ክፉሰውዓመፃንብቻይሻል፤ስለዚህጨካኝመልአክይላክበታል።” መጽሐፈ ምሳሌ ቁጠር 17፡11
ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ – ነጻ አስተያየት
አቶ ነዓምን ዘለቀ “በፍትህ ላይ የተመሰረተ ሰላም ወይንስ “በሰላም” ሽፋን የአብይ አህመድ የተለመዱ ቧልቶች” በሚል ርዕስ ቦርከና ድኅረ ገጽ ላይ ያሳተመውን ጽሁፍ በጥሞና አነበብኩ። በጣም ገራሚ ነው፤ ኢትዮጵያ እንደ አቶ ነዓምን ያሉ የፖለቲካ “ጅምናስቲከኞች” የበዙባት ሃገር መሆኗን በተደጋጋሚ አይተናል። ግንቦት 7 የተባለው ቡድን፤ በኤርትራ መንግሥት ሥር ሆኜ “ለኢትዮጵያ እታገላለሁ” ባለበት የስላቅ ዘመን፤ ከአቶ ነዓምን ጋር ኢትዮ ሚድያ፤ አቡጊዳና፤ ናዝሬት በተባሉ ድኅረ ገፆች ላይ ከፍተኛ ክርክሮች አካሂደናል። በወቅቱም፤ ኢሳያስ አፈወርቂ የተባለ ጉድ፤ ለኢትዮጵያ የማይበጅ አደገኛ ሰው መሆኑንም በመጥቀስ በርካታ ጽሁፎችን አስነብብያለሁ። “ከታሪክ የማይማሩ ሰዎች፤ ታሪካዊ ስሕተትን ይደግማሉ” እንዲሉ፤ እነ ነዓምን ከኤርትራ በርሃ ትግል እንጀምራልን ያሉት፤ የኢሳያስ አፈወርቂ አረመኔ መንግስት እነ ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህንና ጓዶቻቸውን ቅርጥፍ አድርጎ በበላበት ወቅት መሆኑን ግምት ውስጥ ያላስገባ መሆኑ፤ እነዚህ ሰዎች የደከመ ስትራቴጂያዊ እሳቤ እንዳላቸው የሚጠቁም ነበር።
ከጅምሩ፤ ለኢሳያስ አፈወርቂ ደጅ መጥናት የጀመረው የወቅቱ የኢትዮጵያን ሪቪው አዘጋጅ የነበረው አቶ ኤልያስ ክፍሌ ነበር። ከእሱ ጋር በነበረኝ ሙግትም፤ ከኢሳያስ ጋር መሥራት እንደማያዋጣ በማያሻማ ሁኔታ ከነማስረጃ ሞግቼ ነበር። ይህ ክርክራችን ሳይቋጭ ነበር፤ የኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህና ጓዶቻቸው በሻዕብያ መታሰር የተሰማው። በወቅቱም “ብዬ ነበር ማለት” ጠቀሜታ የለውም በሚል ጽሁፍ፤ የተሰማኝን ሃዘንና በእነ ኤልያስ ክፍሌ አርቆ ማየት ድንክዬነት መበሳጨቴን ገልጬ ነበር። እነ ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ መጨረሻቸው ሳይታወቅ ነበር፤ ግንቦት ሰባት ከኤርትራ በርሃ ትግል ጀመርኩ ያለው። ምንም እንኳን መሳይ መኮንንና ተባባሪዎቹ በኢሳት ቴሌቪዥን አማካኝነት፤ ግንቦት 7 ያልነበረውን ወታደራዊ ኃይል እንደነበረው አድርጎ በፎቶ ሾፕ (Photo Shop) በተቀነባበር ምስል ለሕዝብ ቢያደርሱም፤ በመጨረሻ ሕዝቡ የተረዳው ነገር፤ ግንቦት 7 ምንም ወታደራዊ ኃይል ያልነበረው፤ አመራሩም ልክ እንደ ኦነግ አስመራ ቢራ ሲጋት የሚውልና፤ በአውሮፓና አሜሪካ እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ በመዘዋወር ከፈረደበት ዲያስፖራ ገንዘብ በማሰባሰብ የተጠመደ እንደነበር ለመረዳት ችለናል።
እነ ነዓምን ዘለቀ በወቅቱ በሌላቸው የወታደር ኃይል፤ “ጀግና ጀግና” በመጫወት ገንዘብ በማሰባሰብ ተግባር ላይ ተጠምደው፤ በኢሳትና በመሰሎቹ ፕሮፖጋንዳ ተሳስቶ ወደ ኤርትራ በርሃ ያቀናው ወጣት፤ ለውጡ እስከመጣበት ጊዜ ድረስ፤ ተስፋ ቆርጦ፤ የኤርትራን መንግሥት መሬት ሲኮተኩትና የጉልበት ሥራ ሲስራ ቆይቶ፤ ዶ/ር ዐብይ አሕመድ ባደረጉት የሰላም ጥሪ ወደ ሃገር ተመልሷል። ግንቦት 7 ወደ ሃገር ሲመለስም፤ እዚህ ግባ የማይባል ወታደራዊ ቁጥር ያልነበረው እንደነበር ሁሉም በአደባባይ ለማየት ችሏል። ትላንት የዚህ የሰላም ጥሪ ተቀባይና ተጠቃሚ ሆኖ ወደ ሃገሩ መግባት የቻለውና ከአራት ዓመታት በላይ የሥራአቱ ጋሻ ጃግሬ ሆኖ የቆየው ነዓምን ዘለቀ፤“በፍትህ ላይ የተመሰረተ ሰላም ወይንስ “በሰላም” ሽፋን የአብይ አህመድ የተለመዱ ቧልቶች” በሚል ርዕስ ክህደት የተመላበት፤ ጭብጥ የጎደለውና በውሸት የተሞላ ጽሁፉን ያስነበበን።
በጣም በሚገርም ሁኔታ፤ በአውሮፕ አቆጣጠር በታህሳስ 2022 (ከዓመት ተኩል ገደማ በፊት) አዲስ አበባ ኢሳት ቲቪ ላይ ቀርቦ “ተረኝነት የሚባል ነገር የለም፤ እኔ በግሌ ጥናት አድርግያለሁ ውሸት ነው” ሲል ዛሬ ኦሮሙማ እያለ ለሚያወግዘው የዶ/ር ዐብይ አሕመድ መንግሥት ምስክርነት የሰጠ ሰው ነው። እኔ በወቅቱ አዲስ አበባ ነበርኩ። ይህንን ስሠማ በውስጤ ከፍተኛ ቁጣ ነበር የፈጠረብኝ። በወቅቱ አዲስ አበባ ለሚገኘ የኢሳት ቴሌቪዥን ብደውልም ምላሽ አላገኘሁም። ሆኖም፤ በታህሳስ 9፣ 2022 (እአአ) “ጽንፈኛ ኦሮሞዎችና የጋረጡት አደጋ” በሚል ርዕስቦርካና ድኅረ ገጽ ላይ ባሳተምኩት ጽሁፍእንዲህ ብዬ ለአቶ ነዓምን ምላሽ የሚሆን ነገር ጽፌ ነበር።“በቅርቡ፤ አቶ ነዓምን ዘለቀ የአዲስ አበባ የኢሳት “ሞጋች” የተሰኘው መርሃ ግብር ላይ ቀርበው “ተረኝነት” የሚባለው የውሸት ትርከት ነው ማለታቸው አስገርሞኛል። እሳቸው ሰራሁት ባሉት ቀመር፤ በሥልጣን ላይ ያሉት ኦሮሞዎች፤ ከሌላው አይበልጡም ብለውናል። አቶ ነዓምን የሳቱት ዋና ነጥብ ግን፤ “ተረኝነቱን” የሚያሳየው፤ የኦሮሞ ባለሥልጣኖች የቁጥር መብዛት ሳይሆን፤ በሥልጣን ላይ ያሉትም ሆኑ በአንዳንድ የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ አንዳንድ ኦሮሞዎች፤ ለሁሉም ዜጋ እኩል የሆነ አገልግሎት አለመስጠታቸውና፤ አንድ አንድ የኦሮሞ ተወላጅ ተገልጋዮች ደግሞ “የኦሮሞ ዝርያ” ስላላቸው ብቻ፤ ከሌላው የተለየ አገልግሎትና ጥቅም ለማግኘት የሚሄዱበት “ሕገ ወጥ” ወይም ደንብ አልባ ድርጊት ነው። የተረኝነት ስሜቱ፤ በመንግሥት የተነደፈ ፖሊሲ ነው ለማለት የሚያስደፍር ነገር ባይኖርም፤ ይህንን የተረኝነት ስሜትና አድሎዋዊ አሰራር ግን በሕግ ለማገድ የሚደረግ እንቅስቃሴ ባለመኖሩ፤ “ኦሮሞነት” የተለየ ጥቅም የሚያሰጥ (privileged) ተደርጎ ለመወሰዱ ብዥታ የሚፈጥር ነገር የለም።”በወቅቱ ይህንን የፃፍኩት እኔው እራሴ አዲስ አበባ ያየሁትን ነገር ለመመስከርና የአቶ ነዓምን ገደብ የለሽ ለመንግስት የነበረውን ድጋፍ ለማሳየት ነበር። ዛሬ ይህ ሰው ነው፤ የዘር ብልቃጥ ውስጥ ገብቶ የለየለተ ጽንፍ ረግጦ፤ የኢትዮጵያን መንግሥት የሰላም ጥሪ የሚሳለቅበትና በሃሰትና በክህደት የተሞላ ትርከቱን ሊነግረን የሚፈልገው።
ነዓምን ከጅምሩ ከአሁኑ መንግሥት ጋር ያጋጨው፤ የፕሪቶርያ ስምምነት መደረጉ ነው። ነዓምንና ጉደኞቹ፤ ፍፁም የሆነ የትግሬ ጥላቻ እንዳለባቸው፤ በጦርነቱ ወቅት አይተናል። ኢሳት የተባለው ቡድን በወቅቱ፤ “ጦርነቱ ከ 5 ሚሊዮን ሕዝብ ጋር ነው፤ ትግሬና ወያኔ አይለይም፤ ከወያኔ ጋር ግንኙነት ይኑረውም አይኑረውም፤ ትግራዋይ ሁሉ በኮንሰንትሬሽን ካምፕ ውስጥ መቀመጥ አለበት” የሚል ጭካኔ የተመላበት መልዕክት ሲያስተላልፍ የነበረው። እን ነዓምን የዶ/ር ዐብይ መራሹን መንግሥት ይደግፉ የነበረው፤ ይህ መንግሥት ሕወሃትን ሙሉ ለሙሉ ያጠፋል በሚል ተስፋና ምኞት ነበር። መረጃው የለኝም እንጂ የነዚህ ሰዎች ፍላጎት አጠቃላይ የትግራይ ሕዝብ እንዲጠፋ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለኝም። እነ ነዓምን ትልቁ ያኮረፉበት ምክንያት የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት በመፈረሙ ነው።ጦርነቱ እንዲቀጥል ፍላጎታቸው ከነበረ አንዱ ነዓምን ነው።ምክንያቱም በጦርነት ያተርፉ ስለነበር ነው። ይህ ጦርነት ፈላጊ ሰው ነው እንግዲህ፤ “….“በሰላም” ሽፋን የአብይ አህመድ የተለመዱ ቧልቶች” ሊለን የሚፈልገው።“ማነሽና ማንን ታምያለሽ” ዓይነት ነገር ነው።
ነዓምን ዘለቀ በጽሁፉ “የዛሬ አመት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን በመቃወም በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ባደረገው ታሪካዊ ንግግር “የአማራ ሕዝብ ከብልጽግና ጋር ላይገናኝ ተፋቶአል” ብሎ ነበር። ዛሬ ያ እውነታ በእጥፍ ድርብ በጨመረበት ሁኔታ የአማራ ክልል ሆነ የኢትዮጵያን ችግሮች በዋዛ ፈዛዛ፣ በግርግር፣ በድለላና፣ በሽንገላ ለመፍታት መሞከር ሌላ ክሽፈት ነው። የአብይ አህመድና የአማራ ብልጽግና ሌላ የቀን ቅዠት።” (ድምቀትና ሰረዝ የተጨመረ) ይለናል። ነዓምን ለዚህ መላ ምቱ የሚያቀርብልን አንዳች መረጃ የለውም። ያኮረፉና በሃሰት ፕሮፖጋንዳ የተወናበዱ ጥቂት አማሮች ለመኖራቸው ምንም ጥርጥር የለውም፤ እነዚህ ግን 5% እንኳን የሚሆኑ አይደሉም። በተደጋጋሚ በአማራ ክልል፤ ከሕዝብ ጋር የተደረጉ ስብሰባዎችን እንዳየነው፤ ሕዝቡ ለዚህ ላኮረፈ ቡድን ድጋፍ የለውም። ከዚህ በተጨማሪ፤ በገፍ ለመከላከያ እጃቸውን እየሰጡ ያሉ ወጣቶች ድርጊት የሚያሳየው፤ ይህ ቡድን የነበረውን ጥቂት ድጋፍ እንኳ እያጣ መሆኑን ነው። በተለያዩ ቪድዮዎች እንዳየነው፤ የዚህ ቡድን ጀሌዎች “ካልደገፋችሁን እንገላችኋለን” እያሉ እያስፈራሩ ነው ከሕዝብ እንኳን ገንዘብ የሚዘርፉት። ብዙዎቹም በርሃብ መሰቃየታቸውንና እጅግ መቸገራቸውን ነው የሚነግሩን። ይህ ቡድን ምንም ዓይነት የሕዝብ ድጋፍ እንደሌለው የሚያሳብቅ ነው። ገንዘቡም ድጋፉም የሚመጣው ከጽንፈኛው ዲያስፖራ ነው። ከፊሉ ዲያስፖራ በሚሰማው ፕሮፖጋንዳ የተሸነፈ ሲሆን ከፊሉ ደግሞ በጥላቻ የተጠመቀ ነው። እንደተለመደው፤ ይህ ግጭት እንዳይቆም የሚፈልጉ የነዓምን ዘለቀ ዓይነት ሰዎች፤ የደም ንግዳቸውን ቀጥለዋል። ከተለመደው አጋራቸው ከኢሳያስ አፈወርቂ ጫማ ሥር ወድቀው በሚደረግላቸው ድጎማ ትላንት በኢሳት ዛሬ በኢሳን የለየለት ቅጥፈታቸውን እየነገሩን ነው።
መንግሥት በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ አቅርቧል። ከዛ ሁሉ ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ፤ ከሕወሃት ጋር ለሰላም ድርድር የተቀመጠ መንግሥት፤ ከሸኔ ጋር ለድርድር የተቀመጠ መንግሥት፤ በአማራ ክልል ካለው ቡድን ጋር ለሰላም ድርድር የማይቀመጥበት ምንም ምክንያት የለም። “ድርድር የሚባል ነገር የለም” የሚለው በጢሻ ውስጥ ተደብቆ ያለው “የፋኖ አመራር ነኝ” የሚለው ፈሪ ኃይል ነው። ድርድር እቀበላለሁ ካለ፤ እነ ነዓምን የሚልኩለት ዶላር ሊቀር ነው። የዚህ ቡድን ወደ ሰላም መምጣት የሚያሰጋቸው በዲያስፖራ ያሉ የደም ነጋዴዎች ብቻ ናቸው። የአማራ ሕዝብ ከብልጽግና ጋር ተፋቷል የሚለው ቅዠት የእነ ገዱ አንዳርጋቸው እና የነ ነዓምን ዘለቀ ቅዠት ነው። የአማራ ሕዝብ፤ የመንግሥት አጋር ሆኖ ለሰላም ተግቶ ሲሰራ እያየን ነው። ትምህርት ቤት ውስጥ ቦምብ እየወረወረ ተማሪ የሚገድል ቡድን፤ የአማራን ሕዝብ መሰረት ልማት የሚያወድም ቡድን፤ መምህራንን ለምን ታስተምራላችሁ የሚልና በእንብርክክ የሚያስኬድ ቡድን፤ የአማራን ሕዝብ “ግብር እያለ” የሚዘርፍ ቡድን፤ እርጉዝ ሳይቀር የአማራ ልጆች ላይ የነጭ ሽብር ዘመቻ የከፈተ ቡድን፤ ለአማራ ሕዝብ ቆሟል ማለትስ እንዴት ይቻላል? በተለያዩ አካባቢዎች፤ በተለይ ሸኔ የተባለው አረመኔ ቡድን፤ በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈጽመውን አሰቃቂ ግድያ ለማስቆም ተግቶ የሚታገለውን የመከላከያ ሰራዊት ከጀርባው እየወጋ ያለ፤ እራሱን ፋኖ ብሎ የሚጠራ ዝርክርክ ቡድን፤ የቆመው ለአማራ ሕዝብ ነው፤ ወይስ አመራሩን በዶላር ላሰከሩ፤ እቡይ መንፈሳቸውን ለማርካትና ገንዘብ በማሰባሰብ ኑሯቸውን ለሚያሻሽሉ፤ እንደ እነ ነዓምን ዘለቀና መሳይ መኮንን ያሉ ዋልታ ረገጥ ጽንፈኞች ነው? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል።
ብልጽግና ዛሬ በአማራ ክልል ከፍተኛ የልማት አውታሮችን እየገነባ ነው፡ ለሕዝቡ የሥራ እድል እየፈጠረ ነው። የአማራ ሕዝብ አለኝ የሚለውን ጥያቄ ለመፍታትም ጠንክሮ እየሰራ ነው። ትላንት በደሴ ላይ ያየነው እንኳን ትልቅ ምስክርነት ነው። እን ነዓምን እና ገዱ፤ የአማራ ሕዝብ ከብልጽግና ጋር “እኒዲፋታ ቢፈልጉም” የቀን ቅዠት ስለሆነባቸው ነው ሌት ተቀን የሰላም ጥረቱን የሚኮንኑት።”ነዓምን የሃሰት አቁማዳውን ሲፈታ እንዲህ ይላል “ባለፉት 11 ወራት በአማራ ክልል ህዝብ ላይ ሲደርስ የነበረው ግፍና በደል፣ ከሰላምና ከፍትህ ጋር የማይተዋወቀው የብልፅግና አገዛዝ በአማራ ህዝብ ላይ የጫነው የህልውና አደጋ ነው። በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በአማራው ላይ በተደጋጋሚ ሲፈጸም የቆየው ጭፍጨፋ እና ማፈናቀል አልበቃ ብሎ፣ በሸገርና በአዲስ አበባ ማንነት እየተመረጠ የሚደረጉ ጥቃቶች፣ ወከባዎች፣ ማፈናቀሎች፣ የጅምላ እስራቶች አልበቃ ብሎ፣ አማራውን “ሱሪህንም ትጥቅህንም እናስፈታለን” ብለው ክልሉን የጦርነት ቀጣና ያደረገው የአቢይ አህመድ መንግስት ያሰበውን እውን ማድረግ አቅቶች ተከታታይ ሽንፈትና ውርደት ሲደርስበት፣ “ሰላም” “ሰላም” የሚል ያልተቃኘ ዘፈን መዝፈን ጀምሯል።”
ለመሆኑ ይህንን ጦርነት ማን ጀመረው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል። ይህን ፋኖ የተባለውን ዝርክርክ ቡድን፤ እራሱን ለዓመጽ ያደራጅ የነበረው፤ ገና መከላከያ ሰራዊታችን ከሕወሃት ጋር ጦርነት እያደረገ በነበረበት ወቅት ነበር። እራሱ ፋኖ የተባለው ቡድን አመራር፤ ይህ ኃይል እራሱን ማደራጀት የጀመረው ከነሐሴ 2021 (እአአ) ጀምሮ በፍኖተ ሰላም እነደሆነ ነግሮናል። ይህ ኃይል መከላከያውን ከጀርባ እየወጋ፤ የመከላከያውን ክላሽ ሲነጥቅ እንደነበር እንደ ጀብዱ ያወራዋል። ነፍሳቸውን ይማርና፤ አቶ ግርማ የሺጥላም የተገደሉበት ምክንያት ይህንን ሃቅ በአደባባይ በመናገራቸው ነው።ይህ ኃይል ልክ እንደ ጡት አባቱ እንደ ወያኔ መከላከያውን ካምፕም ውስጥ እያለ ነበር የሚያጠቃው፤ ችግኝ ተክሎ የተመለሰን የመከላከያ ኃይል አጠቃ፤ ትጥቁን አስቀምጦ በካምፑ ውስጥ ኮስ ሲጫወት የነበረን ኃይል አጠቃ። የአማራን ሚሊሽያ፤ የአማራን ፖሊስ፤ የአማራን አድማ በታኝ በአሰቃቂ ሁኔታ ገደለ። እነ ዮሃንስ ቧ ያለው ከውስጥ ድጋፍ ይሰጡት እንደነበር ከተጠለፈው የስልክ ውይይታቸው መስማት ችለናል።
ይህ ኃይል የመከላከያ ሰራዊት ወደ አማራ ክልል እስከገባበት ጊዜ ድረስ በርካታ መሰረተ ልማቶችን አወደመ፤ ንፁሃንን ገደል፤ ይህንን ተቆጣጠርኩ ያንን ተቆጣጠርኩ ብሎ አወጀ። ልክ እንደ ወያኔም በሁለት ሳምንት አራት ኪሎ እገባለሁ ብሎ ደሰኮረ።ይህንን ያዩ እንደ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ ዓይነት ሰዎች ወደ ናፈቁት የአራት ክሎ በትረ መንግሥት ለመገስገስ ዘመቻውን ተቀላቀሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን የዶ/ር ዐብይ መንግሥት “ጦርነት አያዋጣም” እያለ ይለምን ነበር። የወያኔ ቡቱትዎች የሰላም ፍለጋው ፍርሃት እንደመሰላቸው ሁሉ፤ ይህ የወያኔ የሽንት ጨርቅ የሆነ ኃይልም የሰላም ፍላጎት ፍርሃት መስሎ ታየው፤ በትዕቢትም ፈነጨ። ያኔ ነው እነ ነዓምን “ተስፋቸው ለምልሞ” የለበሱት “የኢትዮጵያዊነት ጭምብል” ተገልጦ ወደ ዘር ብልቃጣቸው ውስጥ የገቡት። ትላንት ልዩ ኃይል የሚባል ነገር መኖር የለበትም እያሉ ላንቃቸው እስኪቆስል ሲለፍፉ የነበሩ ሰዎች፤ መንግሥት ልዩ ኃይል የሚባል አደረጃጀት ሕገ ወጥ ነው፤ ልዩ ኃይል ውስጥ ያለው ሰራዊት በሙሉ በመከላከያ ወይም ፖሊስ መአቀፍ ሥር መሆን አለበት ሲባል፤ የዩቲዩብ የደም ነጋዴው ምላሱን በእጥፍ ዘረጋ። ይህ አማራን ትጥቅ አስፈትቶ አማራን ለማስወጋት ነው የሚለውን ትርከት ሌት ተቀን ይተረትረው ጀመር። በዚህ የተወናብዱ ጥቂት የአማራ ልዩ ኃይል አባላት እራሱን “ፋኖ” ብሎ ወደ ሚጠራው ቡድን ተቀላቀሉ። ያኔ ነው እነ ነዓምን፤ በጽንፈኛው የአማራ አክቲቪስት የተተፉ ስለነበሩ፤ ከጳጳሱ የበለጠ ካቶሊክ ሆነው ለመቅረብ የሞከሩት።”ለዚህም ነው ዛሬ፤ በመብራት ተፈልጎ የማይገኘውን ዝርክርክ ኃይል “እያሸነፈ ነው ለማለት የሚዳዳቸው። “ደሃ በሕልሙ ቅቤ ባይጠጣ ኖር ንጣት ይገድለው ነበር” እንዲሉ፤ እነ ነዓምንም እንዲህ ካልደሰኮሩ፤ የገንዘብ መዋጮ መሰብሰብ አይችሉም።
ትእግስቱ ያለቀው መንግሥት፤ የመከላከያ ሰራዊቱን ወደ አማራ ክልል ሲልክ ግን፤ ያ ሁሉ ይደነፋ የነበረ ኃይል ማጠፊያው አጠረበት። ይዣለሁ ብሎ የነበረውን ከተማ ሁሉ ለቆ ፈረጠጠ። “የፍየል ወጠጤ ትከሻው ያበጠ ልቡ ያበጠበት፤ እንዋጋ ብሎ ከነብር ላከበት” የሚለውንም ስንኝ አስታወሰን። ትላንት መንግሥት ከሕወሃት ጋር የሰላም ድርድር ያደረገው፤ ሕወሃት መግቢያ መውጫው ጠፍቶት በጭንቀት በነበረበት ስዓት ነው። ያ የሰላም ድርድር ደግሞ ተጨማሪ የሰው ሕይወትና ንብረት እንዳይጠፋ ያደረገ ተገቢ ውሳኔ ነበር። እን ነዓምንን ያስኮረፈውም ይኸው ነው። መንግሥት ከሸኔ ጋር የሰላም ድርድር ማድረግ የፈለገው ሸኔ ውልቅልቁ ወጥቶ እርቃኑን በቀረበት ስዓት ነው። የሰላም ጥሪውም ተጨማሪ ሞት እንዳይኖርና ተጨማሪ የንብረት መውደም እንዳይኖር ነው። ይህም ተገቢ ነው። ዛሬም በአማራ ክልል እርስ በእርሱ እየተጋደለ ላለ ዝርክርክ ቡድን የሰላም ጥሪ እየቀረበ ያለው፤ “መንግሥት እየተሸነፈ ነው” በሚለው አስቂኝ ምክንያትም አይደለም። የወጣቶችን ሞትና የንብረት ጥፋት ለመቀነሰ ነው። በነገሬ ላይ፤ በርካታ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ በአማራ ክልል የመከላከያ ሰራዊት የሚጠቀመው ኃይል ካለው ኃይል 5% እንኳን አይሆንም፤ የበርካታም ከባድ መሳሪያዎቹንም ሆነ የአየር ጥቃት ገትቶ ነው። ይህ ኃይል ከምላሱ በቀር ምንም ኃይል እንደሌለው ነጋሪ የሚያሻው አይደለም። ነዓምን ዘለቀ ግን ‘ከተመቻቸ ቤቱ ውስጥ ሆኖ’ በዚህ መስኪን ወጣት ሥም ገንዘብ እየነገደ “የአብይ ሰራዊት” እየተንኮታኮተ ነው ይለናል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እንኳን ይህንን ዝርክርክ ኃይል ይቅርና፤ በትጥቅ እና በወታደር ብዛት ይበልጠው የነበረውን፤ ከፍተኛ የጦር ልምድ ያለውን ሰራዊትና የጦር መኮንኖች የያዘውን የሕወሃት ሰራዊት አይቀጡ ቅጣት የቀጣ ሰራዊት ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት እንዳየነውም፤ ረጅም ጊዜ ልምድ ያለውንና ከዚህ ዝርክርክ ኃይል የተሻለ ቁመና ያለውን የአልሸባብ ቡድን፤ በሚገርም ፍጥነትና ብቃት ድባቅ የመታ ኃይል ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላም ጥሪውን ያቀረበው እርስ በእርስ መገዳደል እንዲቆም ለማድረግ እንጂ፤ እንኳን ይህንን ከመሬት ብቅ ያላለ ዝርክርክ ኃይል ይቅርና፤ ለሌላም ጠንካራ ኃይል አይበገርም።
ነዓምን ዘለቀ፤ በጽሁፉ ያንፀባረቀው ክህደቱንና ውሸቱን ብቻ ሳይሆን፤ አላዋቂነቱንም ጭምር ነው። ስለፓርቲ ፖለቲካና በተለይም የፓርላመንት ሲስተምን (የአሰራር ዘይቤ) በቅጡ ሊገነዘብ የሚችል ሰው እንደሚረዳው፤ በምርጫ የሚያሸንፈው ፓርቲው እንጂ ግለሰብ አይደለም። በሕዝብ ተመርጦ ያሸነፈ ፓርቲ መሪውን ይመርጣል። በኢትዮጵያ በፌደራልም በክልልም ደረጃ የሕዝብ ድምጽ አግኝቶ የተመረጠው ፓርቲ ብልጽግና ነው። ዐብይ አሕመድን ጠቅላይ ሚኒስትር ያደረጋቸው ሕዝብ የመረጣቸው የብልጽግና የሕዝብ ተወካዮች እንጂ በቀጥታ የሕዝብ ምርጫ አይደለም። በተመሳሳይ መልኩም፤ በየክልሉ አመራሩን የሚመርጠው የክልሉ አሸናፊ ፓርቲ እንጂ ሕዝብ በቀጥታ መሪዎቹን አይመርጥም። ይህንን የፖለቲካ ሀሁ ያልተረዳው ናዓምን ዘለቀ፤ አረጋ ከበደን ሕዝብ አልመረጣቸውም ሊለን ይሞክራል።
ይህ ብቻ አይደለም፤ ነዓምን፤ “ፋኖ የተባለው ኃይል” አደረጃጀቱንና ከባባድ መሳርያን እንዴት እንዳገኘ ሊነግረን ይሞክራል። ሞርታሩና ዲሽቃው ከመከላከያ ሰራዊት የተማረከ ነው ሊለን ይዳዳዋል።ይህ ኃይል፤ ሞርታርና ዲሽቃ አለኝ ሲል ሰማን እንጂ በየትኛውም የጦርነት አውድ በነዚህ መሳሪያዎች ቆሞ ሲዋጋ አይተነው አናውቅም።ይህ በውሃ መጠጫ የፕላስቲክ ጠርሙስ 70 ወታደር የሚማርክ ኃይል ምን ይሳነዋል? “ለማያውቅሽ ታጠኚ ይሉ የለ። ዛሬ የአደባባይ ሚስጥር የሆነው፤ ወያኔም ሻእብያም ይህንን ዝርክርክ ኃይል እያስታጠቀና እያሰለጠነ መሆኑ ነው። ጦርነት ምን ማለት እንደሆነ ከሕወሃት ጋር በተደረገ ጦርነት አይተናል። በአማራ ክልል ያለው ለአቅመ ጦርነት ያልድረሰ የዝርክርክ ኃይሎች ትንኮሳ ነው። ነዓምን ዘለቀ የሚነግረን ውሸት እስክንድር ነጋ በቅርቡ ከ80%-90% ያለውን የአማራ ክልልን ተቆጣጥረነዋል ከሚለው ቅጥፈት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው። ይህ ኢሳት ይሰራው ከነበረ የግንቦት 7 የፎቶ ሾፕ ወታደር የተለየ አይደለም።ነዓምን በምናቡ የሚያይው “ጠንካራ የፋኖ ሰራዊት” መሬት ላይ የሌለና ነዓምንና መሰሎቹ በምኞት ፈረስ ላይ ተፈናጠው የሚጎመዡት የሕልም እንጀራ ነው።
የሚያሳዝነውና የሚያሳፍረው፤ ይህ ዝርክርክ ኃይል በዲያስፖራው በየኪሳቸው “ዘውድ” በያዙና እራሳቸውን አግዝፈው በሚያዩ እንደ ነዓምን ዓይነት ባሉ ድንክዬ ፖለቲከኞች ምክንያት እርስ በእርሱ ተከፋፍሎ እርስ በእርሱ እየተጋደለ ያለ ኃይል ነው። ምንም ዓይነት የአመራር ብቃት የሌለው ኃይል መሆኑን፤ እርስ በእርሱ እንኳን የማይናበብና እርስ በእርሱ ለመገዳደል እየተፈላለገ መሆኑንም እራሱ የሚነግረን ኃይል ነው። በቅርቡ ዘመድኩን በቀለ እንዳለው፤ ሕዝቡ ፋኖ መጣልኝ ይል ነበር አሁን ግን ፋኖ መጣብኝ እያለ ነው።ይህ ዝርክርክ ኃይል “ፋኖ” የሚለውን የተከበረ ሥም ያጎደፈ የሰፈር ዱርዬ ሆኗል። ታድያ ነዓምን ዘለቀ የትኛውን ኃይል ይዞ ነው “እያሸነፈ ያለ ኃይል” እንደሆነ ሊነግረን የሚፈልገው። ነዓምን ዘለቀ ከተኛበት የምኞት እንቅልፍ እራሱን ቢቀሰቅስ ምናልባት እውነቱ ፍንትው ብሎ ይታየው ይሆናል። ጦርነት ውስጥ መሳተፍ፤ አስመራ ተቀምጦ መሎቲ ቢራ የመጠጣት ያክል ቀላል አይደለም። መንግሥት አሁንም በግጭት የሚሞተውን የአማራ ወጣቶችን ሞት ለማስቀረት፤ ለሰላም እጁን ዘርግቷል። በእነ ጄነራል አበባው ታደሰ በኩልም ጥረት እየተደረገ ነው።ወጣቱ ነቅቶ፤ እራሱን ለሰላም ማዘጋጀት አለበት። ያልፈው አንድ ዓመት የሚነግረን ነገር፤ ይህ ኃይል ይዣለሁ ያላቸውን ከተሞች ሁሉ ከመልቀቁም ባሻገር፤ አንድ ስንዝር እንኳን መራመድ ያልቻለ ኃይል መሆኑን ነው። ይህ ኃይል ሕፃናትን እያገተ፤ አዛውንትን እየዘረፈና አንደግፍህም ያሉትን እየገደለ፤ የአማራን ክልል ትልቅ ኪሳራ ውስጥ የከተተ ኃይል ነው። የዲያስፖራው ጽንፈኛ የሚንጫጫው የራሱን ዕቡይ መንፈስ፤ የጥላቻና የቂሙን ስሜት ለማርካት ነው። የአንተን ሞት አይሞተም። ከዚህ ቀደም በኦሮሞ ጽንፈኞች ተሳስተው ጥፋት ላደረሱ የኦሮሞ ወጣቶች የነገርኩትን ልንገርህ። በአንተ ሞት፤ የዲያስፖራው ጽንፈኛ የሚጠጣው ማክያቶ እንኳን አይነቃነቅም። አገርህን አትውጋ፤ ሕዝብህን አታሳዝን። በአንድ ወቅት “ኢሳያስ አፈወርቂ ጭር ሲል አይወደም” የሚል ጽሁፍ አስነብቤ ነበር። እነ ነዓምንም ይህ የጌታቸው የኢሳያስ አፈውርቂ በሽታ የተጋባባቸው ይመስላል። እነ ነዓምን ጭር ሲል የማይወዱት የደም ነጋዴዎች ስለሆኑን ነው። የኢትዮጵያ ሰላም የእነሱ የገቢ ምንጭ መድረቅ ነው።
የኢትዮጵያችን ሰላም ይብዛ፤ ቸሩ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ።
ዝግጅት ክፍሉ – ጽሁፉ የታተመው አቶ ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ እንዲታተምላቸው በአድራሻችን በላኩት መሰረት ነው። በመሆኑም አሳቡ የሳቸው ብቻ መሆኑን የዝግጅት ክፍሉ ያስታውቃል። ጽሁፉ ምላሽ የተደረገላቸውና በስም የተጠቀሱት አቶ ነአምን አሳባቸውን እንድናትምላቸው ስላልጠየቁ ወይም በአድራሻ ባለመላካቸው አላተምንም። ምላሽ ካላቸው ግን ለማስተናገድ ዝግጁ ነን።