አሁን የራቀው ደስታ ተመልሷል፣ የተከፋው ልብ ተጠግኗል፣ ያቺ ኀያል ሠንደቅ በዓለሙ ፊት ከፍ ብላለች፣ እንደ ወትሮው ሁሉ ከፊት ቀድማለች፣ የሚመጥናትን ቦታ ይዛለች፤ አሁን ሌሎቹን እያስከተለች በድል ታይታለች፣ የደከመው ጉልበት ተቀስቅሷል፣ ምን ነካው የተባለው ወኔ ተነስቷል፤ የተኛው አንበሳ ተቆጥቷል፡፡
ኢትዮጵያ በልጇ ኮርታለች፣ በልጇ ደስ ተሰኝታለች፣ በፓሪስ ሰማይ ሥር ልጆቼን ምን ነካቸው፣ ወኔያቸውን ማን ወሰደባቸው፣ ጀግንነታቸውንስ ማን ነጠቃቸው እያለች የቆዘመችው፣ ምን ኾኑ እያለች የተከዘችው ኢትዮጵያ ጀግና ልጇ ሠንደቋን አስቀድሞ ሲገባ ተመልክታለች፤ ለክብሯ በጀግንነት ላቡን ሲያፈስስ አይታለችና ከቁዘማ ነቅታለች፣ ወደ ደስታም ተመልሳለች፡፡
የሠንደቃቸውን ከፍ ማለት፣ በጀግንነት ተነስቶ በድል መግባት የሚመኙ ኢትዮጵያውያን ከተከዙበት ተነስተዋል፤ በደስታ ተሞልተዋል፤ በደስታ ባሕር ውስጥ ገብተዋል፤ ስለ ምን ቢሉ አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ ሠንደቃቸው ደምቃለች፣ ከፍ ብላለች፣ በድል ቀድማለችና፡፡ የራቀ ደስታ መላሽ፣ የተኛ አንበሳ ቀስቃሽ ልጅ አግኝተዋልና በደስታ ተሞልተዋል፡፡
ድል የለመደችው፣ በድል የኖረችው፣ በዓለም አደባባይ መቅደምን ታሪክ እና ባሕል ያደረገችው ኢትዮጵያ በ2024ቱ የፓሪስ ኦሎምፒክ እንደቀድሞው ሁሉ ድል አላገኘችም፣ በምትታወቅበት ታሪክ አልደመቀችምና ኢትዮጵያውያን ተከፍተው ሰንብተዋል፤ ዘወትር ከፊት የምትገኘው ሠንደቃቸውን ፈልገዋል፤ አልሸነፍም የሚሉ እልኸኛ እና ሞገደኛ ልጆቻቸውን የት ገባችሁ? ምንስ ኾናችሁ? እያሉ ተጨንቀዋል፡፡ በዓለም አደባባይ አረንጓዴ ጎርፍን ሲያዩ የኖሩት፣ የድል ዜማ ማዜም የሚያውቁት ኢትዮጵያውያን ስለምን አይጭነቃቸው? ስለ ምንስ አይከፋቸው? ስለ ምንስ አያሳስባቸው? ለጀግና ከድል ውጭ ሌላ አይገባውምና፡፡
ዛሬ ግን አረንጓዴ ቢጫ ቀዩዋ ሠንደቅ በፓሪስ ደምቃለች፡፡ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን የሰጡትን አደራ የተሸከመው፣ የኢትዮጵያውያንን ጭንቀት እና ጉጉት በልቡ የያዘው ታምራት ቶላ 42 ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጦ ሠንደቋን ከሁሉ አስቀድሟልና፡፡
በፓሪስ ሰማይ ሥር እንደ ወትሮው በድል ያልደመቀችው ኢትዮጵያን ወደ ድል መልሷታል፡፡ በክብር ዙፋኗ ላይ አስቀምጧታል፡፡ አሁን ያለፉ ብስጭቶችን እና ሀዘኖቹን በደስታ ቀይሯቸዋል፡፡ ከምንጊዜውም ምርጡ አትሌት ቀኒነሳ በቀለ እና ዴሬሳ ገለታ ጋር ሀገሩን የወከለው ታምራት ቶላ ለአዘነች ሀገር የደስታ በረከት ሰጥቷታል፡፡ ታምራት የፓሪስ ጎዳናዎችን በጀግንነት አቆራርጦ ኢትዮጵያን በዓለሙ ፊት ቀዳሚ አድርጓታል፡፡ አሁን ወሬዎች ሁሉ ስለ እርሱ እንዲኾኑ አድርጓል፤ አሁን ከጀግና ሀገር የመጣ፣ የጀግኖችን አደራ የተሸከመ፣ ጀግና መኾኑን አስመስክሯል፡፡
በሮም፣ በአቴንስ ፣ በቶኪዮ እና በሌሎች የዓለም ታላላቅ ከተሞች የደመቀችው ኢትዮጵያን ዛሬም በፓሪስ አድምቋታል፡፡ ከድሉ በኋላ የዓለም አትሌቲክስ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጹ “ ኢትዮጵያዊው ታምራት ቶላ በኦሎምፒክ ታሪክ እጅግ አስቸጋሪ በኾነው የማራቶን ውድድር የኦሎምፒክ ክብረ ወሰንን ሰበረ” ብሏል፡፡
ታምራት ቶላ ከ24 ዓመታት ጥበቃ በኋላ የማራቶን ወርቅን ወደ ኢትዮጵያ አምጥቷል ይላል የዓለም አትሌቲክስ፡፡ በኦሎፒክ አዲስ ታሪክ ያስመዘገበው ኢትዮጵያዊው ጀግና 2፡06፡26 የገባበት ሰዓት ነው፡፡ ከፍታ እና ዝቅታ በበዛበት የፓሪስ ማራቶን የታላቅ ሀገር ታላቅ አደራ ይዞ የሮጠው ታምራት ቶላ አደራውን ከአዲስ ታሪክ ጋር ተወጥቷል፡፡
ቢቢሲ በዘገባው ኢትዮጵያዊው ታምራት ቶላ በ2008 ዓ.ም በኬኒያዊው አትሌት ሳሙኤል ዋንጂሩ ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን መስበሩን አመላክቷል፡፡ እ.አ.አ. በ2022 የዓለም ሻምፒዮን የኾነው ታምራት ቶላ ወደ ማራቶን የገባው ከሁለት ሳምንት በፊት ኢትዮጵያዊው የቡድን አጋሩ ሲሳይ ለማ ላይ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ነበር ይላል ቢቢሲ በዘገባው፡፡ ግማሽ ማራቶኑን ከሌሎቹ ተነጥሎ የሮጠው ታምራት ቶላ የአስደናቂ ድል ባለቤት ኾኗል፡፡
ሮይተርስ ደግሞ አዲስ ክብረ ወሰን በመጻፍ ያሸነፈው ታምራት ቶላ በፓሪስ ኦሎምፒክ ለሀገሩ የመጀመሪያውን ወርቅ አስገኝቷል ብሏል፡፡ ሱፐር ስፖርትም ታምራት ቶላ ከኦሎምፒክ ክብረ ወሰን ጋር ለሀገሩ የወርቅ ሜዳሊያ ማስገኘቱን ዘግቧል፡፡
ከድሉ በኋላ የኢትዮጵያ መሪዎችን ጨምሮ ኢትዮጵያውያን ደስታቸውን እየገለጹ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ሳኅለወርቅ ዘውዴ ከድሉ በኋላ ደስታቸውን ሲገልጹ”ታምራት ቶላ ለሕዝባችን የሚገባውን ደስታ እና ኩራት አመጣህለት፤ የዛሬው ድል ልዩ ትርጉም አለው፤ ፈጣሪ ይባርክህ” ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ደግሞ “በፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ ጀግናው አትሌት ታምራት ቶላ በማራቶን ውድድር ላይ ወርቅ በማግኘት ሠንደቅ አላማችንን በድጋሚ ከፍ አድርጓል” በማለት ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡
ታምራት ያመጣው ድል ከሩጫ ባሻገር ነው፣ ይህ ድል ክብር፣ አደራ፣ ታሪክ ነውና፤ የራቀች ደስታን መልሰሀል፣ የቆየ ታሪክ አስቀጥለሀል፣ አዲስ ታሪክም ጽፈሀል እና ክብር ይገባሀል፡፡
Via (አሚኮ)
