የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ላይ ባዋለው የውጭ ምንዛሪ መመሪያ ቁ.01/2016 መሠረት የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎችን ለመክፈት የሚፈልጉ የሥራ ፈቃድ ማመልከቻ እንዲያቀርቡ ጥሪ አቀርቧል። ።
በዚህም በገበያ ላይ ተመሥርተው የውጭ ምንዛሪ በጥሬ ገንዘብ መሸጥና መግዛት የሚፈልጉ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ማቋቋም የሚፈልጉ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የሌላ ሀገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን መስፈርት አሟልተው ወደ ሥራ መግባት እንደሚችሉ ተነግሯል። ።
አሠራሩ ተግባራዊ መደረጉ የውጭ ምንዛሪ ገበያን መሠረት ለማስፋትና ለማጠናከር እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ በጥሬ ገንዘብ ለመሸጥም ሆነ ለመግዛት የሚሹ ደንበኞችን ፍላጎት ለማርካትና የጥቁር ገበያውን ለማዳከም እንደሚረዳ እየተነገረ ነው ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህሩ አጥላው ዓለሙ (ዶ/ር) እንደሚገልጹት፤ የብሔራዊ ባንክ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎችን መክፈት ለሚፈልጉ አካላት ፍቃድ መስጠቱ ነፃ ገበያን በመፍጠር ጥቁር ገበያው ሕጋዊ ፍቃድ አግኝቶ እንዲሠራ ማድረግን ያለመ ነው። ።
ማንኛውም አቅም ያለው ግለሰብ ቢሮ በመክፈት ዶላርንም ሆነ ሌሎች የውጭ መገበያያዎችን መሸጥና መለወጥ መቻሉ ግልጽ በሆነ መንገድ የውጭ ምንዛሪ እንዲንቀሳቀስና ባንኮችም በቀጥታ የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኙ የሚያግዝ መሆኑንም ጠቁመዋል።
እንደ መምህር አጥላው ገለጻ፤ የውጭ ገንዘቦች በተለያየ ሁኔታ ውስጥ በሚመነዘሩበት ሁኔታም ኢኮኖሚውን መደገፋቸው አይቀሬ የነበረ ቢሆንም በሕጋዊ መንገድ ሲመጡ መንግሥት ከዘርፉ ማግኘት ያለበትን ገቢ እንዲያገኝ ያግዛል። ። እንዲሁም የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችም በድብቅ ከመሽሎክሎክ ይልቅ ሕጋዊ ሰውነት አግኝተው በነፃነት እንዲሠሩ ያደርጋል።
የጥቁር ገበያው ከመደበኛው የባንክ ምንዛሪ ተመን እጥፍ ሲመነዘር ኢኮኖሚውን በእጅጉ እየጎዳ እንደነበር የሚገልፁት አጥላው (ዶ/ር)፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በማበረታት የቴክኖሎጂ ሽግግርን፣ የመሠረተ ልማት እድገትንና የሥራ እድልን በማስፋት ለፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋፅዖ የሚያበረክት መሆኑ እሙን ቢሆንም የሠላም ጉዳይን ጨምሮ ለኢንቨስትመንት የሚሆን ምቹ ከባቢን መፍጠር ይፈልጋል ይላሉ።
የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች እንዲከፈቱ መፈቀዱ ትክክል ነው። ይህ አሠራር በኬንያ፣ ጅቡቲና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ላይ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል። ። አብዛኛውን ጊዜ ጥቁር ገበያ የሚንሰራፋው በመደበኛው የውጭ ምንዛሪ ተመንና በገበያው ፍላጎት መካከል ከፍተኛ ልዩነት ሲፈጠር ነው።መገበያያዎች በጥቁር ገበያ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት የአደንዛዥ ዕፅና የተለያዩ ወንጀሎች እንዲሠሩ ሲደረግ የነበረበት ሁኔታ አሁን የሚቀንስ ይሆናል ነው የሚሉት።
መምህር አጥላው፤ አሠራሩ ከሀገር ውጭ መውጣት የሚፈልጉ ግለሰቦችም ሆነ ነጋዴዎች በቀላሉ የውጭ ምንዛሪዎች እንዲያገኙ ቢያደርግም በተቃራኒው በሀገር ውስጥ ለሚኖሩ ዜጎች ጉዳቱ ያመዝናል፤ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ሁኔታ ብር እየረከሰ በመሆኑ ሁሉም ዶላር የመያዝ ዝንባሌ እንዲያድርበት በማድርግ ብርን የበለጠ አቅም ሊያሳጣው ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ይገልፃሉ።
ፈቃድ መሰጠት መጀመሩ መልካም ቢሆንም ውሳኔው ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት በቂ ተቀማጭ የውጭ ምንዛሪ መኖሩን ማረጋገጥና ኤክስፖርትን በማሳደግ የውጭ ምንዛሪ ምንጮችን ከመቼውም በበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ የሚያነሱት አጥላው (ዶ/ር)፤ ነገር ግን በቂ የውጭ ምንዛሪ ምንጮች ሳይኖሩ ወደዚህ አሠራር መግባቱ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ይጠቁማሉ።
በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ዳዊት ሀይሶ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ማንኛውንም የውጭ ምንዛሪ የሚፈልግ አካል እንደማንኛውም ቁስ ከገበያ ተደራድሮ መግዛት መቻሉ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ በአቅርቦትና ፍላጎት እንዲወሰን በማድረግና ለገበያው ነፃነትን በመስጠት ተወዳዳሪነትን ያሳድጋል። እንዲሁም መንግሥት ከጉዳዩ መውጣቱ የጥቁር ገበያውንና የባንኮችን የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተቀራራቢ ያደርገዋል ይላሉ። ።
በተጨማሪም ለአላስፈላጊ ተግባር ዶላር የሚከማችበትንም ሁኔታ ያስወግዳል የሚሉት ዳዊት (ዶ/ር)፤ ሕጋዊ ያልሆኑ የግብይት ሠንሠለቶችን በመበጠስ የጥቁር ገበያው እንዲጠፋ ከማድረግ ባለፈ በጥቁር ገበያውና በሕጋዊ የምንዛሪ ገበያው መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ እንደሚያግዝ ይገልጻሉ። ።
እንደ ምሑሩ ገለጻ፤ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሀገር ውስጥ ምርቶች ይልቅ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የመሸመት ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው። ነገር ግን ከዚህ በኋላ ምርቶችን ከውጭ ወደሀገር ውስጥ ለማስገባት ውድ የሚሆንበት አጋጣሚ የሚፈጠር በመሆኑ ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ያለው ፍላጎት እየቀነሰ ይመጣል። ። ይህም ሸማቹ ማኅበረሰብ ፊቱን ወደ ሀገር ውስጥ ምርቶች የሚያዞርበትን ዕድል ይፈጥራል።
እንዲሁም ምርቶችን ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገቡ አካላት በሀገር ውስጥ እንዲያመርቱ አዎንታዊ ጫናን በማሳደር ከውጭ ምርቶችን ከማስገባት ይልቅ ወደውጭ ምርቶችን የመላክ ፍላጎት እያደገ እንዲሄድ እንደሚያግዝ የሚገልጹት ዳዊት (ዶ/ር)፤ ከዚህ ቀደም መንግሥት በኢኮኖሚ ሥርዓት ሳይሆን በሚሰጠው ድጎማ የብር አቅም ጠንካራ ሆኖ የቆየ ነበር ቢሆንም አሁን ላይ ይህንን ማስቀጠል የማይቻልበት ሁኔታ ላይ መደረሱን ያክላሉ።
አሠራሩ ተግባራዊ መደረጉ ብርን ከመገበያያነት ያወጣዋል የሚሉ ስጋቶች እንዲስተዋሉ ያደረገ መሆኑን ጠቁመው፣ ነገር ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛው የመገበያያ ገንዘብ ብር ብቻ ነው። በመንግሥት ተወስኖ እስካልተቀየረ ድረስ በብር መገበያየት ግዴታ ነው። በብር አልገበያይም የሚል አካልም በሕግ ተጠያቂ ይሆናል ሲሉ ስጋቱ ተገቢነት እንደሌለው ይገልፃሉ።
እንደ ዳዊት (ዶ/ር) ማብራሪያ፤ አሁን የሽግግር ጊዜ በመሆኑ ለአጭር ጊዜ የሚቆዩ የዋጋ ጭማሪዎች እና በነጋዴው ማኅበረሰብ ላይ ሸቀጦችን የማሸሽ ሁኔታዎች እየታዩ በመሆናቸው ተገቢውን ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል። መንግሥት ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ማኅበረሰብ ለመደገፍ በመሠረታዊ ሸቀጦች ላይ ድጎማ የሚያደርግ ከሆነም ሽግግሩ ጤናማ ይሆናል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ፤ “የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች እንዲከፈቱ የሥራ ፈቃድ መስጠታችን የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስትመንት ለመክፈትና ዘርፉን በቀጣይ ዓመታት ከዓለም ምርጥ ተሞክሮዎችና አሠራሮች ጋር የተመጣጠነና ተወዳዳሪ ለማድረግ የጀመርነውን አዲስ ምዕራፍና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የጀመረውን ስትራቴጂካዊ ለውጥ ከግብ ለማድረስ በቁርጠኝነት መነሣሣቱን የሚያመለክት ነው” ማለታቸው የሚታወስ ነው።