“የአደዋው ቡድን” የሚባለው የትህነግ አመራር አካል እንደሆኑ የሚነገርላቸው ከሻዕቢያ ጋር አብሮ ለመስራትና መንግስትን ለመጣል ዕቅድ ማውጣታቸው ከወራት በፊት ሲገለጽ መቆየቱ ይታወሳል። ስማቸው ተጠቅሶ አስመራ እንደሚመላለሱ የተነገረባቸው የአድዋው ቡድን ወገን የሆኑ የትህነግ ሰው ብቻ ሳይሆኑ ዶክተር ደብረ ጽዮን የሚመሩት ቡድን የዚሁ ግንኙነት አካል መሆኑ መረጃ ወጥቷል።

ይህ ውስጥ ውስጡን ሲብላላ የቆየ ጉዳይ ትህነግ በግልጽ ሁለት ቦታ መከፈሉ ይፋ ከሆነ በሁዋላ በከፍተኛ አመራሮች ደረጃ ይፋ እየሆነ ነው። የትህነግ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ ” የህዝብ የሰላም ፍላጎት ወደጎን በመተው፣ ለግዜው ማን መሆኑ በግልፅ ከማይታወቅ እና እነሱ ደጀን ይሆነናል ያሉት የውጭ ኃይል ተማምነህ፥ ያልሆነ ዝግጅት፣ የተወሰነ ግለሰቦች ጠባብ ፍላጎት ሲባል የትግራይ ህዝብን ዳግም ወደ አደጋ ለመዳረግ የሚደረግ እንቅሰቃሴ ነው እየተካሄደ ያለው ” ሲሉ እነ ዶክተር ደብረ ጽዮን የሚመሩት ቡድን እያደርገ ያለውን እንቅስቃሴ ገልጠዋል። አካሄዱ እንደማይጠቅምም አመልክተዋል።
የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር መሪና እና የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ ከአንድ ሺህ በላይ ተሰብሳቢ በተሳተፈበት የአንድ ቀን ስብሰባ፣ በአመራሮች መካከል ያለው ልዩነት ጉባኤ ይደረግ አይደረግ የሚል ሳይሆን እንዴት ይደረግ የሚል መሆኑን ገልጸዋል።
የእውቅናው ጉዳይ ከፌደራል መንግስት ጋር በሚደረግ ፖለቲካዊ ውይይት መፍትሔ እንዲገኝለት ሁሉም ተግባብቶ እያለ፥ የተወሰኑ ግለሰቦች በጎን በመንቀሳቀስ ወደ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ወረቀት በማስገባት ከመግባባቱ ያፈነገጠ ስራ ማከናወናቸውን በመጥቀስ የልዩነቱን መነሻ ያስረዱት አቶ ጌታቸው ” የተፈጠረው አለመግባባትና ክፍፍል፥ የፕሪቶሪያ ስምምነት ያለባለቤት የሚቀርበት ዕድል የሚፈጥር ነው። ይህን አደጋ ለመቀልበስ ጥረት ይደረጋል” ብለዋል።
“ሁኔታው የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ሂደት ባለቤት አልባ ሊያደርግ የሚችል ነው። ይህን ጉባኤ የፌደራል መንግስት አልተቀበለውም። ፌደራል አለመቀበሉ የራሱ ትርጉም አለው። ዋናው ነገር ግን በፓርቲያችን ውስጥ አንድነት እና መቀራረብ፣ በሐሳቦች ዙርያ አብሮ መስራት ሳይሆን መከፋፈል እና መራራቅ የሚያስከትል አደገኛ መድረክ ነው” ሲሉ ስጋታቸውን አመልክተዋል።
የተፈጠረው ልዩነት አስጊና ‘ጠላቶች’ ሊጠቀሙበት የሚችል መሆኑን በማስጠንቀቂያ መልክ አሳስበው ስማቸውን ያልጠቀሷቸው የውጭ ሃይሎችን ተማምኖ የሚሰራ ስራ መሆኑን በመጠቆም አካሄዱ ክልሉን ወደ ጦርነት የሚያስገባ ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል።
በዶክተር ደብረጽዮን የሚመራው የትህነግ ወገን ጠቅላላ ጉባኤ ቃል አቀባይ አቶ አማኑኤል አሰፋ የአቶ ጌታቸውን ንግግር ” ይህ አገላለጽ ትክክል አይደለም” በሚል ይቃወሙና “ትህነግ እምነቱ በትግራይ ሕዝብ፣ በፕሪቶሪያው የሰላም ሥምምነት በተቋማዊ አሰራር ነው። ሁሉም ችግሮች በሰላማዊ ፖለቲካዊ መንገድ ይፈታሉ ብለን ነው የምናምነው ” ሲሉ ወደ ጦርነት የሚያስገባ ነገር እንደሌለ አመልክተዋል።
በምህረት ከእስር የተፈቱት አቶ ስብሃት ነጋ አሜሪካ ሆነው ትህነግ መጠለፉን ጠሰው መናገራቸው ይታወሳል። እሳቸው በስፋት አብራተው እንዳስረዱት ትህነግ ግማሽ አካሉ ብልጽግና ሆኗል።
ዶክተር ደብርጽዮን ትግራይን እንዲመሩ የሚያስችላቸውን ምደባ አድርገው ለመንግስት ሲልኩ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንደማይቀበሉት ማሳወቃቸውን ተከትሎ አቶ ጌታቸው መሪ መደረጋቸው ሌላ የትህነግ ቡድን እንዲቋቋም ምክንያት እንደሆነ ቢነገርም፣ ጉዳዩን ከስር መሰረቱ የሚያውቁ እንደሚሉት ልዩነቱ የተፈጠረው ከሻዕቢያ ጋር በተፈጠረ ንክኪ ነው።
ከሰላም ስምምነቱ በሁዋላ ከሻዕቢያ ጋር መስራትና መንግስትን መጣል አለብን የሚሉት ወገኖች አማራ ክልል በተለይም ጎጃም ውስጥ ከሚንቀሳቀስው የፋኖ ተዋጊዎች ጋር ህብረት እንዳላቸው የሚያረጋግጡ መረጃዎች አሉ። ይህ ሻዕቢያ እንደሚመራው የሚነገርለት የአማራ ክልል ቀውስ ከእነ ደብረጽዮን ሃይል ጋር አቆራኝቶ ለማስኬድ የሚደረገውን ሁሉ መንግስት እንደሚያውቀውና ዝግጅት እንዳደርገበት ይገልጻሉ።
ከእነ ዶክተር ደብረጽዮን ወገን ስለሚታሙበት ጉዳይ ምንም ምላሽ ሲሰጥ አይሰማም። ይሁን እንጂ የእነ አቶ ጌታቸው ቡድን ባካሄደው የአንድ ቀን ስብሰባ ባወጣው ባለ አስር ነጥብ የአቋም መግለጫ ” ሰላም አማራጭ የሌለው አማራጭ መሆኑ በመቀበልና በመረዳት ማንኛውም ወደ ግጭትና ጦርነት የሚመራ የውስጥና የውጭ ተንኮል በፅኑ እንቃወማለን ” ብሏል።
በዚሁ በአቋም መግለጫው በትህነግ ሊቀ መንበር ዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው የ14ኛው ጉባኤ ህጋዊነ እንዳልሆነ ብስፋት ቀርቧል። ” ተደናግረው በጉባኤው በመሳተፍ ላይ የሚገኙት የህወሓት አባላት ወደ ቀልባቸው በመመለስ ከህዝባቸው ጎን እንዲሰለፉ ” ሲል ጥሪም አቅርቧ።
በሌላም በኩል በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኘው የክልሉ ተወላጅ ፣ የድርጅቱ አባልና ደጋፊ ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ፣ ማህበራት ፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ምርጫ ተካሂዶ መንግስት እስኪቋቋም ድረስ ጊዚያዊ አስተዳደሩ ደግፈው እንዲቆሙ መግለጫው ጥሪ አቅርቧል።
” የተከበራችሁ የትግራይ የፀጥታ ሃይሎች በድርጅታችን ውስጥ የተፈጠረው የሃሳብ ልዩነት እንደ ሁሉ ጊዜ በጥሞና በማየት በማያዳላ መንገድ የህዝቡ ፀጥታና ሰላም ማስከበር ይገባል ” ያለው የውይይቱ ተሳታፊዎች መግለጫ የፀጥታ ሃይሎች አሁን የያዙት የማያዳላ አቋም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ሲል አሳስቧል።
“ትህነግን ማዳን” በሚለው ስብሰባ አስራ ሰባት የሚጠጉ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም የቁጥጥር ኮሚሽን አባላት ተሳታፊዎች መናቸውን በስፍራው የተገኙ የውጭ አገር ሚዲያዎች ገልጸዋል።
ይህ ስብሰባ የተካሄደው የትህነግ ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ቡድን እያካሄደ ባለው ጉባኤ፤ አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ አስራ ሰባት የሚጠጉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ከፓርቲው ከፍተኛ አመራርነት ካገደ በኋላ ነው።
በጉባኤው ተሳታፊ ያልሆኑ አባላት ከከፍተኛ የፓርቲ ኃላፊነታቸው ታግደዋል መባሉን ተከትሎ አቶ ጌታቸው ረዳ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በድርጅቱ ሊቀ-መንበር (ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል) የሚመራው ቡድን የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሥልጣን ለመንጠቅ ሙከራ ሊያደርግ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ቢቢሲ መዘገቡ አይዘነጋም።
ትህነግ በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ “ቅጽበታዊ” ያለውን ጥቃት ከሰነዘረ በሁዋላ በተጀመረው ጦርነት ሻዕቢያ ክፍተቱን ተጠቅሞ የጦር ወንጀል መፈጸሙ አይዘነጋም። ከተራ የቤት ቁሳቁስ ጀምሮ እስጀ ጀፍተና ማሽነሪዎችና የሆድፒታል ቁሶች ዘርፎ ማጋዙ ይታወሳል። ለጊዜው በዳታና በአሃዝ ያልተገለጸ ቁሳዊና ሰብአዊ ጉዳት አድርሷል። በርካታ ሴቶችን ህጻናትን ሳይቀር ደፍሯል። በቅናት ትግራይን አፈራሯታል። ይህን የሚያውቁ እነ ዶክተር ደብረጽዮን እያደረጉ ያሉትን የውስጥ ለውስጥ ስምምነት አይቀበሉም። እንዳውም ቁጣቸው የከረረ ነው።
ትግራይን ዳግም ወደ ጦርነት የሚያስገባ ተጨባጭ ስጋት አለ ?
” ይሄ የአንድ ድርጅት ጉዳይ ነው። ወደ ጦርነት የሚያስገባ ምንም ነገር የለም ” – አቶ አማኑኤል አሰፋ
በሊቀ – መንበሩ ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው የ14ኛው የህወሓት ጉባኤ ቃል አቀባይ አማኑኤል አሰፋ ፤ አሁን ባለው ሁኔታ ወደ ጦርነት የሚያስገባ ነገር የለም ብለዋል።
አቶ አማኑኤል ፥ ” በአንድ አዳራሽ ውስጥ ገብቶ ተሰብስቦ ስለ አንድ ድርጅት ውስጣዊ ጉዳዮች መወሰን ወደ ጦርነት የሚያስገባ አንድም ምክንያት የለም ” ሲሉ ተናግረዋል።
” ጦርነት በዚህን ያህል ኢትዮጵያ ውስጥ ርካሽ አይደለም ” ብለዋል።
” ጦርነት አስፈላጊ ሆኖ አማራጭ ቢሆን ኖሮ ትግራይ ውስጥ ያሉት ችግሮች ሌላ ጦርነት ይጋብዙ ነበር ” ሲሉ ተደምጠዋል።
እንዚህ ችግሮች ለተፈጸሙ ወንጀሎች የተጠያቂነት አለመረጋገጥ ፣ በህገመንግስት ላይ የተቀመጠው የክልሉ ግዛት አለመመለስ ፣ የተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው አለመመለስ ፣ የኢኮኖሚ ቀውስ …ወዘተ እንደሆኑ ነው የጠቆሙት።
” ዛሬም ትግራይ ውስጥ ብዙ ችግሮች አሉ። ህዝቡ መስእዋትነት እየከፈለባቸው ነው ግን የተጀመረውን የሰላም ተስፋ ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዲሸጋገር ህዝቡ መስእዋትነት እየከፈለ እየኖረ ነው ” ብለዋል።
” ያሉ ችግሮች ወደ ጦርነት ሳያስገቡ አንድ ህወሓት የሚባል ድርጅት በፕሪቶሪያ ስምምነት አካል የሆነ ባለቤት የሆነ ውስጣዊ ችግሮች አጋጥመውት ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ሰላሙን ዘላቂ ለማድረግ የሚያስችል ስራ በመስራቱ ወደ ጦርነት ሊገባ አይችልም ” ሲሉ ተደምጠዋል።
” ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደዚህ ብለዋል … እንዲህ ብለዋል ተብሎ የተለያየ ትርጉም ከተሰጠው በኃላ ይሄን በሚመለከት ህወሓት ጠቅላይ ሚኒስትሩን engage አድርጓል። ” ብለዋል።
” በዚህ ደረጃ ጦርነት ውስጥ የሚያስገባን ነገር እንደሌለ ግልጽ ሆኗል ” ሲሉ አክለዋል።
” ህወሓት አንድ ድርጅት ነው ” ያሉት አቶ አማኑኤል አሰፋ ፥ ” የተለያዩ ስራዎች ሊሰራ ይችላል ፤ ያን ስራ በሚመለከት መወያየትና መነጋገር ይቻላል። ችግሮች ካሉ ለመወያየት እና አብሮ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የተጀመረ የሰላም ማዕቀፍ አለ ያን መሰረት አድርጎ መወያየት እና መፍታት ነው ” ሲሉ ተናግረዋል።
” ኢትዮጵያ ውስጥ በተከታታይ የተደረጉ ጦርነቶች ናቸው የዛሬውን ችግር ያመጡት ” የሚሉት አቶ አማኑኤል ” ብዙ ችግር ባለበት ሀገር ሆነን አሁንም ጦርነት ውስጥ ለመግባት የሚያስችል ምንም ምክንያት የለም ” ብለዋል።
” ስለተሰበሰብን ፣ አንድ አዳራሽ ውስጥ ገብቶ ህወሓት የሆነ ነገር ስላደረገ ጦርነት አይመጣም ፤ እንዴት ጦርነት በዚህ ልክ ርካሽ ይሆናል ? ” ሲሉ ጠይቀዋል።
” ይሄ የአንድ ድርጅት ጉዳይ ነው ፤ ውስጣዊ ችግሩን ለመፍታት ነው ጉባኤ የሚደረገው ” ሲሉ ለወይን በሰጡት ቃለ መጠየቅ ተናግረዋል።