በተለምዶ ሿሿ እየተባለ በሚጠራው የወንጀል አፈፃፀም በርካቶች ንብረታቸውን አጥቸዋል። ፖሊስ ወንጀል ፈፃሚዎቹን ለመቆጣጠር ከሚያከናውነው ልዩ ልዩ ተግባራት ባሻገር ወንጀል ፈፃሚዎቹ የእጃቸውን እንዲያገኙ ከሚመለከታቸው የፍትህ አካላት ጋር በትስስር ይሰራል ፡፡ በተለያዩ የከተማዋ ጎዳናዎች ላይ እየተንቀሳቀሱ የማታለል ወንጀል ለመፈፀምና የወንጀሉን ፍሬ ለመካፈል አሰቀድመው በመስማማት መጋቢት 30 ቀን በ2015 ዓ.ም ተሽከርካሪ በመጠቀም የወንጀል ድርጊቱን ሲፈፅሙ የተገኙ አስራ ሶስት ተከሳሾችን ፖሊስ እጅ ከፍንጀ መያዙን በተመለከተ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ፖሊስ በፌስ ቡክ ገፃችን ላይ መዘገባችን ይታወሳል ።
በወቅቱ ተከሳሾቹ በሰሌዳ ቁጥር ኮድ3-79184 ኦሮ በሆነ ተሽከርካሪ እና በተከሳሽ አሊ ረሺድ አሽከርካሪነት በመንቀሳቀስ እያንዳዳቸው በቀን 3ሺህ ብር ሊከፍሉት ተስማምተው እንደነበረ ከጉለሌ ክ /ከተማ ፖሊስ መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በዕለቱ ተከሳሽ ጋዲሳ በቀለ የተባለው ግለሰብ የስራ ድርሻው የተሽከርካሪው ረዳት መምሰል ሲሆን የግል ተበዳይን ትራፊክ ይቀጣናል ውረድልን በማለት የወንጀል ድርጊቱ እንዲፈጸም ሲያመቻች ተከሳሽ ዳዊት ባንቲ የተባለው ግለሰብም የግል ተበዳይ ኪስ የነበረውን ቴክኖ ስልክ በማውጣት የስርቆት ወንጀሉን የፈፀመ ነው ፡፡ ሌሎች 10 ተከሳሾች ደግሞ ተሳፍሪ በመምስል የግል ተበዳይን በማዋከብ ወንጀሉ እንዲፈፀም አሰተዋፅኦ ያደረጉ መሆናቸውን የምርመራ መዝገባቸው ያስረዳል፡፡
በወንጀሉ ዙሪያ ተደጋጋሚ አቤቱታ የተቀበለው የጉለሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ፤ የክትትልና የምርመራ ቡድን በማዋቀር አስራ ሶስቱን ተከሳሾች በቁጥጥር ሰር አውሎ ከተከሳሾች ላይ የተገኙትን የወንጀል ፍሬዎች እና የግል ተበዳይ ያቀረበውን አቤቱት በመቀበል መዝገቡን አደራጅቶ በአቃቤ-ህግ በኩል ክስ ሊመሰረትባቸው ችሏል።
የተከሳሾችን ጉዳይ ሲከታተል የቆየው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የመናገሻ ምድብ 2ተኛ የወንጀል ችሎትም ሃምሌ 23 እና 24 /2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሾች ያቀረቡትን የተለያዩ የቅጣት ማቅለያ እና አቃቤ-ህግ ያቀረበውን የቅጣት ማክበጃ ተመልክቶ የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 32/”ሀ እና ለ ” እንዲሁም የ669/3/”ሀ እና ለ”ን በመተላለፍ የተፈጸመ ወንጀል ነው በማለት ተከሳሾችን ያሰተምራል ሌሎችን ያስጠነቅቃል በማለት የእስር ውሳኔ አሰተላልፏል። በዚህም መሠረት፡- ተከሳሽ አሊ ረሻድ߹ጋዲሳ በቀለ߹ አቤኔዘር አብራር߹ዳዊት ባንቲ ߹ጊዜ እንዳለ߹ ቃልኪዳን አንዳረጋቸው እያንዳንዳቸው በ12 አመት ፅኑ እስራት እንዲተቀጡ ሲወሰንባቸው ተከሳሽ ከበቡሽ ጌታነህ በ11አመት ፅኑ እስራት እንድትቀጣ ተወስኖባታል ፡፡ ተከሳሽ መስፍን በየነ߹ አስፋው ኡመር ߹ ጌቱ ገብረ አማኑኤል߹ አይምሩ መሃመድ߹ ሙሉጌታ ግዛው߹ በእያዳንዳቸው ላይ 13አመት የእስር ውሳኔ ሲተላለፍባቸው እድላዊት አላምራው14 አመት እስራት ተቀጥታለች
በአብዛኛው በተለምዶ ሿሿ እየተባለ የሚጠራው ወንጀል የሚፈፅመው በትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ላይ ቢሆንም በትራንስፖር መጠበቂያ ቦታዎች ߹በገበያ ቦታዎች߹ በመዝናኛና በሌሎች ቦታዎችም ሊፈፀም ስለሚችል ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያርግ እንደሚገባ ያሳሰበው ፖሊስ አጠራጣሪ ነገሮችን ሲያጋጥሙ ለፖሊስ በመጠቆም ህብረተሰቡ ተባባሪነቱን ማጠናከር እንደሚጠበቅበት መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
ዘጋቢ :ሳጅን ፈለጉሽ አሻግሬ













