“እውነት ለመናገር፣ ሁሉንም እውነት ለመናገር፣ ከእውነት በስተቀር ሌላ ላለመናገር ቃል እገባለሁ። ስለዚህም እግዚአብሄር እርዳኝ” በውርስ ቃሉ “I Swear to tell the truth, the Whole Truth, and nothing but the Truth, So Help Me God” ሲሉ በአሜሪካን ምስክር የሚሆኑ ወይም መንበር የሚሰጣቸው መሃላ ይፈጸማሉ። ይህ ሲከናወን በአብዛኛው ቀኝ እጅ በቅዱስ መጸሃፍ ላይ ይቀመጣል።
በዚህ እሳቤ መሰረት ሁሉንም እውነት አለመናገር መዋሸት እንደሆነ ይቆጠራል። ከፓሪስ የሚወጡ መረጃዎችም ሆኑ ከኢትዮጵያ በቅብብል የሚሰራጩ ዜናዎች ወይም ወሬዎች “ሁሉንም እውነት” አያሳዩም። ስለዚህ ከላይ በተቀመጠው ምህላ መሰረት ሲመዘን “ሁሉም እውነት አልተካተተም” ስለዚህ ህዝብ እየተዋሸ ነው። ይህ ደግሞ የሚሆነው ለምንመካበት አትሌቲክስ ከመቆርቆር አንጻር ሳይሆን ከግለሰቦች ፍላጎት አንጻር የሚቃኙ መረጃዎች እንዲተላለፉ ስለሚፈለግ ነው። ይህን ውድድሩ ሲፈጸም አረጋግጠናል።
ለምን ሁሉም እውነት አይቀርብም?
እውነት፣ ሙሉ እውነት የማይቀርበው የተቆራረጡ መረጃዎች ሆን ተብለው እንዲቀርቡ ስለሚፈለግ ነው። ይህ ደግሞ የሚሆነው በተወሰኑ ቡድኖች፣ ግለሰቦች ወይም አስተሳሰብ ላይ የተንጠለጠለ መረጃን ለህዝብ በሚፈልገው መልኩ ለማቅረብ ሲባል ነው።
በኢትዮጵያ ኩነትን፣ ታሪክን፣ አጋጣሚን፣ ሆን ተብሎ የሚፈጸም ሴራን፣ የታዋቂ ሰዎችን ንግግር፣ የመሪዎችን አንደበት ወዘተ … በመቆራረጥ ከአውዱ ውጪ ለሚፈለግ ዓላማ በማዋል ህዝብን ምሬት ውስጥ መክተት የተለመደ ነው። ህዝብን ሆድ አስብሶ በማበሳጨት የግል አጀንዳን ማስፈጸም አሁናዊ ፈሊጥ ሆኗል። ይህ መረን ከወጣው የኢትዮጵያ ፖለቲካና የፖለቲካ ቡድኖች ጀርባ ከሚነቀሳቀሱ የሚዳዎች አሰላለፍ የተቀዳ አካሄድ ከአዲስ አበባ እስከ ፓሪስ ኦሊምፒክ መድረክ ተዘርግቶ ይፋ ሆኗል።
ትንሽ እውነት እየተቆነጠረ፣ ሙሉ እውነቱ እየተደበቀ ሲቀርብልን የነበረው መረጃው ለሚፈለግ አጀንዳ እንዲውል ታስቦ እንጂ መረጃውን በቀናነት ለህዝብ ለማድረስ ታስቦ አይደለም። በዚህ መነሻ እየተቆነጠረ ሲቀርብ የነበረ መረጃ ሰፊ መተራመስ ፈጥሯል። ህዝብ ሆነ ተበሎ ግራ እንዲጋባ ተደርጓል። በዚህ ጎራ በለየና ስልጣንን አጀንዳ አድርጎ በተጀመረ የሚዲያ ዘመቻ አትሌቶች ሰለባ ሆነዋል። የራሱ የተፈጥሮ ችግር ካለበት የፌዴሬሽኑ የማይጸዳ አሰራር ጋር ተዳምሮ ኢትዮጵያን እንደ አገር ዋጋ አስከፍሏል።
አንዱ ጎታች፣ አንዱ ሳቢ ሆነው (PULL AND PUSH SYSTEM )የፈጠሩት ትርምስ በሚፈለገው ውጤት መሰረት ከተጠናቀቀ በሁዋላ ዘመቻው በተጀመረበት ሚዲያ ” ስልጣን ልቀቁልኝ” በሚል የአጀንዳው ዋና ግብ ተጠናቀቀ።
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የገፊና ጎታች ቅብብሎሽ ሴራ ኦሊምፒክ የተሳተፉ ተወዳዳሪዎችን ጎድቷል። አነካክቷቸዋል። የተለያዩ ጊዜያት የተነገሩ ንግግሮችን ሳይቀር በመገጣጠም አሁንም ለሚፈለገው ዓላማ ማቅረብ የሚዲያዎቻችን ባህል መስሏል። ይህ በሁሉም አውድ በሚባል ደረጃ ያለ አንዳች ነውር የሚተገበር፣ ተቆጪ የሌለው፣ ዒላማ የሆኑ ሰዎችን ወይም ተቋማትን ወይም ባለስልጣናትን ወይም ወዘተ እንደፈለጉ ለማነካከት የሚመረጥ መንገድ ነው። በዚህ አካሄድ በርካታ ሰዎች በደቦ ጥላቻ ታውጆባቸዋል። በደቦ ሚዛን የጎደለው ፍርድ ተፈርዶባቸዋል። እንዲህ ያለውን የጅምላ ፍርድ ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት በተግባር አይተናል። በቡድኖች ዓላማ ተቃኝተው የሚቋቋሙ ሚዲያዎች መረን የለቀቀ አካሄድ ሳቢያ በርካታ ጨዋ ዜጎች ተሸማቀው ዝምታን እንዲመርጡ ተገደዋል። በተመሳሳይ አትሌቶች ሳይቀሩ “ፈራን” በሚል ዝምታን መርጠዋል።
ይህ አደገኛ አካሄድ ያሳደረው ጫና በርካቶችን በፍርሃት አፍ ማዘጋቱ፣ ተደራጅተውና ተናበው ጥላቻን የሚያውጁትን “ጀግናችን፣ መተኪያ የሌለህ፣ አንበሳችን” የሚል ክብር የሚያጎናጽፍ ድምጾች ብቻ እንዲሰሙ አድርጓል። በዚሁ የተነሳ ስማቸው ገናና ሆኖ ዕለት ዕለት አየር ላይ እየወጡ የሚያውቁትንም የማያውቁትንም ሳይመርጡ የሚዘረግፉ ቁጥር ጨምሯል። አትርሱ ግማሽ እውነት ማቅረብ ወይም ሙሉ እውነትን አለማቅረብ መዋሸት ተደርጎ ስለሚታሰብ እየተዋሸን ስለመሆኑ እያወራን ነው። ስለዚህ ሁሉም እውነት የማይቀርበው፣ እንዲቀርብ የማይፈለገው ወይም ደግሞ ተቆርጦ ትንሽ እውነት የሚቀርበው መዋሸት አግባብ ሆኖ ስለነገሰ ነው። ወደ አትሌቲክሱ ልመለስ?
በአትሌቲክስ ውጤት ኪሳራ የተመዘገበው እንዴት ነው? የኪሳራው አቀራረብስ ጤነኛ ነው?
በፓሪስ ኦሊምፒክ እየተመዘገበ ያለው ውጤት ያስከፋል። በፓሪስ ብቻ ሳይሆን በሪዮና በቶኪዮ ኦሊምፒክም ስኬት አልተመዘገበም። የፓሪሱን ጨምሮ የተገኘው አንዳንድ ወርቅ ብቻ ነው። በሰሞኑ የፓሪስ ውድድር ማንም አገሩን የሚወድ ሁሉ ቅር ተሰኝቷል። በዚሁ ቅሬታ መነሻ ከፓሪስ የሚወጡ ናቸው የሚባሉና አገር ቤት የሚወረወሩ አሳቦችን ዝም ብሎ መቀበል ግድ ሆኗል።
በብስጭቱ ውስጥ ተቆርቋሪ መስለው ያለመታከት አሳብ የሚሰጡና የተራጁ በሚመስል መልኩ የሚሰራጩ መረጃዎች ውድቀቱን በአመክንዮ ለይተው የሚያሳዩ አይደሉም። ለውደቀቱ ተጠያቂዎችን ለይቶ አያቀርቡም። ዝም ብሎ በብስጭት ውስጥ ያለን ህዝብ በደንብ ለማበሳጨት ምሬትና ሙሾ ከማውረድ የዘለሉ አልነበሩም። ጉዳዩን ቀርበው የሚያውቁ እንደሚሉት ከውጤቱ መበላሸት በበለጠ የመረጃዎቹ መተራመስ ያበሳጫል ባይ ናቸው። “አንቱ” የሚባሉትን ጨምሮ በእንደዚህ ዓይነት የህሊና መደንደን ላይ ወድቀው ትርምስ ሲፈጥሩ ማየት ረግተው ነገሮችን ለሚመረመሩ ግራ ሆኖባቸዋል። በቀረቡትና በተረጩት ወሬዎች የኪሳራውን ምክንያት መረዳትም ሆነ ኪሳራ አድራሾችንም ለይቶ ማውጣት ያልተቻለው ለዚህ ነው።
የአትሌቲክስ ፌዴሬሽንን ፣ የኦሊምፒክ ኮሚቴን፣ የስፖርት ሚኒስትሩን፣ የተለያዩ ተዋንያኖችን፣ የህክምና ዲፓርትመንቱን ሚናና ሃላፊነት ሳይለዩ በጅምላ ሲቦካ የነበረው ወቀሳ ፍሬ አልባ፣ የተበላሸውን ውጤት ለማቃናት ምንም የማይፈይድ፣ ይልቁኑም የመቀመጫ ፍትጊያ መሆኑ የታየበት ሆኗል። ይህ ከውጤቱ ማሽቆልቆል በላይ አሳፋሪ ታሪክ ሆኖ የሚመዘገብ ሆኗል። ለመቀመጫ ሲባል ባራሳቸው አገር ሚዲያዎችና ባልደረቦች ዘመቻ የተደረገባቸው አትሌቶች ቢኖሩ የኢትዮጵያ አትሌቶች ብቻ ስለመሆናቸው ዓለም በሚመስክረው ደረጃ ታሪክ ሆኖ ይመዘገባል።
እውነታዎች በደምሳሳው
- በበርካታ ምክንያቶች በፓሪስ ኦሊምፒክ የተሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በገዛ አገሩ ሚዲያዎችና ሮጠው ባለፉ አንጋፋ ሯጮች ወንጀል ተፈጽሞበታል። ይህ ታሪክ ሆኖ ይመዘገባል።
- ፓሪስ ድረስ ስልክ እየተደወለ አትሌቶች እንዲያድሙ፣ እንዲለግሙ፣ መግለጫ እዲሰጡ ወዘተ በየቀኑ ጫና ይደረግባቸው ነበር።
- በገሃድ እንደታየው አትሌቶቻችን ከሶስት ሺህ መሰናክልና ማራቶን በቀር ተፎካካሪ መሆን አልቻሉም። ለምን አልቻሉም? በሚል የሚጠይቅ ሚዲያም ሆነ ባለሙያ አልተሰማም። ይህ የሆነው ለሚፈለገው የስልጣን ጥያቄ ስለማይጠቅም ነው
- ሚዛናዊና ችግሩን ለመንቀስ የሚይስችል የጅምላ ዘገባ የተመረጠው ህዝብን ሆድ ለማስባስና በምሬት የተደበቀውን አጀንዳ እንዲቀበል ለማድረግ ስለታሰበ ብቻ ነው።
- አብዛኛዎቹ ሚዲያዎች ያዘሏቸው አካላት ወይም ግለሰቦች አሉዋቸው። የእነዚሁ ግለሰቦች ዓላማ ተሸካሚ በመሆናቸው ነጻና ገለልተኛ አልነበሩም። በዚህ ሸውራራና የተንጋደደ አቋማቸው ሳቢያ ለማህበራዊ ሚዲያው ሲረጩለት የነበረው መረጃ ውጤቱ እንዲበላሽ አጋዥ ሆኗል።
ኃይሌና ገዛኸኝ
“ ራሴን በይፋ ከኦሎምፒክ ኮሚቴ አግልያለሁ “ ሲል ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ የተከለውን አጀንዳ የትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንትና የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢው አትሌት ገዛኸኝ አበራ “አትሌቲክሱ መጫወቻ ሆኗል” ሲል አጀበው። ብታምኑም ባታምኑም ይህ በመናበብና ልክ እንደ ፖለቲካው የገፊና ጎታች ስልት የተከናቅወነ ነው።
ኃይሌ ገብረስላሴና ገዛኸን አበራ ኦሊምፒክ ሊጀመር ቀናት ሲቀር ተናበው ዘመቻ ሲከፍቱ አትለቶች ላይ የስነልቦና ተጸዕኖ እንደሚያሳድር አይውቁም? ይህን ጽሁፍ የምታነቡ ሁሉ ይህ የስነ ልቦና ጫና ሊያደርስ እንደሚችል ለመረዳት ይከብዳችኋል? ዘመቻውን የከፈቱት ኃይሌ ገብረስላሴና ገዛኸን አበራ ከመሆናቸው አንጻር ጫናው ምን ያህል ከፍተኛ እንደሚሆን ግልጽ ሆኖ ሳለ ለምን በግዴለሽነት ገቡበት? ቀነኒሳም የዚሁ ዘመቻ አባል እንዲሆን ታስቦ ለቃለ ምልልስ ቢጋበዝም ዘመቻ ውስጥ ስለሌለበት ለታሰበው ቅስቀሳ ሊውል የሚችል መረጃ አልሰጠም እንጂ አበበ ግደይ የሚመራው ዘመቻ አያያዙ ክፉ ነበር።
የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ዋና ዓላማ የተጨበጠ መረጃ ለመፍትሄ አፈላላጊዎች፣ ከተራ ዘለፋና ድንፋታ በመውጣት ጉዳዩን ከስሩ መመልከት ለሚፈልጉ፣ ለመንግስት የሚመለከታቸው ሃላፊዎችና በቂ መረጃ ሳይዙ የአንድ ጉዳይ እውነትን ጫፍ ይዘው እሱኑ በማሳየት ሙሉውን እውነት ለሚደብቁን ሁሉ መረጃ መስጠት በመሆኑ መረጃውን ለማጉላት ስም ቢጠራ በሌላ እንዳይተረጎም ቀድመን አደራ እንላለን።
“ የተከበሩ ዶክተር አሸብር የትም ሂዱ ብለውናል የትም እንሄዳለን “
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል የነበረው ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በወረቀት ላይ ብቻ ከተካተትኩበት የኦሎምፒክ የኮሚቴ አባልነት በይፋ መልቀቄን ህዝብ ይወቅልኝ ሲል ያስታወቀው የኦሊምፒክ ውድድር በይፋ ሊጀመር ቀናት ሲቀሩት ነው። ሃያሌ “የግል ቤቱ” በሚባለው ሸገር ሬዲዮ ስፖርት ከፍለጊዜ የለኮሰው አጀንዳ ማሳረጊያውም እዛው ሸገር ስፖርት ስቱዲዮ ውስጥ ” ስልጣኑንን ይልቀቁልኝ” በሚል መድምደሚያ ነው።
የተከበሩ ዶክተር አሸብር የኢትዮጵያን ህዝብ የሚያከብሩ ከሆነ ስልጣኑን ለሌላ ይልቀቁ” ሲል ኃይሌ የታገለበትን የሚዲያ ትግል በስልጣን ጥያቄ ቋጨ። ዶክተር አሸብር ከለቀቁ ሃይሌ ምክትል ስለሆነ ይተካል። ስለዚህ ኃሌ ፋልጎቱ ስልጣን እንጂ ሌላ እንዳልሆነ ራሱ አረጋገጠ።
አሁን ያለው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል የስራ ዘመኑ ሊጠናቀቅ ስምንት ወይም ዘጠኝ ወራት እንደሚቀሩት የገለፀው ኃይሌ ” እኔ በወረቀት ላይ ብኖርም ጥዬ የወጣሁት ግን ከቶኪዮ ኦሎምፒክ በፊት ነው ” ብሎናል። ሻለቃ ሃይሌ ከዓመታት በፊት ከአባልነት መልቀቁን ለህዝብ ያላሳወቀው የባሰ ብጥብጥ ውስጥ እንዳይገባ በመስጋት መሆኑን አመልክቷል።
” በድጋሜ ያለ አግባብ ሌላ ምርጫ ማድረግ እና ሌላ ስህተት ግን ተቀባይነት የለውም ያንጊዜ ማድረግ የነበረብኝ ነው አሁን ከአባልነት መልቀቄን በይፋ ያደረኩት” ሲል ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ተናግሯል። ልብ በሉ የቶኪዮ ኦሊምፒክ ሲጠናቀቅ ኃይሌ ከኦሊምፒክ መውጣቱን ይፋ ቢያደርግ ብጥብጥ ይነሳል። የፓሪስ ኦሊምፒክ ሲጀመር እሳት መልኮስ ግን ችግር የለውም። ቅን ልብ ይላችሁ ፍረዱ የትኛው ወቅት ነበር ችግሮችን ለመፍታት አመቺ የነበረው? ወይም የሚሻለው? ይህን ጥያቄ ኃይሌ አንድ ቀን ጥሩ ሚዲያ ሲያገኝ ያብራራዋል።
ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በደሉን ለአዲሷ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ አቅርበ መልስ እየተጠበቀ መሆኑን አስረድቷል። ” የተከበሩ ዶክተር አሸብር የትም ሂዱ ብለውናል የትም እንሄዳለን ” ያለው ኃይሌ ” በኋላ ግን ለምን ሄዳችሁ ለምን ይህንን አደረጋችሁ እንዳይሉ እፈራለሁ ፣ እንኳን ይሄን 42 ኪ.ሜ በሞት እና በህይወት ውስጥ ሆነን ሮጠናል ” በማለት አስፈራርቷል።
የችግሩ መነሻ ስልጣን ስለመሆኑ ከዚህ በላይ ማሳያ የለም። ኃይሌ አስከብረዋለሁ የሚለውን መብቱን ባሻው መልክ ማስፈጸም ይችላል። ጥያቄው ግን ፍላጎቱን ለማሳካት አገርን በሚጎዳ፣ ከፖለቲካው ከተቀዳ የገፊና ጎታች ስልት የሚዲያ ዘመቻ ስልት ተግባራዊ ማድረጉ ላይ ነው። ሌላው ጥያቄ ይህ አካሄዱ ሆን ተብሎ ኦሊምፒክ በሚጀመርበት ዋዜማ ላይ መሆኑ ችግር ብቻ ሳይሆን ታዋቂነቱን ተጠቅሞ በአትሌቶች ላይ ሆን ብሎ ጫና መፍጠሩ፣ ጫናውም በመናበብ የተከናወነ መሆኑና በውጤቱም የባንዲራ ጥያቄ ስለሚያስከትል ነው። ከዚህም በላይ አትሌት ገዛኸኝ አበራንና በጦርነቱ ወቅት AWLO MEDIA የሚባል ቻናል አቋቁሞ ከነበረው አትሌት ገብረ እግዚአብሄር ጋር የፈጠረው ሰንሰለትና የሚዲያ ዘመቻ አንዱ ማሳያ ነው።
ኃይሌ በገሃድ የወንበር ጥያቄውን ካነሳ በሁዋላ የፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበርና የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ አስገራሚ መግለጫ ሰጠ። ” አትለቲክሱ መጫወቻ ሆኗል። የብቃት ችግር አለ” ሲል ሂሳብ አልባ መርዶ አረዳን።
አስቡት ገዘኸኝ የደራርቱ ምክትል ከመሆኑ በተጨማሪ የቴክኒክ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ ነው። የአትሌቶችን ስልጠና፣ የስልጠና ዕቅድ፣ ምርጫና የአስልጣኖች ምደባ የምመራና የሚያጸድቅ እሱ ሆኖ ሳለ ለማን ነው ” አትሌቲክሱ መጫወቻ ሆኗል፣ የብቃት ችግር አለ” ብሎ ያፓሪስ ውድድር ሊጀመር ቀናት ሲቀረው የሚናገረው? ይህን ሲል ቁጭ ብለው የሚያደምጡ ሚዲያዎች ” እራስህ ሃላፊ ሆነህ እየመራህ፣ ራስህ ምርጫ አካሂደህ፣ ራስህ አስልጣኝ መድበህ፣ ኦሊምፒክ ሲጀመር ይህን የምትለው በምን ድፈረት ነው? ችግር ካለ አራት ዓመት ለምን ተኛህ” ተብሎ አለመጠየቁ ጉዳዩ የሃይሌን ዘመቻ የመደገፍ አንዱ አካል በመሆኑ ምክንያት እንጂ ነገሩ ገዛኸኝ እጅ በአፍ የሚያስጭንና መደበቂያ የሚያሳጣ ስህተት ነበር። ከስህተትም በላይ የአንገት በላይ ጨዋነቱን የሚያሳይ፣ በዚህ ጭንቅላት የአትሌቲክስ የቴክኒክ ክፍል መመራቱ ደረት የሚያስደቃ ነው። እንደ አገር አሳፋሪም ጭምር ነው። ሚዲያውም አድምቶ መስራት የነበረበት ጉዳይ ቢኖር ይህ ብቻ ነበር።
የራሱን ሃላፊነትና ለሃላፊነቱ ብቁ አለመሆኑንን በአደባባይ የመሰከርው ገዛሃኝ አበራ ኃሌን ኦሊምፒክን እንዲመራ፣ እሱ ደርቱን ተክቶ ከፌዴሬሽኑን እንዲረከብ ተቀነባብሮ የተሰራውን የህልም ዕቅድ ዞሮ የሚበላው ስለመሆኑ እየተሰማ ነው።
ገዛኸን አበራ ደራርቱን ያጠቃ መስሎት በራሱ መቅመጫ ላይ ነዳጅ ነስንሶ አሁን ግምገማ እየጠበቀው ነው። ከኦሮሚያ ውክልና ያገኘው ገዛኸኝ አበራ በጥቅምት በሚካሄደው አዲስ ምርጫ ኦሮሚያን ስለመወከሉ ከወዲሁ ጥያቄ እየተነሳበት ነው። እስካሁን ምንም ዓይነት የፌዴሬሽን ውክልና የሌው ኃይሌም ከኦሮሚያ የመወከል ዕድል የለውም። እናም ዘመቻው በዚህ ተጠናቋል።
ለማጠቃለያ
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፊዴሬሽን ውስጥ ጥቅል የአሰራር ችግር ነበር። አለ። በዚህ አያያዙ ወደፊትም ችግሮቹ አይቀረፉም። ኦሊምፒክ ኮሜቴ ውስጥ በተመሳሳይ ችግር አለ። ማንም አይክድም። ከዚህ በፊት የነበሩት ችግሮች አሁን ፓሪስ ላይ ከታየው የሚብሱ፣ ለጆሮ የሚያሙና ለማመን የሚያስቸግሩ ነበሩ። ወቅቱ ሚዲያ የተቆለፈበትና እንደዛሬው ክፍት ያልሆነበት ስለነበር እንደዛሬው አልተጯጯኸም እንጂ የችግሩ ስፋትና ግዝፈት ጭራሽ ከዛሬው ጋር አይወዳደርም።
እናም ኦሊምፒክን፣ አትለቲክስ ፌዴሬሽንን፣ ስፕርት ሚኒስርቲሪውን በልቶ ለመውቀስ ከበቂ በላይ ምክንያት እያለ ቆርጦና በጥሶ፣ የቢሆን ትንተና ውስጥ በመግባት ስዎችን አዋርዶና ጥቂት እውነታዎችን አጋኖ ማቅረብ አጥፊዎችን አሸናፊ ማድረግ ነው። በተለይም መፍትሄ ሊፈልገለት ለሚገባው አትሌቲክስ ስፖርት ፋይዳ የለውም። ጨዋ አካሄድም አይደለም።
ችግሩን በየወቅቱ ለመቅረፍ አትሌቶች አምጸዋል። አዲስ ማህበር አቋቁመው ኃይሌ ሊቀመበር ከሆነ በሁዋላ መልሶ አፍርሶታል። ድጋሚ የአትሌቲክ ፕሬዚዳንት ሆኖ ከተመረጠ በሁዋላ ሁለት ዓመታት ምንም ለውጥ ሳያደርግ ጥሎ ወጥቷል። ለምን? አድምቶ የጠየቀው የለም።
በሚስቱ እልፍነሽ ዓለሙ ላይ በተፈጸመ ግፍ በቤቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቶ የነበረው አትሌት ገዘኸኝ አበራ፣ ግልጽ አሰራር ዘርግቶ ቤቱን ለማጽዳት የቴክኒክ ክፍሉ ቁልፍ እጁ ላይ ቢቀመጥም አቅም ስለሌለው አልቻለም። “አልቻልኩም በቃኝ” ከማለት ይልቅ ራሱ ራሱን ሲከስ ተሰምቷል። ራሱ የራሱን የስራ ሃላፊነት ጠቅሶ ወንጅሏል።
ገዛኸን የሰራው ፋወል ብዙ ነው። ለምሳሌ በፓሪስ አቀባበል እንዳልተደርገለትና የመግቢያ ሰነድ እንዳልነበረው ከፓሪስ ሲናገር “የኢትዮጵያ ህዝብ ካሳ እፍለጋለሁ። ተባሬያለሁ። ሞራሌ ተነክቷል” ነበር ያለው። ሚዲያውም በቅብብል ያስጮኸው ይህንኑ የተሸረፈ፣ እውነት ሙሉ በሙሉ ያልቀረበበት መረጃ ነበር። ገዛኸኝ አራት ጊዜ ጉዞ ሰርዟል። የሂደው ሳያሳውቅ ነው። ደራቱ ግን ተቀብላዋለች የፎቶ ማስረጃ አለ። በተያዘለት ጊዜ ካልተገኘ አክሪዲቴሽኑ በራኡ ከሲስተም እንደሚሰረዝ አልተገለጸም። ይህ ሁሉ የተቀነባበረ ዘመቻ ስለመኖሩ ያሳያል። ስልክ እየውተደወለ አትሎቶችን ከማመስ በተጨማሪ ማለት ነው።
ስልጣንን እንጂ መሰረታዊ ለውጥን አንግቦ የሚንቀሳቀሱ ጨዋ አካላት ባለመኖራቸው አትሌቲክሳችን ባለበት እየረገጠ ነው። በውስን ልዩ ስጦታ ያላቸው አትሌቶች ትከሻ ተሸፍኖ የኖረው አትሌቲክሳችን ብቁ አሰልጣኞችና ዘመኑን የሚዋጁ ባለውሙያዎች ባለማፍራቱ በውድድር ወቅት የሚዘባረቅ ቡድን ለማየት ተገደናል። ሰዓት ያጠለቀ ሁሉ ራሱ አስልጣጭ አድርጎ እየሾመ በአደባባይ አፍረናል። ሳንቲም ለቃሚ ማናጀሮች ፌዴሬሽኑ ውስጥ ዘልቀው በመግባታቸው ወጥ አሰራርና ብሄራዊ ቡድን እንዳይኖረን አድፍርገው አፈራርሰውናል።
ኃይሌ ይህን ከማስተካከል እድሉን ከአንዴም ሁለቴ ቢያገኝም እሱ በሚያውቀው ምክንያት ጥሎ ሸሽቷል። ዛሬ ደግሞ ምክንያቱ ግልጽ ባልሆነ የስልጣን ጥያቄ የፓሪስ ኦሊምፒክ ሲጀመር ዘመቻ ከፍቶ የትርምሱ ቁልፍ ያዥ ሆኖ ሰንብቷል። ለውጥና ሪፎርም እንዴት እንደሚደረግ የሚያሳዩና የሚያመላክቱ የሚናፍቀው አትሌቲክሳችን ይጮሃል። ኃይሌና ገዘኸኝ የፈጠሩት ጥምረት በፓሪስ ኦሊምፒክ ተወዳዳሪዎች ላይ የፈጠረ የድብርት ደመና በታሪክ የሚዘከር እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።
በኦሊምፒክ ኮሚቴ ዙሪያ ያለውን ሃቅ ይዤ እመለሳለሁ