“ዛሬ በትግራይ እንደተለመደው በህዝብ ስም እየማሉ ለስልጣን የሚሻኮቱት ሃይሎች በሙሉ እንዴት እንደሚያስቡ ማሰብ ለህመም ይዳርጋል” የሚሉ ወገኖች እነዚህ አካላት እከሌ ከከሌ ሳይባል ያለ አንዳች ሃፍረት በሚሊዮኖች መቃብርና ደም ላይ ለስልጣን ሲወዛገቡ ማየታቸው ከቶውንም ሊቀበሉት እንደማይችሉ ይናገራሉ።
በትህነግ ዕቅድ አውጪነትና ትዕቢት፣ በአቶ ጌታቸው ረዳ የፕሮፓጋንዳ ፊት አውራሪነት ተሞልቶ ወደ ጦርነት የገቡት የትግራይ ተወላጆች አካል ጉዳቶችን ሳይጨምሮ ሚሊዮን የሚጠጋ ህይወት መቅጠፉ፣ ትግራይ ለሶስትና አራት አስርት ዓመታት ወደሁዋላ መመለሷ፣ ከምንም በላይ የትግራይን ህዝብ ወዳጅና ጎረቤት አልባ የሚያደርግ መንገድ ተከትለው ብቻውን ያስቀሩት እነዚህ አካልት፣ በየትኛው በጎ ተግብራቸው ህዝብ ፊት ቆመው እንደሚናገሩ ግራ የሚገባቸው “ራሱ የትግራይ ህዝብ ምን ተደርጎ ነው እንዲህ የፈዘዘው ” ሲሉ ይጠይቃሉ።
ሰሞኑን በትህነግ ውስጥ የተፈጠረው መከፋፈል አድሮ የሚጠራ የየራሱ የጀርባ ገፊ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ፣ እነ ዶክተር ደብረጽዮን የሚመሩት ቡድን ” ተው” ሲባል ገፍቶ ያካሄደው ጉባኤ ሲጠናቀቅ በገሃድ የመከፈሉን ሚስጢር አሳይቷል።
በዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመራው ትህነግ ባካሔደው ጉባኤ ያልተሳተፉ የፓርቲውን አመራሮች እና ቁጥጥር ኮሚሽን ማገዱን፣ ይህንኑ ተከትሎ ትህነግን ወክለው የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደርን እየመሩ ያሉ አካላት ውክልናቸው መነሳቱን፣ በዚሁ ሳቢያ አዲሱ አመራር የክልሉን አስተዳደር የመመደብ ህጋዊ ስልታን እንዳለው ተጠቁሟል።
ይህ “መፈንቅለ ጌታቸው” የተባለው አካሄድ ከጉብኤው መጠናቀቅ ቀድሞ የተነገረው ሁሉ ወደ እውነት ቀይሮታል። የጀርመን ድምጽ ያነጋገራቸው የሕግ ምሁር፣ ገና ጉባኤውን ሲጠናቅቅ ትህነግ በጉባኤው መዝግያ ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች መካከል አንዱና ዋናው ከዚህ ቀደም የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች የነበሩ እና በጉባኤው ያልተሳተፉ አባላቱ ማገዱን ማስታወቁ፣ ቀጣዩን አካሄድ ያሳየ ነበር።
ይህ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እየመሩ ያሉትን አካላት እና የትህነግን የቁጥጥር ኮምሽን አባላት በጥቅሉ መታገዳቸው፣ ይዞት የሚመጣውን ‘የቢሆን ትንተናዎች’ አስተያየት ሰጪው ዘርዝረዋል።
የሕግ ምሁሩ እንደሆኑ ተጠቅሶ ገለጻ የሰጡት አቶ ተኽሊት ገብረመስቀል፣ “ስለቀጣይ ሁኔታ በርካታ የቢሆን ትንተናዎች ማስቀመጥ የሚቻል ቢሆንም፣ በዋነኝነት ግን ጉባኤ ያደረገው ትህነግ በፓርቲው የስልጣን ድርሻ ወደ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የገቡ ወይም የግዚያዊ አስተዳደሩ እየመሩ ያሉ የስራ ሐላፊዎች እንዲነሱ መስራት ሊሆን ይችላል” ሲሉ ከጉባኤው መጠናቀቅ በሁዋላ ተናግረዋል።
ተኽሊት ገብረመስቀል “ይህ ጉባኤ አካሂጃለሁ የሚለው ሐይል፣ በግዚያዊ አስተዳደሩም ውክልና ያለኝ ስለሆነ አልያም እዛ ያሉ ሰዎች በእኔ ስም የተወከሉ ስለሆኑ፣ አሁን ደግሞ ከፓርቲው ስለወጡ ወይም ሐላፊነታቸው ስላጡ፣ የመንግስት ስልጣናቸውም እንዲሁ አብቅቷል ሊል ይችላል” ሲሉ እንደገለጹት፣ ዶክተር ደብረጽዮን ” ተረት ናቸው አሁን” ሲሉ እንመለስ እንኳን ቢሉ በስራ የጉባኤ ተራ አባል ከመሆን የዘለለ አድል እንደማይኖራቸው ተናግረዋል። መንግስት የተፈራረመው ከትህነግ ጋር ስለሆነ በቀጣይም ከትህነግ ጋር እንዲወያይ ጥረት እንደሚደረግ በይፋ ጠቅሰዋል።
ይህ ሁሉ ሲሆን ትንፍሽ ያላለው መንግስት የእነ ደብረጽዮን ቡድን ከትናንት በስቲያ የላከውን ወኪሎች ” እውቅና የላችሁም። ወደ ህጋዊ መንገድ ተመለሱ” ብሎ እንደሸኘ መረጃ ያላቸው ለኢትዮሪቪው ተናግረዋል።
የፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ሥምምነትን የተፈራረሙት “ትህነግና እና የኢትዮጵያ መንግስት ስለሆኑ በህወሓት ስም ወደ ግዚያዊ አስተዳደሩ የገቡ ሰዎች ላይ ውክልናዬ አንስቻለሁ ሊል ይችላል። ይህ በቀጣይ ሊከሰት የሚችል አንድ ግምት ነው” ያሉት የህግ ባለሙያውን ትንበያ ሙሉ በሙሉ የመድገም ያህል ያንጸባረቀው የዶክተር ደብረጽዮን ቡድን፣ የእነ አቶ ጌታቸውን ሃይል ” ታሪክ ሆኗል” ከማለት በተጨማሪ በግልጽ ማንም የማያውቃቸው ስለመሆናቸው ጠቅሰዋል።
ሌሎች የቢሆን ትንተና የሚያስቀምጡት የሕግ ምሁሩ አቶ ተኽሊት ገብረመስቀል፣ ዝቅተኛ ዕድል ቢኖረውም እስከ ቀጣይ ምርጫ ድረስ ግዚያዊ አስተዳደሩ ባለበት እንዲቀጥል መግባባት አልያም ያለው ድርሻ መከፋፈል፣ ሌሎች በቀጣይ ሊከሰቱ የሚችሉ ለውጦች ሊሆኑ እንደሚችሉ ያስቀምጣሉ። ደብረጽዮን ” ህጋዊነቱን አጥቷል” በሚል ያጣጣሉትን የእነ አቶ ጌታቸውን ቡድን የመተካቱን ጉዳይ ግን ባጣጣሉበት ልክ እንዴት እንደሚወገድ አላብራሩም። ይልቁኑም በተደጋጋሚ “በውይይት፣ ውይይት ያስፈልጋል፣ ይህዝብን ሰላም በማይነካ መልኩ፣ ተፈናቃዮችን የመመለስ ጉዳይ አለ ወዘተ ” እያሉ ነው በወጋ ነቀል የገለጹት።
ኢትዮ ኢንሳይደር ባሰራጨው ቪዲዮ ላይ ዶክተር ደብረጽዮን ስለ ውይይት አስፈላጊነት በተደጋጋሚ ሲናገሩ የእነ አቶ ጌታቸው ቡድን ከፍለገ አዲስ ፓርቲ ማቋቋም ይችላል። ሲሉ መደመጣቸው የመቀለ ዙሪያ አካባቢና ራያ መለስ ህዝብ የሚበዙበት አዲስ ፓርቲ ሊቋቋም እንደሆነ የሚሰማውን መረጃ አተንከሮታል። ሰፊ ቁጥር ያላቸውን የትግራይ ህዝብ በድምጽ ሊያስከትል እንደሚችል የተነገረለት አዲስ ፓርቲ ለጊዜው ስማቸው ካልተገለጸ የትግራይ ፓርቲዎች ጋር ግንባር እንደሚገጥምም እየተገለጸ መሆኑ ይታወሳል።
ሌላው ግን በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት መንግስትም በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ የራሱ ድርሻ እንዲኖረው ስለሚደነግግ፣ የተቀናቃኝ ፓርቲዎችም ስለሚገቡ በውይይትም አንድ ላይ ተዳምረው እነ ደብረጽዮንን ሊረቱ እንደሚችሉ የቢሆን ስሌት የሚያስቀምጡ አሉ። ዶክተር ደብረጽዮን ውይይት ያሉትና ሰራዊቱና ባይቶና የሚካተቱበት ጊዜያዊ አስተዳድር ሊቋቋም እንደሚችል በጠቀሱበት ንግግራቸው፣ የፌደራል መንግስትም በስምምነቱ መሰረት ድርሻ አለው ማለታቸውን ገጣጥመው ሰዎቹ ከውይይት የዘለለ ሌላ አቅም እንደሌላቸው የሚናገሩ ጥቂት አይደሉም።
ሁሉንም ጎን አይተው አጠቃላይ በትግራይ ያለው የፓለቲካ እንቅስቃሴ አሳሳቢ አድርገው የሚያስቀምጡት የሕግ ምሁር፥ የአስተዳደር መዋቅር እንዳይጠናከር ዕንቅፋት የሚፈጥር፣ በቀንተቀን የዜጎች ኑሮ ላይም ስጋት የሚፈጥር ፓለቲካዊ ሁኔታ ትግራይ ውስጥ እየታየ መሆኑ አልሸሸጉም። “ይህ ሁኔታ የአስተዳደር መዋቅሩ እንዳይሰራ፣ የቀን ተቀን ስራዎቹን እንዳይከውን ዕንቅፋት የሚፈጥር፣ ሁለት ሶስት መንግስታት እንዳሉ ዓይነት የሚያስመስል በተጨማሪም አሰላለፉ ለመገመት የሚያስቸግር፣ በሁሉ መልኩ እርግጠኛነት እንዲጠፋ የሚያደርግ ነው” ብለዋል። አክለውም “የትግራይ ህዝብ እርግጠኛ ሆኖ ስለ በቀጣይ የሚያቅድበት ዕድል የሚያጠብበት ሁኔታ ነው እየተፈጠረ ያለው” በሚል የችግሩን ድባብ አመላክተዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን ለመምራት ትህነግ የራሱን ሰዎች መመደብ ይችላል ሲሉ ህገወጥ ሲል ምርጫ ቦርድ በፈረጀው ጉባኤ እንደ አዲስ ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በቀጥታ አቶ ጌታቸውን ዒላማ አድርገው ተናግረዋል። እሳቸው ይህን ሲሉ አቶ ጌታቸው ደግሞ “ያለ አስተዳደሩ ፈቃድ ስብሰባ ማካሄድ አይቻልም” ብለው በመቀለ የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን እየመረቁና የአሸንዳን በዓል ለማክበር ሽር ጉድ እያሉ ነው።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግን ቀደም ብሎ ጉባኤው ሳይጀመር የቦርዱን አሰራር ላልተከተለ ጉባኤ እና በጉባኤው ለሚተላለፉ ማንኛውም ውሳኔዎችና ለውጦች እውቅና እንደማይሰጥ በይፋ ማስታወቁና የትህነግን ዕውቅና ሲመልስ በገደብ እንደሆነ በይፋ ማስታወቁ አይዘነጋም። በዚሁ ደብዳቤ ላይ ጠቅላላ ጉባኤ በምን መልኩ መካሄድ እንዳለበት በዝርዝር ማስቀመጡ ይታወሳል።
ከጦርነት ተላቆ ሰላምን ገና በወጉ ያላጣጣመውን የትግራይ ህዝብ ዳግም ወደ ችግር እንዳይከት የተፈራለት ድርጅታዊ መሰነጣጠቅና የስልጣን ግብግብ ተከትሎ ቴዎድሮስ የሚባለው የርዕዮት ሚዲያ ባለቤት ” ደብረጽዮን የጦርነት አንቴና ነው። አንቴና ሞገድ እንደሚስበው እሱ ጦርነትን ብቻ ነው የሚስበው” ሲል ትህነግን ሲያወስድስ በኖረበት አንደበቱ ክፉኛ አውግዟል። በርካቶችም አሁን ላይ በትህነግ ውስጥ የተነሳው የወንበር ጭቅጭቅና “አስፈሪ ድባብ ከአስተሳሰብ መንጠፍና ከቆሞ ቀርነት የሚቀዳ የማይድን የድርጅቱ በሽታ ነው” በሚል እያወገዙት ነው። ብመንም መልኩ በጦርነት እንዲማገድ ለተደረገ ህዝብ፣ ሞቱና ጉዳቱን እንደ ጀብድ በመቁጠር አደባባይ ላይ ለወንበር እየተሻኮቱ ዳግም ለሌላ ችግር መዳረግ ተቀባይነት ሊያገኝ አይገባም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ” ከተያዘው እቅድ ውጭ እኛ የማናቀውን ስብሰባ ማካሄድ አይቻልም ” ሲል የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አስተንቋል።
በትግራይ ክልል በመንግስት መስሪያ ቤቶች ጊዚያዊ አስተዳደሩ የማያውቀው ማንኛውም ሰብሰባ ማካሄድ የሚከልክል የስራ መመሪያ ይፋ የሆነው ከትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፅህፈት ቤት በአቶ ጌታቸው ረዳ ፊርማ ለሁሉም የዞን አስተዳደሮች፣ለወረዳ አስተዳደሮች፣ የክፍለ ከተማ አስተዳደሮችና፣ የወረዳ ምክር ቤቶች
የተላከው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው ጊዚያዊ አስተዳደሩ ከፈቀደው ውጪ ሌላ ስብሰባ ማካሄድ አይቻልም ይላል።
- የኮሌራ በሽታ መከላከል
- ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው መመለስና የክልሉን ግዛታዊ አንድነት ማስከበር
- የ2016 ዓ.ም በጀት መዝጋትና የ2017 ዓ.ም በጀት ማዘጋጀት … ሌሎች ህዝባዊና መንግስታዊ እቅዶች የጊዚያዊ አስተዳደሩ መሆናቸው የጠቀሰው የስራ መመሪያው ፤ ” ከዚህ ውጪ የሚደረጉ ሰብሰባዎች የተያዘው እቅድ ስለሚጎዱ አይፈቀዱም ” ብሏል።
ከላይ ከተጠቀሱት እቅዶች ውጪ ማሰተናገድ የጊዚያዊ አስተዳደሩን ስራ በማደናቀፍ ተጠያቂነት የሚያስከተል መሆኑን በመግለጽ አስጠንቅቋል። የሚመለከታቸው የመንግስት አካላትም ይህኑን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥብቅ መመሪያ ሰጥቷል።