ማንም ይሁን ማን ባንዲራ ላይ ከቆመረ፣ በባንዲራ ስም የግል ጥቅሙን ለማሳካት ሂሳብ ካሰላ፣ ተደረጃቶና አደራጅቶ በመናበብ በባንዲራ ክብር ላይ ጥላውን ካጠላ፣ ባንዲራውን ለሚወድ ህዝብ ባንዲራ በማሳየት ሴራ ከጎነጎነ፣ በዚሁ ሳቢያ ጉዳት ከደረሰ ባንዳነት ተፈጽሟል ማለት ነው። በባንዲራ ላይ ባንዲራ ለብሶ የሚደረግ ውስልትና እንደ አገር ክህደትም ይቆጠራል። ልክ ኢትዮጵያዊ መስለው ከግብጽ ጋር እንደሚጫወቱት “ዜጎች” ሁሉ ከአገር ቤት እስከ ፓሪስ ኦሊምፒክ መንደር የኢትዮጵያ ባንዲራ ከፍ እንዳይል የሴራ ድር የሚያደሩ ሁሉ ብሄራዊ ክህደትን ፈጽመዋል። ይህ መነሻ ነው።
ኦሊምፒክ፣ ዓለም ዋንጫና የአገር አቋራጭ ውድድሮች ኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያችን ቀን ቆጥረው የሚያነግሱበት ነው። በተጠቀሱት ውድድሮች “ወርቅ ወይስ ብር” በሚል ስሌት ውይይት ይደረግ ካልሆነ በቀር ስለማሸነፍ ጥርጥር የለም። በቃ ባህላችን ሆኖ በቅብብል እዚህ ደርሷል። “ረዥም ሩጫ የኢትዮጵያዊያን ነው። እናቁመው ወይ” ተብሎ በአደባባይ እጅ የተሰጠበትም ጉዳይ ነው። እናም ለዚህ ላበቁን ሁሉ ምስጋና ይድረሳቸው። እንደዛሬ ተንኮል ሳይነግስ በመረዳዳት በዓለም አደባባይ ሲፈሱ ለኖሩ ብሄራዊ ጀግኖች ክብር ይሁን። እንደዛሬ ጮሌነትና ሌብነት፣ የስልጣን ጥማት ሳያገነግን በቀናነት አገራቸውን ለዛሬው ክብር ላበቁ፣ በስፖርቱ ሳይገለገሉ አገልግለው ላለፉ ሞገስ ይሁን!!
በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንዳ አትሌቲክስ ልዩ የክብር ማሳያ፣ ዓለም ላይ መድመቂያ፣ ኢትዮጵያን የሚጠሉ ሁሉ ሳይወዱ በዓለም አደባባይ ለኢትዮጵያ የሚንበረከኩበት፣ ለሰንደቋና ለህዝቧ ሳይወዱ ቆመው የሚያጨበጭቡበት፣ ለሳምንታትም ቢሆን ህዝብ አንጀቱን የሚያርስበት ነው። ለዚህ ነው እናቶቻችን አትሌቶች ዓለም አደባባይ ሲከንፉ እንደ ዕምነታቸው ወለል ላይ ተንበርክከው የሚጸልዩት፣ አስቀድመው የሚሳሉት። ይህ የኢትዮጵያ ልዩ መልክ ዛሬ ዛሬ ሃላፊነት በማይሰማቸው ቀትር ቀላሎች ጊዜ ሳይመርጥ ክህደት እየተፈጸመበት ነው።
ውድድሩ ስፍራ ያሉ ታዛቢዎችና ስለ ሁሉም አካሄድ ጠንቀቀው የሚያውቁ ለግንዛቤ ያህል ሲሉ ቆንጥረው እንደገለጹልን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በፓሪስ ታውኳል። የተወዳዳሪነት መንፈስ እምዳይኖረው ተደርጓል። የቡድን ስሜትና መናበብ እንዳይኖር ተዶልቷል። ይህ ሁሉ የሆነው በዕቅድና በሴራ ስለመሆኑ በርካታ መረጃዎች አሉ።
በአደባባይ የአገር ክህደት ተፈጽሟል
እንደ እነዚህ ወገኖች ግምገማ የተፈጸመው የአገር ክህደት ነው። በምሳሌ ሲያስረዱ ” ጦር ሜዳ ጠላትን ሊያጠቃ ቦታ መርጦ በመሸገና ቃት ሊስብ ትንፋሹን የዋጠ ሰራዊት በራሱ ወገን ዒላማውን እንዲስት ዘመቻ አይካሄድበትም” ይላሉ። ቀጥለውም በኦሊምፒክ ለመወዳደር ፓሪስ የመሸገው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድንም ተመሳሳይ መሆኑን ጠቁመው እንዴት ክህደቱ እንደተፈጸመ ይዘርዝራሉ።
ቡድኑ ለውድድር ሊንቀሳቀስ ቀናት ሲቀሩት የሚዲያ ዘመቻ ተጀመረ። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር የሆነው ገዛኸኝ አበራ ” የብቃት ችግር አለ” ሲል በምርጫውና በቴክኒክ ጉዳይ ቅሬታውን አሰማ። “አሳቡ ትክክል ሊሆን ቢችል እንኳ ገዛኸኝ አራት ዓመት የት ነበር? ለምን ውድድሩ ሊጀመር ሳምንት ሲቀረው ይህን ማለት ፈለገ?” ብሎ ለመጠየቅ የደፈረ አልተገኘም።
የጉዞ ቀናቱን ቀያይሮ ፓሪስ የደረሰው ገዛኸኝ አበራ፣ ጉዞውን ስለመሰረዙ አላሳውቀም። መቼም እንደሚገባ አልተናገረም። ብቻ ደስ ባለው ቀን ተከሰተና “ሞራሌ ተነክቷል፣ ካሳ እፈጋለሁ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ካሰኝ” ሲል ድምጹን አሰማ። ነገሩ በታሰበበት መልኩ ይሰራ ስለነበር ስለ አሰራሩ፣ ስለጉዞው መቀያየርና ስለተጓደለበት ጉዳይ ሊጥየቀው የደፈረ ሳይገኝ ጩኸቱን ከፓሪስ ማስተጋባት ተመረጠ።
ኢትዮጵያ የሚሰጣት አክሪዴሽን አስራ አምስት ብቻ ነው። እንደ አስፈላጊነቱ ለአሰልጣኞች ቅድሚያ እየተሰጠ ሰው እየተቀያየረ እንዲገባ ካልተደረረገ አይበቃም። ገዛኸኝ ሲቀር የሆነው ይህ ነው። በመቅረቱ ተሰረዘና ሌሎች እንዲገቡበት ተደረገ። እወነታው ይህ ሆኖ ሳለ ለምን ማጯጯህ ተፈለገ?
ለአንድ ቀን ስታዲየም መግቢያ ባለማግኘቱ ለምን በዛ መጠን ጮኸ? ለምን የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲፈርድ ጠየቀ? ፍርዱንስ እንዴትና በምን መስፈርት ለሱ ሞራል ግንባታ በሚሆን ደረጃ እንዲሆን ጠየቀ? ታዛቢዎቹ ይህን የሚያነሱት አካሄዱ የተደራጀና ከአገር ቤት ጀምሮ ቡድኑንን ፓሪስ ዘለቆ የማመስና ውጤቱ እንዲበላሽ ጫና የመፍጠር አካሄድ መሆኑን ለማሳየት ነው። የዚህ ውጤት ደግሞ የሚያባርሩትን አባረው የሚያነግሱትን ለማምታት እንጂ ለአገርና ለህዝብ እንዲሁም ለባንዲራ ካለ ፍቅር አይደለም። ሃይሌ ገብረስላሴ ኦሊምፒክ ሲደርስ ጠብቆ የለኮሰውን ችቦ ገዛኸኝ ተቀበለ ይሏል ይህ ነው።
በግል አትሌቶችን ዒላማ ያደረገ አካሄድ ደግሞ ሌላው ውጤቱን የማምከንና አገራዊ ክህደት በየፈርጁ ስለመፈጸሙ ማሳያ ነው። አትሌት ፅጌ ዱጉማ በ800 ሜትር ሴቶች ፍጻሜ ሁለተኛ በመውጣት ለኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ ያስገኘት ጠንካራና በዕምነቷ የጸናች አትሌት በመሆኗ በድል አሸበቀረቀች እንጂ የዘመቻው ዒላማ ነበረች። እዛው ፓሪስ ያሉ እንደሚሉት የድጉማን ልጅ “ማን ነው አሰልጣሽ? ማን ነው የሚመችሽ? በደል ተፈጽሞብሻለ ወይ?” ብሎ ለመጠየቀ አንድ ሳምንት መታገስ ያቃታቸው የረጩት የተሳሳተ መረጃ እሷን የሚመከቱ ዘገባዎች ሌላው የተጠናና የተናበበ አካሄድ ማሳያ እንደሆነ ይናገራሉ።
ጽጌ ድጉማ ከቀድሞ አስለጣኟ ጋር አስቀድማ ለማናጀሯ አስታውቃ ውል ማፍረሷን ከፓሪስ አመክታለች። ይኸው ምስክርነቷ ቀድሞ ቢጣራ ኖሮ ጩኸቱ ባልተሰማ ነበር። ነገር ግን ስም ያላቸው ሚዲያውን እያወናበዱና የተሳሳተ መረጃ እያቀበሉ ውጤቱ ላይ ድራቸውን አደሩበት። ለሁሉም ታማኟ አትሌቷ በመሆኗ እሷን ማመኑ ግድ ነው።
ሌላውና ትልቁ ችግር አትሌቶች ላይ በመንጠላጠል ደባ የሚፈጽሙ አስልጣኞችና የእነዚሁ አሰልጣኞች ሰላባ የሆኑ አመራሮች የፈጸሙት ብሄራዊ ክህደት ነው። ዛሬ ውድድሩ ባለማለቁ ብዙ መዘርዘር ባያስፈልግም ጠቆም አድርጎ ለማለፍ በአምስት ሺህ ውድድር 8ኛ ደረጃ ያገኘችው ጉዳፍ ፀጋይ በሶስት ውድድር እንድትወዳደውር የፈቀደው ማን ነው? ብሎ መጠየቅ ግን ግድ ነው? ባለቤቷና አስለጣኟ የሚባለው ሁልፍ ይህደጎ ነው ወይስ የኦሊምፒክ ፕሬዚዳንቱ ዶክተር አሸብር ናቸው? ወይስ ሌሎች በስም የማይጠቀሱ አካላት? ይህም አንዱና ትልቁ ጉዳይ ነው።ሕዝብ እውነቱ ሊነገረው ይገባል።
የዚህ ሪፖርት አዘጋጅ መረጃው አለው። ይሁን እንጂ አሁን ባለቀ ሰዓት የሚለወጥ ነገር ባለመኖሩ ጫና ላለመፍጠር ውድድሩ እስኪያልቅ መታገስን ይመርጣል።
አትሌቷት ጉዱፍ አዲስ ናት። ጫና መሸከም አትችልም። የልምድና የጉልበት ጉዳይም ጥያቄ ያንሳባታል። ነገር ግን በሶስቱም ውድድር ለመወዳደር ሚኒማዋን ታሟላለች። ነገር ግን እንድትወዳደር ሲወሰን ልምድ ያላቸው ሲኒየር አትሌቶች አልተጠየቁም። ስለዚህ ይህ ውሳኔ እንዴት እንደተወሰነ ህዝብ ማውቀ አለበት። በመሃላ ብዛትና “በእኔ ይሁንባችሁ” በሚል የሰፈር ምህላ ተደርጎም ከሆነ መነገር ስላለበት ህዝብ ሰምቶ የህሊና ዳኝነቱን እንዲሰጥ በተራ የማህበራዊ ሚዲያ የወፍ በረር ወሬ ሳይሆን ግልጽ ግምገማ ተካሂዶ መቅረብ አለበት።
ፖሊሲ ላይ፣ እቅድ ላይ፣ ስትራቴጂ ላይ ሊሰራ የሚገባው ሚኒስትር ራሱን ከዚህ ሁሉ ሃላፊነቱና ማዕረጉ ከስክሶ የማህበራዊ ሚዲያ ማድመቂያና ማሻሻጫ ማድረጉ በራሱ የአቅም ማነስ ክህደት እንደሆነ እዚህ ላይ ማንሳት ግድ ነው። አፍንጫው ስር የአዲስ አበባ ስታዲይም አረቄ መቸርቸሪያ ሆኖ የማይተነፍስ የስፖርት ሚኒስትር ….
ውጤቱ ምን ይሆናል
የፓሪሱ ውጤት ከቀደመው ጋር ሲነጻጸር የተበላሸ ይሆናል። በዓለም ደረጃ ሲሰላ ግን እንደወትሮው ሁሉ ትልቅ ነው። አንድም ሜዳሊያ የማያገኙ ወይም ሳያገኙ እድሜያቸውን የሚፈጁ አገራት አሉና። አስተያየት የሚሰጡት ክፍሎች እንደሚሉት ውጤቱ እንዲበላሽ ታቅዶና ታስቦበት ነው የተሰራው። “ይከበራሉ፣ ይወደዳሉ” በሚባሉት ሰዎች መሪነት፣ ይህንኑ በሚያደራጁ ሚዲያዎች አጋዥነት ሳቢያ አትሌቶች የውድድር ስሜታቸው ገሽቧል። በፓሪስ ያለች አንድ ጀግና አትሌት ” የሌሎች አገር አትሌቶች ያላቸው ህብረትና ፍቅር ያስቀናል። እኛን ግን የአገራችን ሰዎችና ሚዲያዎች በውድድር ላይ ሆነን እንኳ አያከብሩንም። ምን አደርግናቸው?” ብላለች።
መሆን የነበረበት
ማንም እንደሚያምነው ስፖርተኞ ሲያረጁና ውድድር ሲያቆሙ በአብዛኛው ምላሳቸው ይረዝማል። ይህ በሁሉም ስፖርት የተለመደ ነው። እውነታው ይህ በመሆኑ “ሚዲያዎች” ዝም ብለው መነዳት የለባቸውም። አልነበረባቸውም። ቢቻል በዝግጅት ወቅት አገርና ባንዲራን አስቀድመው የሚስተካከለውን ጉዳይ ነቅሶ በማውጣት መከራከር ነበረባቸው። ካልሆነ ደግሞ ውድድሩ ሲያልቅ ነገሮችን ገምግሞ አስፈላጊውን በትር መምዘዝ ስራቸው ሊሆን በተገባ ነበር። ይህ ያደረጉና የሚያደርጉ ቢኖሩም አብዛኞቹ ግል የሉበትም።
በተለይም ሮጠው ያሳለፉ፣ “የህዝብና የአገር አደራ ተሸክመን ነበር” የሚሉ፣ ስነ ልቦና ለአንድ ስፖርተኛ ውጤት ማማር ያለውን ጫና የሚረዱ በዚህ ደረጃ ፓሪስ ባለው የኢትዮጵያ ህዝብ ወኪል ስፖርተኞች ላይ የግል ፍላጎትን ብቻ በማስላት ዘመቻ መክፈታቸው ወደፊት መነሻውና መድረሻ ዓላማው ይፋ የሚሆን ቢሆንም በአሳዛኝ ታሪክነቱ የሚቅመጥ ታሪክ ሰርተዋልና ባያደርጉት ጥሩ ነበር። ምን ያህል ውጤቱ ላይ ጫና እንዳሳደሩ የሚያውቁ ያውቁታል። ከዚህ በላይ አሳዛኙ ግን የሚዲያ ዘመቻው ብቻ ሳይሆን በስልክ አንዳንድ አትሌቶች ጋር በመደወል ጭምር የተፈጸመ ክፉ ተግባር አለ። ይህን የፈጸሙ አድሮ ይፋ የሚሆን በጀግንነት ታሪካቸው ላይ የሚደረብላቸው የሃፍረት ካባ ይሆንላቸዋል።
ወደፊት ምን ይደረግ
ከፓሪስ መልስ ምርጫው፣ ቴክኒካል ጉዳይ፣ ዝግጅቱ፣ አስተዳደርን የሚመለከተው፣ ፌዴሬሽኑንና ኦሊምፒክ ኮሚቴውን ለይቶ ቀድሞ ግልጽ ግምገማ ማካሄድ። ችግሩን መለየት። አትሌቶች በነጻነት የሚሰማቸውን እንዲናገሩ ማድረግ። ችግሩ ከተለየ በሁዋላ በግል እንደ ችግሩ መጠን አጥርቶ ጥፋተኛውን መለየት። በገለልተኛ ወገኖች ይህን መሰሉ ግምገማ ከተከናወነ በሁዋል ለሚዲያ በይፋ መረጃ አስደግፎ ማቅረብ ቀሪውን ጊዜ የተሻለ ያደርገዋል።
የዚህ አስተየት ዋና ምንጮች ከዝግጅት፣ ምርጫና የአትሌቶች ምዝገባ ጀምሮ በርካታ ስህተቶችን ታዝበዋል። ኦሊምፒክ ኮሚቴንም ከተራ የዘመቻ ወቀሳ በዘለለ ገምግመዋል። ስለሁሉም ጉዳይ በቂ መረጃ አላቸው። ለመንግስት ግብዓት የሚሆን መረጃዎ እያሰባሰቡ እንደሆነ የሚጠቁሙት እነዚህ ወገኖች ለዚሁ ተግባራቸው ዝግጅት ላይ መሆናቸው አመልክተዋል።
ፌዴሬሽኑን በተመለከተ ቀድሞ በሙስናና ሃላፊነትን ተገን አድርገው በግል ንግድ አሰራሩን አበስብሰውት የነበሩና ዛሬ ዳግም ለመመስ በኔትዎርክ አሜሪካ ሆነው ዘመቻውን የሚመሩትን ወገኖች ማንነት የሚያውቁ፣ አሁን የተጀመረው ዘመቻ ማንን ሾሞ ማንን ለማውረድ እንደሆነ አስቀድመው እንደሚያውቁ ተናግረዋል። አማተሪዝማና ፕሮፌሺናሊዝም ተለይቶ በአዲስ ብቁ ሙያተኞች ታክለውበት ሊዋቀር እንደሚገባው ያምናሉ። ከምንም በላይ ነጻ፣ ባለሙያዎች የሚመሩት፣ አትሌቶችን እየተቀራመቱና መያዣ እያደረጉ ቴክኒካል ጉዳይ ውስጥ የሚዋኙትን ሙሉ በሙሉ የሚያርቅ ጠንካራ የቴክኒክ ስታፍ እንዲኖር ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል። አንዱ የዚህ ውድድር ችግርም ይኸው እንደሆነ አመልክተዋል።
እንደ ማሳረጊያ
ህዝብ የለመደውን ውጤት እንዲያጣና እዲቆጣ ነው የተሰራውና እየተሰራ ያለው። ገድለው ቪዲዮ እየቀረጹ እንደሚቆምሩ የብሄር ፖለቲከኞችና አሰማተሪዎቻቸው በተመሳሳይ በፓሪስ ኦሊምፒክ መጀመሪያ ማግስት ጀምሮ የተቀነባበረ ዘመቻ ተከፍቷል። ዘመቻው ፓሪስ አትሌቶቹ ካልረፉበት ሰፈር ገብቶ እየተራመሰና አትሌቶቹን እንዲያመሳቸው ነው። ስልክ በመደወል ጫና የሚፈጥሩና የፈጠሩ እንዳሉ ማረጋገጫ አለ። ይህ ሁሉ የሆነው ለአትሌቲክሱ እድገትና ውጤት ማማር ሳይሆን ለስልጣን ነው።
ሁለት ሳምንት ታግሶ በአሳብ መሟገት፣ በመረጃና ማስረጃ መሞሻለቅ ሲቻል ቀድሞ የተሰራው ስህተት ሳያንስ ለመቀመጫ የሚደረገው ፍትጊያ ውጤቱ ላይ በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኗል። ከፓሪስ እየተባለ የሚወጣውና ያለ አንዳች ማጣራት በየማህበራዊ ግጾች የሚራገበው ቧልት ውጤቱ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል። ይህ አሳፋሪ ባህላችን እንዴት እንደሚታረም ለጊዜው ግልጽ ባይሆንም ዋናዎቹ የዘመቻው መሪዎች በውስጡ ያለፉ ሆነው መገኘታቸው ሃፍረቱን ድርብ ድርብርብ ያደርገዋል።
ከውድድሩ በሁዋላ አካፋውን አካፋ በሚል ይዘት ተከታታይ መረጃ ያለ አንዳች ወገንተኛነት እናቀርባለን። ራሳቸውን ሳያጠሩ፣ በስፕርቱ ስም የሚነግዱ የሚጮሁትን ነጋዴዎች ወደ ሁዋላ መለስ ብለን በመቃኘት መረጃ እንሰጣለን። በሌብነት የመንግስትን ኪስ እንደሚያውለቅ እርበ የለሽ እገር ኳስ ዝም አንልም። የመንግስትን በጀት በተጨዋች ግዢ ስም እያመነዠገ ፎቀቅ ለማይለው የሌብነት ምንጭ እነደሆነው እግር ኳስ “ስራህ ያውጣህ” በሚል በአትሌቲክስን ለማጅራት መቺዎች አሳልፈን አንሰጥም። ማንም ሆነ ማንም ከኢትዮጵያ ክብርና ባንዲራ በላይ አይደለምና በሰራው መጠን በመረጃ ህዝብ እንዲፈርድ አደባባይ ላይ ይውላል።