እኛ የመጀመሪያዎቹ! ብለው አቶ ቃልኪዳን ኃይሉ በድሬቲዩብ 19 January 2016 ይህን ጽፈው ነበር ምንም ሳልቀንስና ስልጨምር “ምን የጥበስ ታዲያ ” ብዬ ላኩላችሁ። ሳነበው በሳቅ ሽንቴን ጨርሻለሁ። ፍሬከስርስኪም ይመስላል። ይህን ሁሉ ማስታውሱም ገረሞኛል። ብቻ አስቆኝ ጭብጡን ስላጠፋብኝ ሌሎችም እንዲወዛገቡ …
እኛ የመጀመሪያዎቹ! ብለው አቶ ቃልኪዳን ኃይሉ
የዳንኤል ክብረትን እኛ የመጨረሻዎቹን አነበብኩት፡፡ ስለ ያ ትውልድ የመጨረሻዎች ሁኔታና አኳኋን ጥሩ አድርጎ ፅፎታል፡፡ ስለዚህም እኛ የዚህ ትውልድ የመጀመሪያዎችን ታሪክ መጻፍ ፈለኩ፡፡ እኛ የመጀመሪያዎቹ በ 1980ዎቹ፤ 1990ዎቹ ላይ የተወለድን እኛ የመጀመሪያዎቹ ነን፡፡
እኛ የመጀመሪያዎች በአዲስ የትምሕርት ስርአት የታነፅን፤ አስከ አራት መውደቅ የለም ተብለን በገፍ ያለፍን፤ ኬጂ ሀ ኬጂ ለ ተብለን ሙዋለ ሕጻናት የተማርን፤ መልእክተ ዮሐንስ፤ አቦጊዳ ሔውዞ ያልተማርን፤ የግዝዙን ቁጥር ያላጠናን፤ ግብረ ገብ ሳንማር ሲቪክስ የሚባል ትምህርት የተማርን፤ በአንድ አስተማሪ ሁሉንም የትምህር አይነት የተማርን፤ የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) ለብሰን ትምህርት ቤት የሔድን፤ በየካቲት ደብተር ጀምረን በሲኒየር ላየን የጨረስን፤ እስከ ስምንተኛ ክፍል ሒስትሪን፣ ጆግራፊን፣ ሕብረተሰብ ተብለን አንድ ላይ የተማርን፡፡
እኛ የመጀመሪያዎቹ አስረኛ ክፍል ማትሪክ የወሰድን፤ ቴክኒክና ሙያ የገባን፤ የመሰናዶ ትምሕርት ፈተና ወስደን ውጤታችን በኤ ቢ ሲ (A,B,C) ሳይሆን በቁጥር ከአምስት መቶና ከሰባት መቶ የታረመልን፤ ሰላሳ ምናምን ዩንቨርስቲ ተመድበን የተማርን፤ ኮስት ሼሪንግ የምንከፈል፤ ብዙዎቻችን ለስራ ብለን የድርጅት አባል የሆንን ጥቂቶችም በፍላጎትና በአላማ አባል የሆንን፡፡ ክፍለ ሀገር፣ አውራጃ፣ ጠቅላይ ግዛት ሳይሆን ዘጠኝ ክልሎች፣ ዞን፣ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳና ቀበሌ የምናውቅ፤ የኢትዮጵያን ካርታ ካለኤርትራ የምናውቅ፤ የኢትዮጵያና ኤርትራን ጦርነት “አሸው!” እያልን ለእናት ሐገር ወታደር ድጋፍ የሰጠን፤ በዘጠና ሶስት አመተ ምሕረት የበጠበጥንና ፍንዳታ፣ አደገኛ ቦዘኔ ተብለን የተሰደብ፡፡
እኛ የመጀመሪያዎቹ ኃይሌ ገ/ስላሴ ዳንኤል ኮመንን፣ ፖርቴርጋትን ሲያሸንፍ፤ ብዙ ሪከርዶችን ሲሰባብር፤ ደራርቱ ቱሉና ጌጤ ዋሚ ታሪክ ሲሰሩ፤ ጥሩነሽ ብርሀኔ ሀደሬንና ደራርቱን ስትተካ፤ ቀነኒሳ ኃይሌን ሲተካ፤ ጥሩነሽና መሰረት ሲፋለሙ ተመልክተናል፡፡
ቀነኒሳና ስለሺ ኃይሌን በአይን የመሮጫ ትራኩ ላይ ሲፈልጉና በልባቸው ሲያከብሩ ተመልክተናል፡፡ ከሰላሳ አመት በኋላ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫ አልፋ በአፍሪካ የእግር ኳስ መድረክ ላይ የተመለከትን፡፡ እኛ የመጀመሪያዎቹ በዘጠና ሰባት አመት ምሕረት የቅንጅትንና የኢሕዴግን የምርጫ ክርክር ሰፍ ብለን ያየን፤ አስኳል፣ ኢትኦጵ፣ ምኒሊክ፣ ሳተናው፣ ነጻነት፣ ሮዝ፣ አዲስ ነገር፣ አዲስ ጉዳይ፣ ፍትሕ፣ ፋክት፣ አዲስ አድማስ፣ ሪፖርተር… ያነበብን፡፡
እኛ የመጀመሪያዎቹ ጥላሁንን አድንቀንና አክብረን፤ የኤፍሬምን፣ የሙሉቀንን፣ የሚኒሊክ ወስናቸውን፣ የአለማየሁ እሸቴን፣ የአስቴር አወቀን… መረዋ ድምጽ እያዳምጥን፤ ቴዲ አፍሮ የሚባል ብላቴና የሙዚቃ ንጉስ አድርገን ያነገስን፤ ቴዲ ጡት ላይ ፈረም ብለን ያጮሕን ያጯጯሕን፤ ቴዲ አፍሮ ጃ! ያስተሰርያል አለ ብለን ግቢ ላይ ቆመን ጃ! ጃ! ጃ! ብለን ክንዳችንን የሰነዘርን፤ ቴዲ ታሰረ ብለን ሰልፍ የወጣን፡፡ እኛ የመጀመሪያዎች በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ታላቅ ፊልምን፣ ሕብረት ትርኢትን፣ መቶ ሀያን፣ የመስኮት ድራማን ያየን፤ የማያና ኮማንደርን ፊልም የኮመኮምን፤ ቲቪ አፍሪካ ላይ ሪሲሊንግ፣ ላቪንግን፣ ማጋቫይረንን…ያየን፡፡
በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ኤፍ 97.1 የሰማን፤ ቀጠለናም ብዙ የግል ኤፍ ኤሞችና ዝግጅቶቻቸውን የሰማን፤ የግል ቴሌቪዥኖች ያየን፤ ቪኤች ኤስ ፊልም አይተን በሲዲና ዲቪዲ የተቀየረልን፤ ከሲዲም በመቀጠል በፍላሽና ሚሞሪ ብዙ ፊልሞች ይዘን የተመለከትን፤ በኤም ፒ ስሪ ዘፈን አዘጋጅተንና ገዝተን ያዳመጥን፡፡ እኛ የመጀመሪያዎቹ በቪኤች ኤስ የሕንድ፣ የሽዋዚንገር፣ የቫንዳም፣ የስቴቨን ሴጋል፤ ታይታኒክን… ብቻ ሳይሆን ያየነው ሕይወት እንደዋዛ፣ ሲኦልን፣ የእሳት ራትን… ያየን፡፡ ሲኒማ ኢትዮጵያ፣ ሲኒማ አምፒርና አምባሳደር የህንድና የሆሊውድ ፊልም ሳይሆን የአማርኛ ፊልም ያየን፡፡
በውሳኔ ፊልም ያለቀስን፤ በቀዝቃዛ ወላፍን ያዘንን፤ በጉዲፈቻ ፊልም የተገረምን፤ ኤድና ሞልና ቦራ አሚውዝመንት ስሪዲ (3D፣ ሰቨን ዲ (7D)ና ኤይት ዲ (8D) ያየን፤ ካልዲስና ቤሉስ ቁጭ ብለን ኬክ የበላን ቡና የጠጣን፡፡ ሚሊኒየም አዳራሽ ኮንሰርት የታደምን፡፡ እኛ የመጀመሪያዎቹ ቤታችን ሳይሆን በሀምሳ ሳንቲም ቪዲዮ ቤት ቁጭ ብለን ቫንዳምን፣ ጄኪ ጃንን፣ ሽዋዚንገርን፣ ጀትሊን፣ ክሪስታከርን፣ ጄሰንን፣ ሊዎርዳኖ ዲካፕዮ፣ ብሩሱሊን፣ ሻሩክን፣ ሀቢታም ፓሻን፣ ሻዋሪያን፣ ኽርቲክን ያደነቅን ስናድግ እንደ እነሱ ለመሆን የተመኘን፡፡
እኛ የመጀመሪያዎቹ ፈታ ብለን ሚሊኒየሙን ያከበርን፤ ኤሚኒየምን፣ጄዚን፣ አሸርን፣ ፋት ጆውን፣ ሪሀናንን፣ ቢዮንሴን፣ አሸርን ዘፈን የሰማንና ያደነቅን፤ ዘፈን በሲዲ ፕሌየር ያዳመጥን ወክማንና ኢርፎን ለጇራችን ማዳመጫ የተጠቀምን፤ ከለር ዴይ፣ ካልቸር ዴይ፣ ቫላንታይን ዴይ፣ ዋተር ዴይ፣ ክሬዚ ዴይ፣ ጀንትል ዴይ ያከበርን፤ ለፍቅረኞቻችን የተለያዩ ዘፋኞችን የፍቅር ዘፈን በካሴት ቀጥሎም በሲዲ አዘጋጅተን የሰጠን ነን፡፡ እኛ የመጀመሪያዎቹ ቤት የሌለን፤ ኮንዶሚኒየም ተመዝግበን በያመቱ እጣ ወጣ አልወጣ ብለን የመንጠብቅ፤ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተን ከቀበሌ ገንዘብ የተበደርን፡፡ ከሀገር ለመውጣት በጣም የምንወድ፤ በእግራችንና በመርከብ አቆራርጠን አውሮፓና አሜሪካ የገባን፤ አረብ ሀገራት በገፍ የሄድን፤ በዲቪ አሜሪካ የሔድን ያልሔድንም በያመቱ ጠብቀን ታትረን ዲቪ የምንሞላ፡፡
እኛ የመጀመሪያዎቹ የመጀመሪያውን ጥቁሩን ፕሬዝዳንት በአሜሪካ ያየን፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ሕብረት ሲቀየር ያየን፤ ኔልሰን ማንዴላ ሲሞቱ የተመለከትን፤ ሙሀመድ ጋዳፊ ሲገደሉ፤ ሆስኒ ሙባረክ ለዘመናት ከከረሙበት ስልጣናቸው ሲወርዱ ያየን ነን፡፡
እኛ የመጀመሪያዎቹ ሙሉ ባንድ ትተን በዲጄ የሰረግን፤ ሽማግሌ መላኩን ቀዝቀዝ አድርገን በአደባባይ እግር ስር ተደፍተን አግቢን ብለን የጠየቅን፤ በማርቼዲስ፣ በቦልስ፣ በቤቢ ፍያት መሰረግና ማጀብ ትተን በሊሞዚን፣ በቪ ኤይት፣ በዴክስ፣ በያሪስ፣ በቪትዝ፣ በቢኤም ደብሊው.. ያገባን፣ ያጀብን፣ የታጀብን፡፡ እኛ የመጀመሪያዎቹ ጤፍ በሁለት ሺህ፤ በሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር ሲሸመት ያየን የሸመትን፤ ዶሮ ሶስት መቶ ብር ሲሸጥ ያየን፣ አንድ ኪሎ ስጋ ሁለት መቶ ብር የገዛን፤ አንድ ኪሎ ብርቱካን ሰላሳ አምስት ብር የገዛን፤ ጋዝ ከአንድ ብር ተነስተን አስራ አራት ብር፤ በሀምሳና በአንድ ብር ታክሲ እንዳልተሳፈርን በብር ከሀምሳ፣ በሁለት ከሀምሳ፣ በአምስት ብር የተሳፈርን ነን፤ እንቁላል የብር አምስት እንዳልገዛን አንድ እንድ እንቁላ ሶስት ከሀምሳ የገዛን፡፡
እኛ የመጀመሪያዎቹ በኮምፒውተር የተማርን፤ ካርቦን ኮፒ ትተን ፎቶ ኮፒ ያደረግን፤ ስካነር የተጠቀምን፤ ላፕቶፕ ማየት የመንካት እንዲሁም ባለቤት የመሆን እድል የገጠመን፤ ጎረቤት ተጠርቶ በባለማዞሪያው ስልክ ከማውራት፤ ወደ ሚነካካው የራስ የሆነ ባለመስመር ስልክ የተሸጋገርን ቆይተንም የእጅ ስልክ የያዝን፤ ከትላልቁ ስልክ ወደ ትናንሽ ስልኮች መያዝ የተሸጋገርን፤ ባለካሜራውን ዘማናዊ ስልክ የያዝን፤ ሶስተኛውን ጀነሬሽን (ስሪ ጂ) የተጠቀምን፡፡ በኢንተርኔት ያሆ፣ ሆት ሜይል፣ ጂ ሜይል፣ መልእክት የተፃፃፍን፡፡
በፌስቡክ ላይ ፎቶ የለቀቅን፤ ፌስቡክ ላይ ፍቅረኛና የትዳር አጋር ያገኘን፤ ፌስቡክ ላይ ብሶታችንን የተናገርን፤ መንግስትን የሰደብን፤ የዘርና የሀይማኖት ስድብ የተሳደብን፡፡ እኛ የመጀመሪያዎቹ የሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህንን ግጥም በራሳቸው ድምፅ በሲዲ ያዳመጥን፤ የበእውቀቱን ፅሁፎች በሲዲ የሰማን፤ የኤፍሬም ስዩምን ግጥም በስልካችን ያዳመጥን፤ ተስፋዬ ካሳ አይጠገቤ ቀልዱን ይዞ የሞተብን፤ ክበብው ገዳን በተስፋዬ ካሳ ተክተን ያደነቅን፡፡
ስብሀት ገ/እግዚአብሔርን፣ ማሞ ውድነህን፣ አዳም ረታን ያየን፡፡ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፣ ስብሀት ገ/ እግዚአብሔር፣ የአለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌን፣ ሙናዬ መንበሩ፣ አስናቀች፣ ጥላሁን ገሰሰ፣ ምኒሊክ ወስናቸው፣ እንግዳዘር፣ ሲራክ አለሙ፣ አለባቸው ተካ፣ ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ ሲሞቱና በክብር ሲቀበሩ ያየን፡፡ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በድረ-ገፅና በብሎግ ላይ ሲፅፍ ያደነቅን፣ የተመሰጥን፡፡ የሲድኒ ሼልደንን፣ የሮበርት ሉድለምን፤ የዳን ብራወንን፣ የዳንኤል ስታሊን፣ የኬን ፎሊትን የትርጉም መጻሕፍ ከማንበብ ወደ ዴርቶጋዳና ሌሎች የሀገር ውስጥ መጻሕፍትን ማንበብ የጀመርን፡፡
ከደጀኔ ጥላሁን የኢትዮጵያ ሬዲዮ ቆንጆዎቹ፣ ሳቤላና መሰል ልቦለድ ትረካዎችን ዘለን የአንዱአለምን የሸገር ካፌ የወግ ትረካዎችን ያዳመጥን፡፡ ልብ ለልብ፣ እርሶ ቢሆኑ ምን ያደርጋሉ፣ እግር ኳስ በሬዲዮ፣ አይሬ፣ ኢትዮጲካል ሊንክ፣ አዲስ ዜማ፣ ታዲያስ አዲስ፣ ዘጠና ደቂቃ፣ ጨዋታ፣ ይበቃል… የተባሉ የሬዲዮ ዝግጅቶችን በጉጉትና በፍቅር ጠብቀን የሰማን፡፡
ኳስ በመሰለ መንግስቱ በሬዲዮ ሲተላለፍ የሰማን፤ በመንሱር አብዱል ቀኒ፣ ገነነ መኩሪያ፣ አበበ ግደይ፣ ዳዊት፣ ፍቅር ይልቃል… ኳስና ሩጫ ሲተነትኑ ሬዲዮኑንና ከጣብያ ጣብያ እየቀያየርን የሰማን ነን፡፡ እኛ የመጀመሪያዎቹ፡፡