ኢትዮጵያን የወከሉ አምባሳደሮቿ በፓሪስ ኦሊምፒክ ውድድር ላይ ባሉበት ወቅት ያልተገባ አስተያየት በማህበራዊ ሚዲያዎችና እንዲሰራጭ ምክንያት የሆኑት የባህልና ስፖርት ሚንስትር ሚንስትር ዴኤታ አቶ መስፍን ቸርነት ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ተሰማ። ካሁን በሁዋላ አፋቸውን እንዲሰበስቡ ማሳሰቢያ ተቀብለዋል። ዝግጅት ክፍላችን አምባሳደር የሚለውን ስያሜ በስራው ላይ ለሌሉ ሁሉ ስለማይጠቀም አቶ ብለናቸዋል።
አዲሷ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ ምክትላቸውን ቢራቸው በመጥራት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሆነው “የሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የማያውቀውን መረጃ ከመስጠት እንዲቆጠቡ ማሳሰቢያ ሰጥተዋቸዋል” ሲሉ በስፍራው የተገኙ ለኢትዮሪቪው ገልጸዋል። አክለውም እንደ መንግስት ኃላፊ እንዲንቀሳቀሱ ከአለቆች ጥብቅ መመሪያ መሰጠቱንም ነግረዋቸዋል።
ሚኒስትሯ አጠንክረው “አትለቶቹ እኮ ውድድር ላይ ናቸው” በማለት እንደገሰጿቸው ያመልከቱት የመረጃው ሰዎች አቶ መስፍን ይቅርታ መጠየቃቸውን ገልጸዋል። ዳግም በዚህ መልኩ መረጃ እንደማይሰጡ ቃል ገብተዋል።
የኦሊምፒክ ውድድር ከመጀመሩ ቀደም ሲል የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮችና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አመራሮች በተገኙበት፣ በስፖርቱ ዘርፍ በነበሩ የግንኙነት አግባቦችና የአሠራር ተግዳሮቶች ዙሪያ ውይይት ሲያደርጉ ሚኒስትሯ ማሳሰቢያ አዘል ማስጠንቀቂያ መስተታቸው ይታወሳል።
የአሠራር ክፍተቶች ጥናት በማድረግ፣ በቀጣይ በውይይት የመፍታት ከሁሉም አገር አቀፍ የስፖርት ማኅበራት ጋር በቅንጅት ለመሥራት በመግባባት መርህን መሠረት ያደረገ ተቋማዊ ግንኙነት መፍጠር እንደሚያስፈልግ ሚኒስትሯ ባወሱበት በዚሁ ስብሰባ፣ መርሃን የጠበቀ ግንኙነት ሊኖር እንደሚገባ ገልጸው ነበር።
አቶ መስፍን በጥናት ያልተደገፈ፣ ሙሉ ሪፖርት ባልቀረበበት ጉዳይ ላይ ከአንድ ፖሊሲ አውጪና አስፈጻሚ ሚኒስትር በማይጠበቅ ደረጃ ” የአትሌቲክስ ውጤታማነታችን በአደገኛ ቀውስ ላይ ነው ፣ ጀብደኛ ፣ አምባገነን ፣ ሴሬኛ እና ክፉ ሰዎች ስፖርታችንን ጠፍረው ይዘው እያሰቃዩት ይገኛሉ ” ሲሉ የሰጡት መግለጫ ፍጹም የሚኒስትር መስሪያ ቤቱ እንዳልሆነ ተነገሯቸዋል። እንዲህ ያለ አደገኛ ድምዳሜ በመንግስት ሹመት ወነበር ላይ ሆኖ መስጠት እጅግ የወረደ እንደሆነም ተነግሯቸዋል።
ችግሮችን፣ ጥፋቶችን፣ ቴክኒካል ጉዳዮችንም ሆኑ ማናቸውንም ህጸጾች በማጥናት፣ በመረጃ አስደግፎ መስራት እንዳለበት አስቀድሞ የገለጹት ሚንስትሯ አሰራሩ በተቋም ደረጃ እንጂ በግለሰብ ደረጃ ስላልሆነ ጥንቃቄ ሊወሰድ እንደሚገባ አስረግጥርው መናገራችውን ለማረጋገጥ ተችሏል።