የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ሰበብ በማድረግ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉና ምርት በሚደብቁ ሕገወጥ ነጋዴዎች ላይ ንግድ ፍቃድ እስከመሰረዝ የሚደርስ ርምጃ እንደሚወሰድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ መንግሥት ይፋ ያደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ በመዲናዋ አንዳንድ ነጋዴዎች አላግባብ ዋጋ ጭማሪዎችን የማድረግና ምርት የመደበቅ ሁኔታ ተስተውሏል፡፡
ቢሮው ይህን ሕገወጥ ተግባር ለመከላከል የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል ያሉት አቶ ሰውነት፤ በዚህ ድርጊት ተሳትፈው በሚገኙ ነጋዴዎች ላይም የንግድ ፈቃድ እስከመሰረዝ የሚደርስ ርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡
ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ቢሮው ባከናወነው የክትትልና ቁጥጥር ሥራ 71 የንግድ ድርጅቶች ላይ ርምጃ መወሰዱን ያስታወቁት አቶ ሰውነት፤ ርምጃው ምርት በማከማቸት፣ በማሸሽ እንዲሁም ከ25 በመቶ በላይ አላግባብ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ የተወሰደ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የክትትልና ቁጥጥር ሥራው በቀጣይነትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰው፤ በሕገወጥ ሥራዎች ላይ በሚሳተፉ ነጋዴዎች ላይ ንግድ ፍቃድ እስከመንጠቅ የሚደርስ ርምጃ ይወሰዳል ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
ቢሮው ከዚህ ቀደም ሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን የመከታተልና መቆጣጠር ሥራዎችን እንደሚሠራ አስታውሰው፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ይፋ መሆንን ተከትሎ ከማዕከል እስከወረዳ ያሉ ባለሙያዎችን አሰማርቶ የበር ለበር ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ምርት የሚከማችባቸው ተብለው በተለዩ መጋዘኖች ላይም ፍተሻ እየተደረገ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት፡፡ቢሮው የሚያከናውነው ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ የህብረተሰቡ ጥቆማ ሕገወጥነትን ለመከላል ወሳኝ ሚና እንዳለው የገለጹት አቶ ሰውነት፤ ሕገወጥ ተግባትራን በመፈጸም ህብረተሰቡ ላይ ጫና የሚያደርሱና ማሻሻያው እንዳይሳካም እንቅፋት የሚፈጥሩ አካላት ላይ የሚያደርገውን ጥቆማ አጠናክሮ በመቀጠል ርምጃ እንዲወሰድባቸው ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከ400 ሺህ በላይ ነጋዴዎች መኖራቸውን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ አብዛኛው ነጋዴ ሕግን አክብሮ ሥራውን እያከናወነ የሚገኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ እነዚህ ሕጋዊ ነጋዴዎች አላግባብ የዋጋ ጭማሪ በማድረግና ምርት በመደበቅ የንግድ ሥርዓቱን የሚረብሹ ነጋዴዎችን በመጠቆም ርምጃ እንዲወሰድባቸው ለማድረግ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
ማህበረሰቡ ሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ሲመለከት በ8588 ነጻ የስልክ መስመር በመደወል፣ በየወረዳው ለሚገኙ የንግድ መዋቅሮች እንዲሁም በአቅራቢያው ለሚያገኛቸው የሕግ አስከባሪ አካላት ጥቆማውን ማድረስ እንደሚችል አቶ ሰውነት ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26 /2016 ዓ.ም