‘ሻይን ማይ ክራውን’ በአስራ ስድስት ዓመቷ የፒኤችዲ እጩ የሆነችውን ሀና ቴይለርን እናስተዋውቃችሁ ሲል ዛሬ አንድ ዘገባ አቅርቧል፡፡ እንደዘገባው ሀና ኢትዮጵያዊት ናት፡፡ ይህንን ማንነቷንም ባለፈው ግንቦት ወር ከቴክሳስ ዩኒቨርስቲ በዲግሪ ስትመረቅ የኢትዮጵያን ባንዲራ በገዋኗ ላይ ከፍ አድርጋ ማሳየቷን ጠቅሷል፡፡ ጋዜጠኞች ‘አስማተኛዋ’ በሚል በአድናቆት ጽፈውላታል።
መጽሔቱ እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያት በምትነሳቸው ፎቶዎችና በማህበራዊ ሚዲያዎች በምትፅፋቸው ፅሁፎች ኢትዮጵያን እንደምትገልፅ አስረድቷል፡፡ ሀና የተወለደችው በደቡባዊ ኢትዮጵያ ክፍል በሚገኝ አንዲት መንደር ውስጥ ነበር፡፡ በተወለደች በጥቂት ጊዜ ውስጥ እናቷ በቲቢ በሽታ የተነሳ በሞት ትለያለች፡፡

ያኔ የአስር ወር ህፃን የነበረች ሲሆን አንድ አሜሪካዊ ቤተሰብ በጉዲፈቻ ወደ አሜሪካ ሊወስዳት ችሏል፡፡ ሀና እንደእናቷ በቲቢ በሽታ ብትያዝም የህይወት ዘመን የህክምና ተከታታይ ለመሆን መብቃቷ የስኬቷ ጅማሬ ነው፡፡ ስትናገርም ‹‹ከቲቢ በሽታ ለማገገም መቻሌ ወደህክምናው ዓለም እንድቀላቀል ያስቻለኝ ከመሆኑም በላይ የአሜሪካን የህክምና አጠባበቅ ጥንካሬ የሚያመላክት ነው›› ብላለች፡፡
የምትማርበት የቴክሳስ የሴቶች ዩኒቨርስቲ እ.ኤ.አ በ1901 የተመሰረተ ሲሆን ባለፈው ግንቦት ወር በሶሲዮሎጂ በዲግሪ ስትመረቅ በዩኒቨርስቲው ታሪክ በእድሜ ትንሿ የሚል ሪከርድን ለማስመዝገብ የቻለች ናት፡፡ አሁን ደግሞ በዚሁ ዘርፍ የዶክትሬት ዲግሪዋን ለመስራት ትምህርቷን ቀጥላ ትገኛለች፡፡ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችውም በህክምናው መስክ ለማድረግ ወደምታቅደው ስራ ከመግባቷ በፊት በትምህርት ላቅ ያለ ደረጃ ለመድረስ በማሰብ እንደሆነ ተናግራለች፡፡ እንደገለፀችውም የቲቢ በሽታ በኢትዮጵያም ብቻ ሳይሆን በአሜሪካ ጭምር አሁን እየተስፋፋ ይገኛል፡፡
ይህንን ለመቀነስ በእናት አገሯም ሆነ በሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገራት የበኩሏን ጥረት የማድረግ ውጥን አላት፡፡ እንደዘገባው ሀና በአስራ ስድስት ዓመቷ ዲግሪ መያዟ በራሱ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ይሁንና አሁን ደግሞ ይህንንም አልፋ በዚህ ዕድሜዋ የዶክትሬት እጩ ተብላ ለመጠራት በቅታለች፡፡
Via Henok Degfu