በዘቅተኛ ደረጃ ላሉ የመንግስት ሠራተኞች የሶስት መቶ እጅ ወይም እጥፍ ደመወዝ መጨመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስታወቁ። የጥቁር ገበያው በሚመራው ንግድ ምንም ሳይፈጠር የዋጋ ጭማሪ ማድረግ አግባብ እንዳልሆነ አመልከቱ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት የየተጠቀሰውን የደመወዝ ጭማሪ ማድረጉን ያስታወቁት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን በተመለከተ ማብራሪያ ሲሰጡ ነው።
በማብራሪያቸው በሪፎርሙ በዋጋ ንረት ምክንያት ሊጎዱ ይችላሉ ወይም በትሩን ሊያሳርፍባቸው ይችላል ተብሎ ከተለዩት የመንግሥት ሠራተኞች ዋነኞቹ የጭማሪው ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እንዳሉት አሁን ላይ መንግስት በወር 1,500 ብር የሚከፈለው ሠራተኛ እንዳለው አመልክተዋል። የሚደረገው የደመወዝ ማሻሻያ ከ90 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ሃብት የሚጠይቅ እንደሆነ ገልጸዋል።
ወጪው ከፍተኛ ቢሆንም በምን መልኩ ታች ያለው 1,500 ብር የሚከፈለውን የመንግስት ሠራተኛ ደመወዙን በ300 እጥፍ እንዲያድግ መደረጉን ገልጸዋል።። ይህ ጭማሪ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ መሆኑንንም አውስተዋል። ከ25 ሺህ በላይ የሚከፈላቸውን ሰራተኞች ለጊዜው ታገሱን ብለዋል። ይህንን ሲሉ ጎን ለጎን ታች ያለውን ሰራተኛ ለማስቀደም እንጂ ከሃያ አምስት ሺህ ብር በላይ የሚከፈላቸው በቂ ገቢ ያገኛሉ ማለት እንዳልሆነ አመልክተዋል።
የተከማቸው ችግር የሚንጣት ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው መስክ ሪፎርም ማካሄዷን የሚነቅፉና የሚደግፉ አካላት አሉ። የሚነቅፉት ሙሉ በሙሉ ሲሆን የሚደግፉት ወገኖች ደግሞ ለውጡን ደግፈው ሊከሰቱ የሚችሉ ጊዜያዊ ችጎችን ማለፍ ግድ እንደሆነ ያመለክታሉ። ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዋ በአስደንጋጭ ንዝረት ውስጥ በመሆኑ፣ የውስጥ ችግርና ዓለም ላይ ያለው ቀውስ ተዳምሮ ኢኮኖሚዋን ይበልጥ እንዳናጋው ይገልሳሉ።
በሌላ ዜና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያ ባንኮች ህልውናን ያስቀጠለ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ትናንት በሰጡት ማብራሪያ አመልክተዋል። ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ዝግ አድርጋ መቆየቷ ለዘመናት ፈተና ውስጥ እንድትወድቅ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም የወጪ ንግዱ የሚፈለገውን ያህል የውጭ ምንዛሬ ማስገባት ተስኖት መቆየቱን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ ምርቶችም በኮንትሮባንድ እንዲወጡ ማድረጉን ነው ያነሱት፡፡ ኢትዮጵያ ባላት አቅም ልክ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻለችም ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የጥቁር ገበያ ስርዓት እንዲስፋፋ በማድረግ የዋጋ ንረት በዜጎች ላይ ጫና እንዲፈጥር ማድረጉን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡ ብከዚህ አኳያ ማሻሻያው በኢኮኖሚው ላይ የተጫኑ ስብራቶችን በማንሳት የተሻለ መነቃቃትን እንደሚፈጥር ጠቁመዋል፡፡ በተለይ የፋይናንስ ሴክተሩን ህልውና በማስቀጠል ረገድም ሚናው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ለአብነትም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቦንድ ግዥ ያሰባሰበውን ገንዘብ ብድራቸውን መመለስ ላልቻሉ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች ተደራሽ ሲያደርግ መቆየቱን አንስተዋል፡፡ ይህም ባንኩን ባለ እዳ እንደሚያደርገውና እዳውን መመለስ ካልቻለ ደግሞ መፍረሱ አይቀሬ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መፍረስ ኢትዮጵያውያን በባንኮች ላይ ያላቸውን እምነት እንደሚያሳጣ መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡ ይህም የሀገር ውስጥ ባንኮችን በገበያው የመቀጠል እድላቸውን አዳጋች ያደርገው እንደነበር ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡
መንግስት ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) እና ከዓለም ባንክ ጋር ባደረጋቸው ድርድሮች ካነሳቸው ጉዳዮች መካከል አንደኛው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የሚመለከት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በድርድሩም ባንኩ 700 ሚሊየን ዶላር የሚሆን ተጨማሪ ገንዘብ ከተቋማቱ ማግኘቱን አብራርተዋል፡፡ ይህም የባንኩን ህልውና ያስቀጠለ ከመሆኑም በላይ በኢትዮጵያ ልማት ላይ ያለውን ተሳትፎ ይበልጥ እንደሚያስቀጥልም ተናግረዋል፡፡