የግል ትምህርት ተቋማት መምህራን የደሞዝና ጥቅማጥቅም ጥያቄ በእኔ በኩል የሚያልፍ አይደለም ሲል የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አስታወቀ!
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር በቅርቡ በሃገር ደረጃ ይደረጋል ከተባለው የደሞዝ ጭማሪ ጋር ተያይዞ በግል የትምህርት ተቋማት የሚያስተምሩ መምህራን በሚመለከት ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ እንዳላቀረበ ገልጿል፡፡
ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የማህበሩ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሺመልስ አበበ በግል ትምህርት ተቋማት የሚያስተምሩ መምህራን በኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት የአባልነት ምዝገባን ስላላከናወኑ ማህበሩ እነሱን በሚመለከት ከመንግስት ጋር የሚያደርገው ንግግር የለም ብለዋል፡፡
ታዲያ የግል የትምህርት ተቋማት መምህራን ጥቅማጥቅማቸውና መሰል መብቶቻቸው በምን መንገድ ነው የሚስተናገዱት ስትል አዲስ ማለዳ ጥያቄ ያቀረበችላቸው ምክትል ፕሬዝዳንቱ በርካታ የግል የትምህርት ተቋማት መምህራን በእኛ ስር እንዲደራጁ ጥሪ እያቀረብን ነው በዚህም ዙሪያ ተከታታይ ውይይት እያደረግን ነው ሲሉ መልስ ሰጥተዋል፡፡
አሁን ላይም የግል ትምህርት ተቋማት ከሰሞነኛው የደሞዝ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር የመመለስ ስልጣንም ሆነ መብት የለውም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰራተኞች ኮንፌደሬሽን (ኢሰማኮ) ከቀናት በፊት የግል ተቋማት ሰራተኞች እንደ መንግስት ሰራተኞች ሁሉ የደሞዝና ተያያዥ ጥያቄዎቻቸው ሊመለሱላቸው ይገባል ሲል ጥያቄ ማቅረቡ አይዘነጋም፡፡
Via addis reporter