ስልጣናቸውን ያለአግባብ በመጠቀም እና ሀሰተኛ ሰነድ በመገልገል በመንግስት ይዞታ ስር የሚገኝ የጋራ መኖሪያ ቤት ለመሸጥ የሞከሩ የወረዳ አመራሮች በቁጥጥር ስር ዋሉ።
የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶችን በማዘጋጀት ስትሸጥ የነበረች ግለሰብ እንደተያዘችም ተጠቁሟል።
የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ቦታው ገላን ኮንዶሚኒየም ነው። ፖሊስ ከክፍለ ከተማው ፍትህ ፅ/ቤት በደረሰው ጥቆማ መነሻነት ምርመራ የማጣራት ስራ መጀመሩን የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀል እና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ም/ዳይሬክተር ኮማንደር አየለ ላቀው ተናግረዋል፡፡
ገላን ኮንዶሚኒየም ብሎክ 231/4 የቤት ቁጥር 19 የሆነ የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ የደረሰው ግለሰብ የሚጠበቅበትን ክፍያ መፈፀም ባለመቻሉ የጋራ መኖሪያ ቤቱ ወደ መንግስት ተመላሽ ተደርጓል፡፡
ይሁን እንጂ በክፍለ ከተማው የወረዳ 12 ዋና ስራ አስፈፃሚ፣ የቤቶች ፅ/ቤት ሃላፊ ፣ የወሳኝ ኩነቶች ፅ/ቤት ሃላፊ እና ሌላ አንድ የሥራ ሃላፊ ይህንን እያወቁ ስልጣናቸውን ያለ አግባብ በመጠቀም በህገ-ወጥ መንገድ በተዘጋጀ ሃሰተኛ የቤት ካርታ ለሌላ ግለሰብ ቤቱን እንዲያከራይ የማዋዋል ስራ ሰርተዋል ።
ግለሰቦቹ በሂደት ቤቱን ወደ አዲስ አበባ ቤቶች ሲስተም ውስጥ አስገብተው ግለሰቡን የቤቱ ባለቤት ለማድረግ አቅደው ሲሰሩ እንደነበር የጠቀሱት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ ለስራ ማስኬጃ ብለው ከዚሁ ግለሰብ ላይ 850 ሺ ብር መቀበላቸውንም አስረድተዋል፡፡
ወደ ሲስተም ከገባ በኋላም ቤቱን ሽጠው ገንዘቡን ለመከፋፈል እቅድ የነበራቸው ሲሆን ሂደቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ የ3 ወር ቤት ኪራይ ተቀብለው ተከፋፍለዋል፡፡ ፖሊስ በደረሰው ጥቆማ እና ባደረገው ማጣራት ቤቱን እንዲያከራይ የተደረገው ግለሰብ ይዞት የተገኘው የቤቱ ካርታ ሃሰተኛ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
በተከናወነው ተጨማሪ ምርመራ ሀሰተኛ ሰነዶቹን እያዘጋጀች ለአንድ ሰነድ ሶስት ሺህ ብር ስትቀበል የነበረች ተጠርጣሪ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ልዩ ቦታው ሰፈራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በቁጥጥር ውላለች፡፡
በህግ አግባብ በመኖሪያ ቤቷ በተደረገ ብርበራም 45 የተዘጋጁ ሀሰተኛ የቤት ካርታዎች ፣ 25 ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችና የልደት የምስክር ወረቀቶች፣ 105 በመንግስት እና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ስም የተዘጋጁ ሀሰተኛ ክብ ማህተሞች ፣108 በተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ፣ግለሰቦች እና ሆቴሎች ስም የተዘጋጁ ሀሰተኛ ቲተሮች ፣ሀሰተኛ ሰነዶችን ለማዘጋጀት ስትጠቀምባቸው የነበሩ የተለያዩ ቁሳቁሶች በቤቷ ውስጥ መገኘታቸውን ኮማንደር አየለ ተናግረዋል።
በአጠቃላይ የወረዳ የሥራ ሃላፊዎቹን ጨምሮ 6 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።
ነሐሴ 25 ቀን 2016 ዓም EPD