በአዲስ አበባ ከተማ ለህዝብ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ የቴሌኮም ገመድን የሰረቁና ንብረት በመቀበል የተጠረጠሩ ስድስት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለጸ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ የመሰረት ልማት ወንጀሉን ፈፅመዋል የተባለው በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ካራ ቆሬ አካባቢ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ከተያዙት ግለሰቦች አንደኛው ተጠርጣሪ ጨለማን ተገን አድርጎ የኢትዮ ቴሌኮም ንብረት የሆነውን ገመድ በመቁረጥ በማዳበሪያ ውስጥ ጠቅልሎ ተሸክሞ ሲሄድ ስራ ላይ በነበሩ የወንጀል መከላከል የፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር ሊውል የቻለ መሆኑን የጠቀሰው ፖሊስ፣ በቁጥጥር ከማዋል በኋላ በተሰራው ምርመራ ሌሎች ለወንጀሉ ተባባሪና በተቀባይነት ከወንጀሉ ጋር ቀጥተኛ ተሳትፎ ነበራቸው የተባሉ 6 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል፡፡
ግለሰቦቹ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 አካባቢ የተሰረቀ የኤሌክትሪክ ገመድ የሚቀበሉ ስለመሆናቸው የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር ዘሪሁን አግዜ ገልፀዋል።
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት ከ1 ሺህ ሜትር በላይ የሚሆን የኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ንብረት የሆነ ገመድን ከነመቁረጫቸው አብሮ መያዙንም ፖሊስ አመላክቷል፡፡







ኮማንደር ዘሪሁን አክለው፣ የተሰረቁ የኢትዮ ቴሌኮምና የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ ገመድን ከሚቀበሉ ግለሰቦች ቤት 3 ጀነሬተሮች፣ 4 የኃይል ማስነሻ ባትሪ እንዲሁም ባለሙያዎች ለስራ የሚጠቀሙባቸውን ቀበቶዎች መያዛቸውን ጨምረው ጠቁመዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ በመሰረተ ልማት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ከመከላከል ባሻገር አጥፊዎች በህግ አግባብ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ኮማንደሩ፣ በመንግስትና ህዝብ ንብረቶች ላይ ጉዳት የሚያደርሱና የስርቆት ወንጀሎችን የሚፈፅሙ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ህብረተሰቡ የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ሲሉ ጥሪውን አቅርበዋል።
ሐምሌ 25/2016ዓ.ም police