዝ/ለመደጎም ጣልቃ ይገባሉ (የሚቆጨው ሌሎች አገራት ዜጎቻቸውን እንዳይደጉሙ ጫና የሚፈጥሩ መሆናቸው ነው)፡፡
ነፃ ገበያ በስም ፍጹም ይምሰል እንጂ በተግባር ፍጹም ሆኖ አያውቅም፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ልትሰራበት የተያያዘችውን ዓይነት አሠራር ምዕራባውያንን ጨምሮ በርካታ አገራት የሚሰሩበት የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ነው፡፡ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ አዲስ የሚሆነው ለመጀመሪያ ጊዜ ስራ ላይ ሲያውሉት፣ በአጭር ጊዜ የተለያዩ የማክሮና የማይክሮ ቀውሶችን የሚያስከትል ስለሚመስል/ስለሚሆን ነው፡፡ ይህ አጠቃላይ እይታ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ሁኔታ የወቅቱ የውጪ ገንዘብ ምንዛሪ የገበያ አካሄድ (floating exchange rate) ሊያስከትል የሚችለው የገበያ ቀውስ ቀለል ሊል የሚችልባቸውን ባሕሪያዊና አስተዳደራዊ ሁኔታዎች/ምክንያቶች ሳልጠቅስ ጽሑፌን አልደመድምም ፡-
- ኢትዮጵያ ያልተነኩ የተፈጥሮ ሀብቶች ያላት አገር ናት፡፡ የተፈጥሮ ሀብቷን በተገቢው መንገድ ልትቆጣጠር ከቻለች የውጭ ምንዛሪ በአገሪቱ ኤኮኖሚ ላይ የሚፈጥረውን ጊዜያዊ ጫና ልትቋቋመው ትችላለች፡፡ ለምሳሌ፣ በኮንትሮባንድ የሚወጡ የአገሪቱን ሀብቶች (ወርቅ፣ የቁም እንስሳት፣ ቡና፣ ነዳጅ፣ ወዘተ) ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ መስራት ይኖርባታል፡፡
- ድሕነት መጥፎ ቢሆንም፣ የውጭ ምንዛሪው ተጽዕኖ ሊቀንስ ከሚችልባቸው አንዱ ድሕነት በአገሪቱ የተንሰራፋ መሆኑ አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ማንኛውም ሸቀጥ ፍላጎት ስላለ ብቻ አይሸጥም፡፡ ድሐው ፍላጎት ያለው ቢሆንም መግዛት ስለማይችል ሸቀጥ እንዲወደድ ምክንያት ለመሆን ቀዳሚ አይሆንም፡፡ ቀዳሚ ስፍራ የሚይዘው የአቅራቢውና የነጋዴው ስጋት በመሆኑ ስለ የውጪ ገንዘብ ምንዛሪ አካሄድ (floating exchange rate) አበክሮ ማስተማርና ማረጋጋት ወሳኝ ይሆናል፡፡
- ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎችን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት ትኩረት ማድረግ በውጭ ምንዛሪ ከውጭ የሚገቡትን ሸቀጦች ለመቀነስና በአገር ውስጥ ምርት በመሸፈን/በመተካት ዋጋን ለማርገብ/ለማረጋጋት ያስችላል፡፡ በአገር ውስጥ ለሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ማዋል ጥቅሙ የጎላ ነው፡፡ እዚያ ላይ አጥብቆ መስራት በረዥም ጊዜ የአገሪቱ ኤኮኖሚ ዕድገት ላይ ትልቅ ሚና አለው፡፡
- ወቅቱ የኢኖቬሽንና ተፈጥሮን የመጠበቅ ሳይንሳዊ አካሄድን የሚደግፍ ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ አገሪቱ ካልደረሰችበት ዕድገት ደረጃ በዘለለ ሁኔታ ዋጋቸው የናሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ወደ አገር ለማስገባት የሚካሄድውን አሠራር ማረቅ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንጻር፣ ፍራንኮ ቫሉታን በመፍቀድ የውጭ ምንዛሪ ያላቸው ማንኛውም ዜጎችና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተሸከርካሪን ጨምሮ ሌሎችን የፍጆታና የማምረቻ ዕቃዎች እንዲያስገቡ መፍቀድ የውጭ ምንዛሪ ጫናን ያቃልላል፡፡ ይህ ሂደት በተዘዋዋሪ መንገድ የውጭ መንዛሪ ክምችትን እንደ ማሳደግ የሚቆጠር ነው፡፡ ለምሳሌ፣ አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ዜጎቻቸው ለሚያስገቡት ዕቃ ለመንግሥት ተገቢውን ቀረጥ መክፈላቸውን እንጂ፣ እንደ ኢትዮጵያ በአከፋፋይ (dealers) በኩል ካልሆነ አይገባም እየተባለ የሚከለከል ሸቀጥ (መኪናን ጨምሮ) የለም፡፡ ከግብሩ መንግሥት ገቢውን ያሳድጋል፡፡ በአቅርቦትም ረገድ አስመጪዎች በአገሪቱ የውጪ ምንዛሪ ከሚያስመጡት ዕቃ (ተሸከርካሪንና ሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ጨምሮ) አቅርቦትን በማሳደግ ገበያን ያረጋጋል፣ ዋጋን ይቀንሳል፡፡ ውድድርን ይፈጥራል፡፡
- የውጪ ምንዛሪ አስተዳደር አንዱ ዓላማ ማክሮ ኤኮኖሚውን ማረጋጋት ነው፡፡ በቀላል አማርኛ ይህ ማለት የመንግሥት ገቢና ወጪን ማስተካከል፣ ምርትን በማሳደግ ዋጋን ማረጋጋት፣ የወጪና የገቢ ንግድን ሚዛን ማስተካከል፣ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት (foreign direct investment) በኤኮኖሚው መስክ እንዲጨምር ማድረግ፣ … የተረጋጋ የአገር ልማት ዕድገት እንዲኖር ማገዝ ማለት ነው፡፡ በጥቂቱ የገለጽኩት መሆኑን አስቡት፡፡ ይህ ሁሉ ተስተካክሎ መረጋጋት እስኪፈጠር ድረስ ግን “ሊነጋ ሲል ይጨልማል” እንደሚባለው ጊዜያዊ መንገጫገጭ እና ድንጋጤ ይኖራል – በአምራቹ፣ በነጋዴውና በሸማቹ፡፡ በዕውቀትና በምክንያታዊነት ላይ ባልተመሰረተ ድንጋጤና መሸበር በወሬ አማካኝነት ገበያውን ለማዋዠቅ አለመሞከር ለሁሉም ይበጃል፡፡ ወሬ ከሚፈጥረው ዋዣቂ ባሕሪ ይልቅ በመረጃ የተደገፈና የተረጋጋ ጠባይን መላበስ አዎንታዊ ውጤት አለው፡፡
- የወቅቱ የውጭ ምንዛሪ ጫና ለኢትዮጵያ ሊቀልል የሚችልባቸው ምክንያቶች፡–
- ስር የሰደደ ድሕነት መኖርና የመግዛት አቅም አለመኖር፣ የምንዛሪን መኖር አለመኖር ከቁብ አይቆጥርም (የመግዛት አቅም ያላቸው ብዙዎቹ፣ በአጋጣሚም ይሁን ህግና ፖለቲካ በድንገት ብር ያሳፈሳቸው ሰዎች ብቻ ናቸው ይባላል፡፡ ይህ ማረጋገጥ ይፈልጋል)፣
- ከድህነት በተጨማሪ፣ አመንቺ ሸማች ብዙ መሆን ጫናው እንዳይበረታና እንዳይቆይ ያግዛል፡፡ በአመዛኙ የኢትዮጵያ ሸማች አመንቺ ነው፡፡ ቆጣቢ እንጂ ያገኘውን ሁሉ አሟጦ ተጠቃሚ (consumer) አይደለም፡፡ እዚህ ላይ የዜጎች የቀጠባ ባሕልና የወቅቱ የቁጠባ ደረጃ ቢጠና መልካም ነው (ድሐ ምኑን ይቆጥባል እንዳትሉ ብቻ)፣
- የኢትዮጵያውን ባሕል የውጭ ምንዛሪው አስተዳደር ጫና እንዳይበረታባቸው የሚያግዝ እሴቶች አሉት፡፡ ዜጎች ከውጪ በሚገቡ የምግብ ዕቃዎችና ልብሶች ላይ የተመሰረቱ አይደሉም፡፡ ባሕላዊ ልብሶቻቸውን በዘመናዊነት ስም ችላ ብለው የበዓል ጊዜ ጌጥ አደረጉት እንጂ፣ በአገር ውስጥ ምርት ብቻ መስራትና ማጌጥ የሚያስችል ስነልቡናም ሆነ የማምረት ብቃት አላቸው፡፡ የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡
- የዋጋ አለመረጋጋቱ እስከ መቼ ድረስ እንደሚቆይ መተንበይ ቢያስቸግርም በአጭር ጊዜ ሊፈጠር የሚችለውን የገበያ አለመረጋጋት እያጉተመተመም ቢሆን ለመቻል/ለመቋቋም የኢትዮጵያ ሸማች ልዝብ ባሕሪ ያለው ነው፡፡ ይህም የውጭ ምንዛሪ ገበያው በአንጻራዊ አጭር ጊዜ እንዲረጋጋ አስተዋጽኦ ይኖረዋል በማለት መገመት ይቻላል፤
በአጭሩ በጠቀስኳቸውና በሌሎች ባልተጠቀሱ የኢትዮጵያውያን ኤኮኖሚያዊ ባሕሪያት ምክንያት፣ በውጭ ምንዛሪ ግብይት የማክሮ ኤኮኖሚ ማስተካከያ ውሳኔና የአሰራር ሂደት የስጋቱን ያህል ዘልቆ ጉዳት የማድረሱ ዕድል አጭር ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ አሜን ይሁንልን ማለት የሁላችንም መልካም ምኞት ቢሆን እመርጣለሁ፡፡ ሰላም ለሁላችን፡፡