በተለያዩ ቦታዎች ከባድ የስርቆት ወንጀል የፈፀሙ ተከሳሾች በተደራራቢ የክስ መዝገብ እስከ 70 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ተቀጡ
ሳሙኤል ሀይሉ እና ሳቢር ከድር የተባሉት ተከሳሾች በተለያዩ ጊዜያት የስርቆት ወንጀሉን የፈፀሙት በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ በተለያዩ ወረዳዎች በመንቀሳቀስ ነው።
የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የልዩ ልዩ ወንጀሎች ምርመራ ማስተባበሪያ ሀላፊ ዋና ኢንስፔክተር በልሁ ወልደኢየሱስ እንደገለፁት ተከሳሾቹ የግለሰቦችን መኖሪያ ቤት እና የንግድ ቤቶችን በር በመገንጠልና በተመሳሳይ ቁልፍ ከፍተው በመግባት ላፕቶፕ ኮምፒውተር፣ ቴሌቪዥኖች እና ሌሎች የተለያዩ እቃዎችን ሰርቀው ወስደዋል።
ፖሊስ ወንጀል ፈፃሚዎቹን በቁጥጥር ስር አውሎ ባከናወነው ምርመራ የማስፋት ስራ የተሰረቁትን ንብረቶች ማስመለሱን የጠቀሱት የምርመራ ሃላፊው፤ እነዚህን ንብረቶች ከወንጀል ፈፃሚዎቹ እየተቀበለች በቤቷ ውስጥ ደብቃ ስታስቀምጥ የነበረች ትዕግስት ስመኝ የተባለች ግለሰብ ተይዛ ምርመራ እንደተጣራባትም አስረድተዋል።
በሶስቱ ተከሳሾች ላይ በአጠቃላይ ዘጠኝ የክስ መዝገብ የተደራጀባቸው ሲሆን ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በአምስቱ መዝገቦች ላይ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል።
በዚህም መሠረት ተከሳሽ ሳሙኤል ሀይሉ በእያንዳንዱ 5 የክስ መዝገቦች ላይ የተሰጠው ውሳኔ በድምሩ 70 ዓመት እስራት ሲሆን ፣ በሁለተኛ ተከሳሽ ሳቢር ከድር ላይ በእያንዳንዱ 5 የክስ መዝገቦች በድምሩ የ65 ዓመት እስራት ቅጣት መወሰኑን ዋና ኢንስፔክተር በልሁ አስረድተዋል።
የተሰረቁትን ንብረቶች በመሸሸግ ወንጀል የተከሰሰችው ትዕግስት ስመኝ ከአምስቱ የክስ መዝገቦች በአራቱ በእያንዳንዱ የሶስት አመት እስራት እንድትቀጣ እና ቅጣቱ በገደብ እንዲሆንላት የተደረገ ሲሆን በአንደኛው መዝገብ በተመሳሳይ በ 3 አመት እስራት እንድትቀጣና ቅጣቷን ማረሚያ ቤት ሆና እንድትፈፅም ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ማስተላለፉን የምርመራ ሃላፊው አብራርተዋል።
ተከሳሾቹ ከተደራጀባቸው ዘጠኝ የክስ መዝገቦች መካከል ውሳኔ ያላገኙት ቀሪ 4 መዝገቦች በሂደት ላይ እንደሚገኙም ሀላፊው ጨምረው ተናግረዋል።
ነሀሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም (ኢ.ፕ.ድ)