ኢትዮጵያ ጽኑ እምነት፣ ለራሳቸው ክብር፣ አገራቸውን ከልብ በሚወዱ ልጆቿ 615.7 ሚሊዮን ችግኝ ተከለች። ከ29.1 ሚሊዮን በላይ አሽራዎች ዛሬ በኢትዮጵያ ማህጸን ውስጥ የአሻራ ዘራቸውን አሳርፈው ታሪካቸውን ጽፈዋል። ይህ ታላቅ ህዝብ የተሳተፈበት ዘመቻ በተጀመረበት ድባብ መፈጸሙ ታውጇል። ይህንኑ አስመልከቶ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ” ምኞት ተግባራችን ሁሉ የተሻለች ኢትዮጵያን በኅብረት ገንብቶ ማቆየት ነው። ይኽንኑ እንቀጥላለን” በሚል መደምደሚያ የምስጋና መልዕክት አስተላፈዋል።
ከግማሽ በላይ የኢትዮጵያ ገላዋ በስነምህዳር መናጋት እየተናወጠና በዚሁ ሳቢያ በመሬት መንሸራተት ከፍተኛ አደጋ እያስተናገደች ያለችው ኢትዮጵያ ከዚህ አስደንጋጭ አደጋ የምትወጣው ችግኝ በመትከል እንደሆነ ባለሙያዎች ሶመክሩ ቆይተዋል። አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በሁዋላ በይፋ አገር አቀፍ አድርገው ጀምረውት ለዓለም ማሳያ ምሳሌ የሆነው የአረንጋዴ አሻራ የኢትዮጵያን ማህጸን እያለመለመ እንደሆነ መረጃዎች ይፋ አድርገዋል። አላፊ አግዳሚውም የሚታዘበው ጉዳይ ሆኗል።
” ለምን ዛፍ ተከልክ፣ አስተከልክ? ለምን ከተማ ጠርግህ፣ የደሆች ቤት አፍርሰህ ሰራህ” በሚል በጎውን ተግባር በክፉ ውንጀላ እየተከታተሉ ሲያጠለሹ የነበሩና ይህንኑ ማጥላላት በዘፈን ሳይቀር ያጀቡ እነደነበር ያታወሳል። ይሁን እንጂ በጀመሩበት የገፉት አብይ አሕመድ ዛሬ 600 ሚሊዮን ችግኝ እንዲተክሉ ጥሪ ያቀረቡለት ሕዝብ ጥሪውን ተቀብሎ ቀኑን በስኬት ማህደር ውስጥ ለማስመዝገብ በቅቷል። እንደ አገርም ይህን አጀንዳ በማጉላት የበኩላቸውን ያበረከቱ ሁሉ ድሉን አብስረዋል። ጅምሩ በሁሉም መስክ እንዲቀጥል ተማምለዋል። አብይ አሕመድ የሚከተለውን ብለዋል። ከስር ያንብቡ
የዛሬ ጀምበር ወጥታ እስክትጠልቅ ስድስት መቶ ሚሊዮን ችግኞችን ልንተክል ኢትዮጵያውያን ሁሉ አቅደን ነበር። ያሰብነውን ሳናሳካ ጀምበር የሚጠልቅብን አይደለንምና በአንድ ጀምበር 615.7 ሚሊዮን ችግኞችን መትከል ችለናል።
ህፃናት ተስፋቸውን ተክለዋል። ወጣቶች ጽናተቸውን አሳይተዋል። አረጋውያን ውርስ አኑረዋል። ኢትዮጵያውያን ከሊቅ እስከ ደቂቅ ከቤታቸው ወጥተው የማይደበዝዝ አሻራ አኑረዋል። በማበራችን እና በመጽናታችን በአለም በሌላ ስፍራ በአንድ ጀምበር ያልተደረገውን እኛ ኢትዮጵያውያን አድርገነዋል። ዛሬ ለአየር ንብረት ለውጥ ሚዛን ጥበቃ ቆመን ውለናል። የአፈር መራቆትን ለመመከት ተሰልፈን ውለናል። የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ስንደክም ውለናል። ምድራችንን አረንጓዴ ለማልበስ ልምላሜን ለመመለስ ሳንበገር ሰርተናል። ፈጣሪም ረድቶን ለዛሬዋ ጀምበር ያሰብነውን አሳክተናል።
ዛሬ 29.1 ሚሊዮን ዜጎች በ318.4 ሄክታር በጂኦስፓሻል መረጃ በተገኘባቸው ስፍራዎች ላይ ችግኞችን ተክለዋል። እስካሁን በመረጃ ቋት ከተመዘገበው ውጭ የተተከሉ ችግኞች መረጃ በተከታታይ የሚገለፅ ይሆናል።
ለአስደማሚው የኢትዮጵያውያን ኅበረት እና ጽናት እነሆ ምስጋና። ለስኬታችን የእቅድ፣ የክትትል እና የመረጃ አውታር በመሆን በትጋት የሰራችሁ አመራሮች ባለሞያዎች እና የሚዲያ ተቋማት ምስጋና ይገባችኋል። ምኞት ተግባራችን ሁሉ የተሻለች ኢትዮጵያን በኅብረት ገንብቶ ማቆየት ነው። ይኽንኑ እንቀጥላለን።