በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ወረዳ 9 ቀጠና 3 ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን ጀርባ ( አፓርታማ አካባቢ) በተደራጀ መንገድ በአካባቢ ጥበቃ ለአረንጓዴ ልማት በህጋዊ ካርታ በተሰጠው ስፍራ በተለያየ ግዜ በመግባትና ደን በመጨፍጨፍ በህገወጥ መንገድ መሬት ለመውረር ሲዘጋጁ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በተለያየ ግዜ መልኩን እየቀያየረ ባልተገባ መንገድ መሬት መውረር ተግዳሮት ሆኖ እንደ ዘለቀ ነው።
ዛሬ ማለዳ 12 ሰዓት ላይ በቁጥጥር ስር የዋሉት 97 የሚደርሱ ግለሰቦች ( 20 ሴቶችና 77 ወንዶች) ከቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12፣ ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 እና 6 የመጡ ሲሆን በተያዙበት ወቅት በወረዳው የሚገኙ ወጣቶችን በማሳመን የተጠቀሰውን ለአረንጓዴ ልማት የተከለለ ቦታን በመቆጣጠርና በመንግስት አስተዳደር ላይ ጫና በመፍጠር ቦታውን በህገ ወጥ መንገድ በመውረር በቁጥጥራቸው ስር ለማዋል አቅደው እንደነበረ ከሰጡት ቃል ለማረጋገጥ ተችሏል።
በህገወጥ የመሬት ወረራው 150 የሚደርሱ ግለሰቦች እጃቸው ያለበት ሲሆን 10 ግለሰቦች በማለዳ በተካሄደው ኦፕሬሽን ማምለጣቸው ተገልጿል። ጉዳዩ ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር ውለው በፖሊስና በሚመለከታቸው አካላት ተጨማሪ የማጥራት ስራ እየተሰራ መሆኑን ላፍቶ ኮሚዩኒኬሽን ያደረሰን መረጃ ያሳያል።
(ከንቲባ ፅ/ቤት)