ጅቡቲ በይፋ ኢትዮጵያ የታጁራን ወደብ መቶ በመቶ እንድታስተዳደር ፈቃዷ እንደሆነ አስታወቀች። የጅቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለቢቢ ይህን ሲያስታውቁ እንዴትና በምን ውል ኢትዮጵያ ወደቡን እንድታስተዳድር ጅቡቲ እንዳሰበች ያሉት ነገር የለም። ኢትዮጵያ ከሶማሊ ላንድ ጋር የባህር በር ባለቤት ለመሆን ያደረገችውን ስምምነት ተከትሎ ሶማሊያን ጨምሮ ጅቡቲ ተነሳሳይ አሳብ ማቅረባቸው የኢትዮጵያን አጀንዳና ጭና የሚያሳይ ሆኗል። ጅቡቲ ቀደም ሲል ስምምነቱን መቃወሟ ይታወሳል።
“በአፍሪካ ቀንድ የተነሳውን ውጥረት ለማርገብ ጂቡቲ ከወደቦቿ አንዱን ኢትዮጵያ በቀጥታ እንድታስተዳድር ለማድረግ አማራጭ አቅርባለች” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ለቢቢሲ ትክረት አፍሪካ ክፍለ ጊዜ ላይ “ኢትዮጵያ የባህር መዳረሻ እንድታገኝ አንደኛውን የጂቡቲ ወደብ ሙሉ በሙሉ እንድታስዳድር አማራጭ አቅርበናል” ማለታቸውን ተከትሎ ከኢትዮጵያ ወገን ለጊዜው የተባለ ነገር የለም። ቢቢሲ በሪፖርቱ ኢትዮጵያ የባህር ጦር ማስፈርና መትከል ስለመቻሏ ጥያቄ አላቀረበም።
ጂቡቲ ያቀረበችው ወደብ ከኢትዮጵያ በመቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን የታጁራ ወደብን እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ውሳኔውም ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር በገባችው ውል መነሻነት የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ እንደሚረዳ አመልክተዋል።
ከኢትዮጵያ በየዓመቱ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ግድም የምትሰበስበው ጅቡቲ፣ ይህን አማራጭ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኦማር ጉሌህ ለኢትዮጵያ እንዳቀረቡ ሚኒስትሩ ለቢቢሲ ከተናገሩት ለመረዳት ተችሏል።
ጅቡቲ ባቀረበችው በአማራጭ ሃሳቡ ዙሪያ በሚቀጥለው ሳምንት በሚካሄደው የቻይና አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ከሁለቱ መሪዎች ጋር ለመወያየት ዕድል እንደሚኖር ሚኒስትሩ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
የታጁራ ወደብ በ90 ሚሊዮን ዶላር በፈጀ ወጪ ማሻሻያ ተደርጎበት ኢትዮጵያ ከአራት ዓመት በፊት መጠቀም እንደጀመረች በወቅቱ የሁለቱም አገራት የሚመለከታቸው ተቋማት ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያ በአፋር ክልል አለ የሚባለውን በቢሊዮን ቶኖች የሚገመት የፖታሽ ክምችትን እንዲሁም ለድንጋይ ከሰል እና የብረት ጭነቶችን በታጁራ ወደብ በኩል ወደ ውጪ ለመላክ እቅድ መሰነቋ በወቅቱ መገለጹ አይዘነጋም። ከታጁራ ወደብ እስከ ወደቧ ከተማ በልሆ ድረስ ያለው 120 ኪሎ ሜትር መንገድ በ156 ሚሊዮን ዶላር የተገነባ ምቹ አስፋልት በመሆኑ በተሽከርካሪዎች ዘንድ ተመራጭ እንደሆነም በወቅቱ ተገልጾ ነበር።
ኢትዮጵያ እያደገ ላለው ኢኮኖሚዋ፣ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ላለው ህዝቧ የባህር በር ባለቤትነት አሁን ላይ ህልውናዋ በመሆኑ የባህር በር ጥያቄዋ ህጋዊ መሰረት እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በተደጋጋሚ መናገራቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያን መንግስትና የመከላከያ ሃይሏን በጋራ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር አብረው ያፈረሱት ሻዕቢያና ወያኔ ባደረጉት ስምምነት ኢትዮጵያ ባህርቭ አልባ እንድትሆን ከተፈረእደባት በሁዋላ ኢትዮጵያ ቡና ሸጣ ያገኘችውን፣ ተበድራ የሰበሰበችውን ሃብት ለውደብ ኪራይ ስትገብር መኖሯ ይታውሳል። አብይ አሕመድ ወደ ስልታን በመጡ በአራተኛው ዓመታቸው በይፋ የባህር በር እንደሚያስፈልግ ቢያስታውቁም የባህር ሃይል ማደራጀት የጀመሩት ስልታን በያዙ ማግስት ነው።
አብይ አህመድ “የምናደርገውን የሚያውቁት ጠላቶቻችን ናቸው” በሚል በተደጋጋሚ እንዳሉት፣ የኢትዮጵያ አካሄድ ያስደነገጣቸው ኢትዮጵያ ፊቷን ወደ ሶማሊላንድ ስታዞር ተባብረው ቁጣ ማሰማታቸውና ወታደር ማስለጠን፣ መሳሪያ ማጋጋዝና ኢትዮጵያን ለማወክ ያላቸውን ሃይል ሁሉ ለመጠቀም ዝግጅት ላይ ናቸው። ሁሉም ቢሆንም ግን ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄዋ እንደማይቆም ይፋ አድርጋለች።
ጅቡቲ ለኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ እፈቅዳለሁ ያለችው ወደብ ኢትዮጵያ ለሰላም ዋስትናዋ፣ በቀይ ባህር ላይ ጉልህ ሚና ለመጫወት ያላትን ዕቅድ ለማሳካት ፈቃድ የምታገኝበት ስለመሆኑና ቦታው ልክ ሶማሊላንድ እንዳዘጋጀችው አይነት ስትራቴጂክ ስፍራ ይሆን አይሆን ለጊዜው የተባለ ነገር የለም።