“የጠላ ጥንስስ ወንበር ላይ ቆማ ስታላቁጥ በአናቷ በርሜል ውስጥ ታለው ጥንስስ ላይ ተወትፋ ዳፍቃ ዳፍቃ ሞተች” ተብሎ በጎንደር ኤፍ ኤም ዜና እንደሰተራላት ሴት ከመሆን አትድኑም። አስተውሉ በማህበራዊ ሚዲያ ማዕበል ውስጥ መዳፈቅ ከጀመራችሁ ሰንብታችኋል። ዋ!!
መንግስት ሕዝብን ማድመጥ አለበት። ምክንያቱም መንግስት ስራው ሕዝብን ማዳመጥ ነውና። ቃል ኪዳኑም ጭምር!! መንግስት ይህን ካላደረገ ” ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ” እንደሚባለው ይመነገላል። ይጣላል። ይፈርድበታል። አገርና ትውልድን ለእዳና ለባንዳ አስረክቦ የታሪክ አተላ ሆኖ ይቀራል። ሕዝብም መንግስትን ማድመጥ አለበት። የሚያዳምጥ ህዝብ ራሱን ከውርደት፣ አገሩን ከውድቀት፣ መጪውን ትውልድ ከእዳና ከባንዳዎች ይታደጋልና። እናም መደማመጥ፣ መናበብ፣ ከምንም በላይ አስተውሎ መራመድ በሁሉም ዘንድ አግባብ ነው።
ለምን ይህ አልን? ይህን ያልነው አገሪቱን የሚመራው ብልጽግና በማህበራዊ ሚዲያ ማዕበል ውስጥ የሚንቦራጨቁ ከፍተኛ አመራሮች ስላሉትና፣ በማህበራዊ ሚዲያ ጫና የሚመሩትን ተቋም ቻናል ሲቀያየሩ፣ ሲያጠፉና ሲያበሩ የሚውሉ፣ ያገኙትን እየለጣጠፉ በላይክና በሼር እንደሚተዳደሩ የዘመኑ ” ሹመኛ አክቲቪስቶች” ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ተጥደው ስለምናያቸው ነው። ይህ ብቻ አይደለም ስራቸውን ትተው ” ዛሬ ምን ተባልኩ” በሚል ሞባይላቸውን ሲጠቀጥቁ የመዋላቸውና፣ በመንግስት በጀትና ጥቅማ ጥቅም የማህበራዊ ሚዲያ ተከላካይ ስኳድ ማሰማራታቸውን ስለምናውቅ ነው። በስም ጠቅሰን ማስረዳት እንችላለን።
ብልጽግና ማንም ሳይክድ የሚመሰክረው ታላላቅ ፕሮጀክቶችን አከናውነሃል። ለያውም ችግር ውስጥ ሆነህ፣ ሳትጸና፣ በዘመቻ ዓለም አድሞ ሲንጠን በነበረበት ጌዜ፤ አሁንም እያከናወንክ ነው። ” ሸጠው፣ ለወጠው፣ አወደመው…” ስትባል በተግባር አሳይተህ “እጅ በአፍ አስጭነሃል”። የተሰሩቱን ሜጋ ፕሮጅክቶች መዘርዘሩ ቢቀር በስንዴ፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ቱርፋት ፕሮግራም፣ በኮሪዶር መንገድ ግንባታ፣ በሳይንስ ማዕከልና ላይበሪዎች ግንባታ፣ ወዘተ … ከምንም በላይ ደግሞ በህዳሴ ግድብ ክንውንና የታነቀችውን ኢትዮጵያ የታነቀችበትን ገመዷን በጥሰህ የባህር በር ባለቤት ለማድፈግ የደፈርክበት ወኔና የተከተልከው ስልት ድንቅ ነው። የሚያምርብህም በዚህ መልኩ በታላላቅ ጉዳዮች ማተኮር እንጂ ከ120 ሚሊዮን ችግር ውስጥ በአንድ ቁልፍ የተፈታ ችግር ላይ ተቸንክሮ ማህበራዊ ሚዲያ ማጣበብ ሊሆን አይገባም። ዜናውን ለሚዲያ ትቶ ስራ ላይ ማተኮር የተሻለ ነው።
በሌሎች ወገኖች በኩል በሚዲያና ማህበራዊ አውዶች ተደራጅቶ በአሉባልታ መንግስትን ለመብላት፣ አገሪቱንም ለምናምንቴዎች፣ ለባዕዳን አሳብና ለኢትዮጵያ ህዝብ ታሪካዊ ጠላቶች አሳልፎ ለመስጠት የተቀናጀ ዘመቻ በመረጨት ሃያ አራት ሰዓት ያለማሳለስ የሚደክሙና በቅብብል ህዝብን በብሶት የሚያዝሉ ቀበኞች እንዳሉ እናውቃለን። እነዚህ የተደራጁ አካላት ጥቂት እውነት እየጨለፉ ለሚፈልጉት ዓላማ እንዲያመች አድረገው ያበጁትን ልውስ መረጃ ሲረጩ ባለማወቅ ሳያላምጡ የሚውጡ፣ አውቀውና አስበውበት የሚያሰራጩ ሃይሎች በዚሁ ክፉ ተግባራቸው ያደረሱት መከራና የህዝብ ስቃይ እንዲሁም አጠቃላይ አገራዊ አሳር ለማንም የተሸሸገ አይደለም። አያያዙ መቆሚያ ያለውም አይመስልም። እንደ አገር የደቦ ውንብድናና ውርጅብኝ እየናጠን ነው።
ይህን የተጠና፣ በጀት ያለው፣ መሪና ተመሪ ደቀመዝሙር የተበጀለት የማህበራዊ ሚዲያ ማዕበል እጃችሁን አጣጥፋችሁ”ዝም ብላችሁ ጠጡ” አንልም። በህግ ማረቅ አንዱና አግባብ ጉዳይ ቢሆንም፣ ማስተባበያ፣ ማኮላሻ፣ ማምከኛ ማዘጋጀት ያስፈለጋል። ይህ የሚከናወነው ግን በሚኒስትር፣ በሚኒስትር ዳዔታ፣ ወይም በከተማ አስተዳደሮችና ከፍተኛ አመራሮች ሳይሆን በመንግስትና በተቋማቱ በየደረጃ ባሉ የመረጃ ዴስኮች፣ እንዲሁም በደጋፊዎችና በመላው አገር ወዳዶች ነው። ከምንም በላይ በመንግስት ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን በኩል ሊሆን ነው የሚገባው።
አንዳንድ “ተከታይ አለን” የሚሉ ውርጋጦች፣ እፍኝ የማይሞሉ “የምንመራው ሃይል አለን” የሚሉ እየተነሱ 120 ሚሊዮን ህዝብ ላይ የስኒ ማዕበል ለመድፋት የሚዳዱትና ስርዓትን ጥሰው በአደባባይ የሚዳፈሩት አንዳንድ ባለስልጣናት እስራቸው ስለሚርመጠመጡ ነው። በተለይም ጀርባቸው ያልጸዳ ሃላፊዎች የማህበራዊ ሚዲያ ሰልፈኞችን እየታከኩ በምንኮራባቸው ተቋሞቻችን ሳይቀር እንዲዛበቱ አድርገዋቸዋል። የአገር ህልውናና ዘብ በሆነው የመከላከያ ሰራዊታችን ላይ፣ ልዩ ቅርሳችንና ወደብም ሆኖ እያገለገለን ባለው አየር መንገዳችን ላይ፣ ታዋቂና ብሄራዊ ጉዳዮቻችን ላይ መርዝ ሲረጩ ለማየት የደረስነው እንደ መንግስት ህግ አስከባሪዎች ጭምር ስራቸውን እንዳይሰሩ ማህበራዊ ሚዲያ ውስጥ የሚዋኙ እንቅፋት ስለሆኑባቸውም ጭምር ነው። ሳይበዛ የተገባውንና ደረጃቸውን የሚመጥን መረጃ መስጠት ትክክል ቢሆንም፣ ከዚህ በተቃራኒው የግል ስብዕና ግንባታ ላይ ስለተጠመዱ ስፍራቸው ላይ ያሉ ይመስላሉ እንጂ ከዋና ጉዳዮች ላይ ተንሸራተዋል። ዝም ከተባሉና በዚህ ከቀጠሉ አወዳደቃቸው ሌላውንም ይዞ የሚሄድ ነውና ጠንቀቅ!! ይህ የውድቀቱ ቁልቁለት ማሳያ ነውና ሳይቃጠል በቅጠል!!
ባለፉት ዓመታት እንዳየነው ከላይ ያነሳናቸው የመንግስት የመረጃ ማሰራጫና አሉባልታ ማምከኛ ተቋማቱ በተለይም የኮሙኒኬሽን ቢሮ ሽባ ነው። ይህ ነው የሚባል ፍሬ ያለው ስራ ሲሰራና ከሌሎች ወገኖች ኢትዮጵያ ላይ የሚረጨውን የወሬ ማዕበል ሲያመክን አላየንም። እንደ ካድሬ ሴሚናር ሲያዘጋጅና የራሱን ወገኖች ሲሸልም እንጂ አጀንዳ ተክሎ ሌሎችን መንዳት እጣ ፈንታው አይደልም። “ቆሞ ቀር” የሚባለው ትህነግ እንኳን በአቅሙ በረሃ ሆኖ በአንድ ጌታቸው ረዳ በኩል አጀንዳ እያመረተ ይርደው የነበረ ቤት እንደሆነ አንክድም። ደግነቱ በወቅቱ ህዝቡ ሁሉ የማህበራዊ አውዱ አርበኛ ነበርና አልተጋለጠም እንጂ።
አሁን ላይ አንዳንዴ እንደ እሳት አደጋ አጀንዳ እየተቀበለ ከሚጮኸው ውጪ ያው እንደቀድሞው አጀንዳ ሲሰጥና በመረጃ ግንባር ሆኖ ሲቆም አይታይም። ሌላውን ብንተወው በሶማሊያ የመንደር መንግስት እንድንበለጥ አድርጎናል። እነሱ አጀንዳ በሰፈሩ ቁጥር ምላሽ የምንሰጥ የሰነፍ ቡድን ግብ ጠባቂ አስመስሎናል። ድክመታቸው ጠቅላይ ሚኒስርቱን ጨምሮ አንዳንድ ባለስልጣናት በየአጋጣሚው በሚያቀቡት ዲስኩር ተሽፍኖ እንጂ ቢሮው እንደ አገር ሲታይ ሙት ነው። ሊበተን ይገባል። ኖረም አልኖረም ያው ነው። እንኳን አጀንዳ ሊሰፍር ቀርቶ የተሰራውንና የተሰጠውን መረጃ አደባባይ በትኖ ለመናገር የሚከብዳቸው ሃላፊዎች በትዝብት የምናይበት አቀመ ቢስ ቢሮ ነው። አንዳንዴ በዞሩበት የብሄር ብሄረሰቦችን ልብስ ለማስተዋወቅ የተሾሙ ሁሉ ይመስላሉ።
የማህበራዊ ሚዲያውንና “አክቲቪስት ነን” የሚሉትን ነጋዴዎችን ለመመከት በከፍተኛ በጀት (አስደንጋጭ በጀት) የተሰማሩትም ቢሆን የመንግስት ሚዲያዎች፣ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያሰራጯቸውን መልዕክቶች ቃል በቃል እየቀዱ ከመለጠፍ የዘለለ ሚና የላቸውም። አንዳንዶቹ ቢሞክሩም ከሌላው ወገን አደረጃጀት ጋር ሲነሳጸሩ እዚህ ግባ አይባሉም። ስለዚህ ይህኛውም አግባብ እንደ ኮሙኒኬሽን ቢሮው የከሸፈ ተቀላቢ ምስሏል። ይህንንም ዘርዝረን ማስረዳት እንችላለን። ይህን ስንል በወጉ ስራቸውን የሚሰሩ፣ በአግባቡ የሚቃወሙ ጭራሹኑ አይታዩም ለማለት አይደለም። ከሁለቱም ጎራ ታታሪዎች አሉና!!
አግባብ ባለው የመንግስት መዋቅር ወይም፣ በየተቋሞቻቸው የህዝብ ግንኙነት በኩል መረጃ ለህዝብ ማቀበል፣ በመንግስት መገናኛዎች በኩል ተግቶ በመስራት ሰፊውን ህዝብ በትክክለኛ መረጃ ማስታጠቅ፣ በማህበራዊ ሚዲያዎች ነቅቶ መሰራቱ ለመንግስት የህልውናው ጉዳይ በመሆኑ ለራሱ ይወቅበት። “ለራሱ ይወቅበት” ብለንልም በተወሰኑ ጉዳዮች “ዋ” ብለን ለማስጠንቀቅ ከላይ በነካካናቸው መነሻዎች እንገደዳለን።
አንድ ሊትር ዘይትና ሶስት ኪሎ ዱቄት በማንጠልጠል በዓል እየጠበቁ ከኪሳቸው እንዳወጡት፣ ንብረታቸውን ለበጎ አገልግሎት እንዲውል ብሎ እንደሸጠ ሩህሩህ ውዳሴ ፈለጋ ድሆችን የማህበራዊ ሚዲያ ማስታወቂያ ከሚያደርጉ አስመሳይ ካድሬዎች ጀምሮ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻና ጩኸት የመዋጥና የመስመጥ፣ አፍታ ቆይቶ የዛው ማዕበል ዋናተኛ የመሆን አዝማሚያ እያየን ነው። ይህ አደገኛ ነው። መላ ካልተባለ ማህበራዊ ሚድያው ላይ በጀት አፍስሰው ሊንዱን ለሚተጉት በአቋራጭ አጅ መስጠት ይመጣል።
ከላይ እንዳልነው ሕዝብን ማድመጥ የመንግስት ስራ ቢሆንም በሴራ በሚቀጣጠል የማህበራዊ ሚዲያ ባህር ውስጥ መንግስት ሲዋኝ ማየት ያስፈራል። የህዝብን ድምጽ ለይቶ ማዳመጥና በጅምላ ጩኸትን ሰምቶ መበርገግ ልክ አይሆንም። ቅንጅት ፓርላማ እንዳይገባ ሲጮሁ የነበሩ የሚዲያ ተዋንያኖች ዛሬ ውጭ ሆነው የተቃውሞውን ሰፈር በአካባቢ ተከፋፍለው የሚመሩት ናቸው። መቼ እንደሚጸጸቱ እሱ ይወቀው። ያለፈው ጸጽቷቸው ይቅርታ በመጠየቅ አርፈው ሊቀመጡ ሲገባ በሰከነ ቁጥር አድራሻ፣ አጀንዳና የሚደገፉትን የሴራ ማሽን በመቀየር፣ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በማበር እያደናገሩና ብር እያመረቱ ነው። ያሳዝናል።
” ፓርላማ ትገቡና ዋ” በሚል ዛቻ ሲያሰራጩና ጋዜጣ ሲያትሙ የነበሩ ዛሬ በገሃድ ጫካም ገብተዋል። ምርጫው የራሳቸው ቢሆንም ያኔ ” ፓርላማ እንዳትገቡ፣ አዲስ አበባን እንዳትረከቡ” ሲባሉ የሰሙ የቅንጅት አመራሮችና በምርጫ ያሸነፉ የህዝብ እንደራሴዎች ያን የመሰለ ምርጫና የህዝብ ትግል ገደል ከተው ቃሊቲ ተዘጋባቸው። “ሕዝብ ጭራ እንጂ ቀንድ አይደለም። ፓርቲ ቀንድ እንጂ ጭራ አይደልም” ሲባሉ ከመስማት ይልቅ ፍረጃን መርጠው ቀድመው ሳየይቀናጁ “ተቀናጀን”ብለው የክሽፈት ማስተማሪያ ምስላ ሆነው ቀሩ። እነሱም ከስህተታቸው መማር አቅቷቸው “ነውጥ እንጂ የሰከነ አካሄድ አይመችም” በሚል ድርጅት እያፈረሱ ድርጅት እያቋቋሙ እድሜያቸውን እየገፉ ነው። እንደባተቱን ሳይረጉ ያለፉም አሉ። እንዲሁ ማሊያ ሲቀያይሩ ለራሳቸውም ለሌላውም ሳይሆኑ ዘምናቸው ቋጭተው በስደትና የተቀመጡ፣ ቤታቸውም የቀሩ አሉ። ይህ አሁን በማህበራዊ ሚዲያ ጩኸት እየጦዙ ላሉት የብልጽግና ሹመኞች ትልቅ ትምህርት ይሆናል።
የወቅቱ መሪ የአቶ መለስ መንግስት ሴራ እንዳለ ሆኖ፣ ያንን የመሰለ ምርጫ በዜሮ ያባዙ ” ጅግና” ተብለው አሁን ድረስ የሳይበር ጡረተኛ ሆነው አገር የሚንጡት ለማን ብለው እንደሆነ ህዝብ እንዲመረምርና እንዲረዳ የመንግስት ሚዲያዎችና የኮሙኒኬሽን ቢሮ ከተራ የካድሬነት አባዜ ተላቀው ሊሰሩ በተገባ ነበር። ሁሉ በእጃቸው ሆኖ፣ ሁሉ በደጃቸው ሆኖ ሳለ ተኝተው በተራ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻና ጩኸት ሲሸበሩ፣ ተሸብረው ሲያሸብሩ፣ አሸብረው መንግስትም ሲያሸማቅቁ፣ መንግስትም ተሸማቆ ለጩኸቱ ምላሽ ለመስጠት በብርሃን ፍጥነት ኮሚቴና ኮማንዶ ሲያቋቁም እያየን ነው።ይህ ያስደነግጣል። ሁለት ምሳሌ እናንሳ።
የፓሪስ ኦሊምፒክ ሊጀመር ሲል ጩኸት ተጀመረ። ጩኸቱ የተደራጀና የተመከረበት ነበር። ብታምኑም ባታምኑም አልቅሰው ሲያስለቅሱ የነበሩት ኦሊምፒክ መንደር ድረስ እየደወሉ አትሌቶቹን ያሰቃዩ ነበር። “ይህን በሉ” በሚል መመሪያ ሲሰጡ የነበሩ የትልቅ ቀላሎች እንደነበሩ እዛው ሆነን አይተናል። ሰምተናል። ይህን ስንል ችግር አልነበረም ለማለት ሳይሆን ችግሩ የቀረበበትና እንዲቀርብ የተደረገበት አግባብ ልክ እንዳልሆነ ለማሳየት እንጂ የየትኛውም ቡድን አራጋቢ ለመሆን አይደለም። እንደ ባዕድ አገር ወኪሎች በራሳቸው አገር ሚዲያና ባልደረቦቻቸው በመሩት አመጽ ክፉኛ የተቀጠቀጠው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ኦሊምፒክ ቡድን ዙሪያ በተከታታይ መረጃ እናወጣለን፤ ለሚሰሙ የሰከኑ ወገኖች እንነግራለን። ለታሪክ ይመዘገብ ዘንድ ማንንም ሳንፈራና ሳንሸማቀቅ የምናውቀውን እናትማለን።
በቅብብል ህዝብ ምሬት ውስጥ ለመክተት ከፖለቲካው የማህበራዊ ሚዲያ ስልት የተቀዳው ይህ አካሄድ ከፓሪስ ሲያወጣቸው የነበሩት መረጃዎች፣ አዲስ አበባ ሲረጩ የነበሩት አሉባልታዎች በሙሉ በነጻ አካል ቢመረመሩ ከማፈር ውጪ አንዳችም አናተርፍም። ይህን የምንለው በፍጹም እርግጠኛነት ነው። ይህን ስንል ስህተትና ያልተገባ ድርጊት አልተፈጸመም ለማለት ግን አይደለም።
በዘንድሮው ኦሊምፒክ ግዙፍ ጥፋት የነበረው አንድ አትሌት በሶስት ውድድሮች እንድትወዳደር የተደርገበት አግባብ ነው። ባላት ሰዓት መሰረት ሶስቱንም ውድድሮች ለማድረግ መብት ቢኖራትም አግባብተው ቢያንስ አንዱን ሊያነሱባት ሲገባ ይህን አለማድረጋቸው ጥፋት ነው። ከዚያ ውጪ ያለው ጋጋታና ጩኸት “ስልጣን ነው”። ይህን ዕውነት ፓሪስ የነበሩ ሁሉ ያውቁታል። ግን ሊገልጡት አልቻሉም። ምክንያቱም “ተከፋይ፣ ተለጣፊ፣ ካድሬ፣ ከርሳም፣ ከሃዲ ወዘተ” በሚል በደቦ የስድብ ውርጂብኝ ይወርድባቸዋል። በዚህ የደቦ ፍርድ ፍርሃቻ ያዩትን መመስከር ትተው አሉባልታ ሲነግስ እያዩ ነው። ይህ አካሄድ ፈጽሞ አይጠቅምም። የጠፋውን ውጤትም አይመልስም። ጥፋቱ የት ጋር እንዳለና በማን እንደተፈጸመ ለማጥራትም አያስችልም። አገሪቱ ላይ ይዞት የሚመጣው ጣጣም ቀላል አይሆንም።
ስለ ፓሪስ ኦሊምፒክ ብዙ የቅጥፈት ዜናዎች እየተመረቱ ሲሰራጩ፣ ይህንኑ መረጃ ባለማወቅም ሆነ አውቀው በማህበራዊ ሚድያዎች ሲያቀጣጥሉት፣ ቤቱ ቀደም ሲል ከነበሩበት ችግሮች ጋር ተዳምሮ በውጤቱ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን አድሮም ቢሆን ስለምንሰማው ቀደሞ በድፍረት ይህን በማለታችን አናዝንም። ስድብም ቢሆን እንቀበላለን። ይህ ገለጻችን የሚገባቸው የጩኸቱ ጠማቂዎች አንድ ቀን በትክክለኛው ወቅት ሰለባ የሆኑት አካላት ይፋ ሰለሚያደርጉት ለምላሹ ከወዲሁ ተዘጋጁ እንላለን። ይህንንም እንደሚያደርጉት ሰለምናምን ” የዛ ጊዜ ሰው ይበለን” ባዮች ነን።
ሰሞኑ ተደፍራ ተገደለች በተባለችው ሕጻን ጉዳይ ደንግጠን ዜናውን አሰራጭተናል። ባሰራጨነው አሳዛኝ ዜና ሳቢያ ህዝብ መጮሁ አግባብ ነበር። ዜናው ጤና የሚነሳ፣ ልብን የሚያዝልና ህሊናን የሚፈታተን በመሆኑ ህዝብ መጮሁና ጫና ማሳደሩ ትክክል ነው። ለወደፊትም በተመሳሳይ ወንጀሎች ዙሪያ ተመጣጣኝ ቅጣት ሊበየን ስለሚገባ መንግስት ህጉን እንዲመረመር የተደርገው ጫናና የባለሙያዎች ማሳሰቢያ አግባብ ነው። ግን በርካታ ስህተቶች ታይተዋል። “ፍርደኛ ይግባኝ የማለት ህጋዊ መብቱን ይጣስ”የሚል ህጋገወጥ ጥያቄ ሲቀርብ ተስተውሏል። መንግስትም ለቅሶ ደራሽ ሆኖ፣ ድንኳን ጥሎ ደረት ሲመታና የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሲንደባለል ታይቷል። ይህ አግባብ ነው ብለን አናምንም። በዛ!! ለዚህ ነው ማህበራዊ ሚዲያ የሚጋልበው መንግስት ያልነው።
መንግስት ለዜጎች ቤትና ስራ መስጠቱ ምረጡኝ ሲል የሚገባው ህዝብ በቃ ሲል የሚያቋርጥበት የኮንትራት ስራው ነው። አልሆነልንም እንጂ ሁላችንም ከንቲባ ቢሮ ሳንሄድ፣ ሳናለቅስን ለብልጽግና ሳናጎበድድ በቀበሌያችን አማካይነት ቤት ማግኘት ነበረበን። ስለዚህ ለአንድ ” ተበዳይ” ቤት ሰጠሁ ብሎ ጉንጭ ሲያብሱ ፎቶ እየተነሱ፣ አልቃሽን ፊትለፊት አቁሞ ተራ የሚዲያ ንግድ መነገድ መንግስት አይመጥነውም። ይልቁኑም ባለስልጣናቱን እዛው አካባቢ ያሉ ካድሬዎች ምን ያህል የማህበራዊ ሚዲያ ሰለባ መሆናቸውን የሚያሳይ አደገኛ አዝማሚያ ይመስለናል። ነገም ሌሎች ህጻናት ይደፈራሉ። “ፍትህ ለእገሌ” እያሉ ካሁኑ እየተፈለፈሉ ነው። ይህ ለቅሶና ድህነት የወለደው ድራማ ይቀጥላል። ብልጽግናም ቁልፍ እያደለ እንባ ሲጠርግ የሚያሳይ ምስል ይረጫል። አይነፋም። ይልቁኑ መንግስት በዚህ ዓይነት ወንጀሎች ላይ ጅራፍህን አስተማሪ ለማድረግ ብትፈጥን ኖሮ ምን ያህል በተመሰገንክ ነበር።
ብዙ ዝርዝር ጉዳይ ማንሳት ይቻላል። አሁን ላይ መንግስት የኮሙኒኬሽን ተቋማቱን በወጉ በማዋቀር፣ የማህበራዊ ሰራዊቱን በአግባቡ በመረጃ በማስታጠቅ መስራት ላይ ካላተኮረ ወደፊትም አልቃሽና አስለቃሽ ሆኖ ይቀጥላል። እሱ አልቃሽ ሆኖ ሲቀጥል፣ ጉንጭ እየወለወለ ፎቶ ለጥፎ ላይክና ሺር ሲሸቅል፣ የማህበራዊ ሚዲያ ፊት አውራሪዎችን ጡንቻ ያበቅሉበትና አይኑ እያየ ማዕበል አስነስተው በዕውር ድንብር ይንዱታል። ትርምስምሱን ለማውጣት አመቺ ሁኔታዎች ስላሉ ይንጡናል። መናጥ ብቻ ሳይሆን ዙሪያውን በጠላቶች አጀንዳ ቃታ የሚስበው ሁሉ ከየስርቻው እየወጣ አገሪቱን ይቀራጫታል። አንዳንድ አካባቢ አሁን እንደሚታየው የጎበዝ አለቃ መናኸሪያ እንሆናለን። ስለዚህ መንግስት ሆይ የፕሮፓጋንዳ ጓዳህን ተመልከት። ባለስልጣናት ቢያንስ የማህበራዊ ሚዲያውን ነገር ለቀጠራችኋቸው ተውላቸውና ስራችሁን ስሩ። ሁሉንም በፖሊሲ መክቱ። አለያ የጠላ ጥንስስ ወንበር ላይ ቆማ ስታላቁጥ በአናቷ በርሜል ውስጥ ታለው ጥንስስ ላይ ተወትፋ ዳፍቃ ዳፍቃ ሞተች” ተብሎ በጎንደር ኤፍ ኤም ዜና እንደሰተራላት ሴት ከመሆን አትድኑም። አስተውሉ በማህበራዊ ሚዲያ ማዕበል ውስጥ መዳፈቅ ከጀመራችሁ ሰንብታችኋል። ዋ!!